“ግዙፍ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መሸጥ የለባቸውም”

Views: 171

ግዙፎቹ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መሸጥ እንደሌለባቸው የፖለቲካዊ ምጣኔ ኃብት አዋቂው ፀደቀ ይሁኔ (ኢንጂነር) ገለፁ::

ፀደቀ ይሁኔ (ኢንጂነር) የኢትዮጵያ ቴሌ ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽንን እና የኢትዮጵያ መብራት ኃይል አገልግሎትን ከመሸጥ እና ወደ ግል ይዞታ ከማዘዋወር አስቀድሞ በሀገሪቱ ዴሞክራሲን ማስፈን እንደሚስፈልግ ገልፀዋል፡፡ የሁለቱ ተቋማት አግልግሎት አሰጣጥ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ከተሞች ድረስ ትስስር ያለው ነው ያሉት ኢንጂነሩ፣ አሁን ባለው ያልተረጋጋ የገበያ ሥርዓት ወደ ግል ይዞታ የሚዘዋወሩ ከሆነ ጉዳታቸው ያመዝናል ብለዋል፡፡

ኩባንያዎችን የሚገዙ ግለሰቦችም ስኬታማ ድርድር ለማካሄድ የተረጋጋ የፖለቲካ ምኅዳር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ድርጅቶቹን ለመሸጥ ዴሞክራሲ ባይሰፍንም እንኳን፣ የአካባቢ ምርጫዎች እስከሚካሄዱ መጠበቅ አግባብ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ‹‹ቢያንስ ምርጫውን አካሂዶ ኅብረተሰቡ በራሱ ጉዳይ፣ በዕለታዊ አጀንዳዎቹ የሚጠመድበትን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ምኅዳር ማደላደል አለብን›› ብለዋል፡፡ የአካባቢ ምርጫው ባለፈው 2010 እንዲከናወን የታቀደ ቢሆንም እስከ አሁን አልተካሄደም፡፡

በሥራ ላይ ካለው ኅብረተሰብ 41 ከመቶው ለራሱ ሥራ የፈጠረ ነው፡፡ 39 በመቶው ደግሞ በግብርና ሥራ የተሰማራ ሲሆን፣ 11 ከመቶው በመንግሥትና በግል ተቋማት ተቀጥሮ የሚሰራ ነው፡፡

ፀደቀ ይሁኔ (ኢንጂነር) እንደሚሉት ብዙ ጊዜ ውይይቶች የሚደረጉት በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ተቀጥረው ስለሚሠሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ነው፡፡ ‹‹89 ከመቶ ስለሆነው የኅብረተሰብ ክፍል ሳንወያይ ለውጥ ማምጣት አንችልም፡፡›› ብለዋል ፀደቀ ይሁኔ፤ ከቢቢሲ የአማርኛው ክፍል ጋር ባደረጉት ቆይታ፡፡ ይህ ባልሆነበት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱም ውጤታማ እንደማይሆን አብራርተዋል፡፡ የመጀመሪያው የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በተለይም አቶ መለስ ዜናዊ በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ስኬታማ እንደነበርም ገልፀዋል፡፡

‹‹የኢሕአዴግ አብታዊ ዴሞክራሲ መስመር ህፀፆች አሉበት፡፡ በነፃነትና በእኩልነት የሚያምን ድርጅት ነፃነትና እኩልነትን አላራመደም፡፡ በገበያው እና በፖለቲካ ውስጥ ነፃ ገበያንና ነፃ ፖለቲካን ዋና ምሰሶዎቼ ናቸው ብሎ የተነሳ ድርጅት ነፃ ገበያም አላካሄደም፡፡ ነፃ ፖለቲካም አላካሄደም፡፡›› ብለዋል ኢንጂነሩ፡፡

መንግሥት የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ላይ እንጂ አጠቃላይ ንግዱን መቆጣጣር እንደሌለበትም ገልፀዋል፡፡ ይህንን ለማድረግ ግን የኅብረተሰቡን ንቃተ ህሊናም ማሳደግ ተገቢ መሆኑንን ነው ያብራሩት፡፡ ፀደቀ ይሁኔ በሪል ስቴት ንግድ ላይ የተሰማሩ ሲሆን፣ የምጣኔ ሃብት ባለሙያም ናቸው፡፡ በቅርቡም ‹ሾተል› በሚል ርዕስ የፖለቲካዊ ምጣኔ ሃብት ዘውግ ያለው መጽሐፍ ለንባብ አብቅተዋል፡፡ በመጽሐፉ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶችን ህፀፆች ከሳይንሳዊ ንድፈ ሃሳቦች ጋር አዛምደው የተነተኑ ሲሆን፣ ለተግዳሮቶች የመፍትሔ አቅጣጫዎችንም ጠቁመዋል፡፡

ግዙፎቹ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መሸጥ እንደሌለባቸው የአዲስ አበባና የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የነበሩት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ክቡር ገና በቅርቡ ባሰራጩት የጥናት ወረቀት ላይ ማሳሰባቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com