ኢትዮጵያ የዕዳ ጫናዋ 52 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል ተባለ

Views: 282

የኢትዮጵያ መንግስት ከውጪ ሀገራትና ከሀገር ውስጥ አበዳሪዎች የተበደረችው ዕዳ 731 ቢሊዮን ብር መድረሱን የገንዘብ ሚኒስትር አስታወቀ፡፡

ሀገሪቱ አጠቃላይ ከውጪና ከሀገር ውስጥ የተበደረችው ዕዳ 52.3 ቢሊዮን ዶላር ወይም 731 ቢሊዮን ብር መድረሱን የገንዘብ ሚንስትር የ11 ወር ሪፖርቱን ለፓርላማው ባቀረበበት አስታውቋል፡፡

ባለፈው ጥር ወር የሀገሪቱ አጠቃላይ ዕዳ ወደ 50 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ እንደነበርም ለማወቅ ተቸሏል፡፡

ባለፉት 11 ወራት ኢትዮጵያ 9.4 ቢሊዮን ዶላር ዕዳዋን ለመክፈል የቻለች ሲሆን፣ በቀረበው ሪፖርት መሠረትም ሀገሪቷ ለዚህ ትልቅ ዕዳ የተዳረገችው አነስተኛ የሆነ የኤክስፖርት ንግድ በመካሄዱና የግል ዘርፉ ደካማ ተሳትፎ እንዲኖረው በመደረጉም እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለአስር አመታት ከተመዘገበው የመንግሥት ኢንቨስትመንት አንጻር በብድር ላይ የተመሰረተ ቢሆንም፣ የኢኮኖሚው እድገት አገሪቷ ዕዳዋን እንድትመልስ ማድረግ አልቻለችም፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ እዮብ ተካልኝ ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት “በጣም ብዙ ገንዘብ ተበድረናል፤ ነገር ግን በተሰጠን የግዜ ገደብ መክፈል አልቻልንም፤ ገንዘቡን የተበደርነው ለመሠረተ ልማት ግንባት ቢሆንም የታሰበው ውጤት ላይ መድረስ አልቻልንም” ብለዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ የዕዳ ክፍያ ፕሮግራም ለማዋቀርና እንደ ቻይና ያሉ ዋና ዋና አበዳሪዎቿን ለመደራደር የተገደደች ሲሆን፣ አዳዲስ እዳዎችንና አዳዲስ የህዝብ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ማስወገድ እንደሚያስፈልጋትም ተነግሯል፡፡

“ለንግድ የሚሰጥ ብድርን አስወግደናል፤ ይህን ያደረግንበት ምክንያትም እንደነዚህ አይነት ብድሮች ሲቆዩ የተጠራቀመ ዕዳ ይሆኑና ትልቅ ችግር ይፈጥራሉ” ሲሉ አቶ እዮብ ተናግረዋል፡፡ አክለውም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በገንዘብ ሚኒስትር የተከናወኑ ሥራዎችን አብራርተዋል፡፡

ሀገሪቷ እስካሁን ድረስ ስንዴና የምግብ ዘይት ከውጪ በማስገባት ነው የምትጠቀመው ያሉት አቶ እዮብ፣ ይህ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባለች ታዳጊ ሀገር ተቀባይነት የለውም፤ ለኢኮኖሚ እድገት የሚሆኑ አቅርቦቶችን ቅድሚያ ሰጥተን እንሰራለን፤ በአምራች ዘርፍ፣ በማእድን ፍለጋ፣ በቱሪዝም፣ እንዲሁም በእርሻው ዘርፍ” ብለዋል፡፡

በ 2009 የሀገሪቷ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 80.56 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ተገልጿል፡፡ በዚህ ዓመትም መንግሥት 9.2 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት እንደሚጠብቅ አስታውቀዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com