ከሃሳብ-መንደር (ክለይቱ) -፪-

Views: 217

እንግዲህ ዓምዱ ‹‹ከሃሳብ መንደር››ም አይደል?! የሰው ዘር ሲኖር-ሲኖር-ሲኖር፣ በኑሮው ውስጥ ያጋጠሙትን ችግሮች ሲፈታ፣ መልሶ ሌላ ችግር ሲገጥመው አሊያም መፍትሄው ራሱ ችግር ሲወልድ- ሲከስት፣ እንደገና ደግሞ የመፍትሄ ሃሳብ ሲያቀርብ እና ሲኖር፤ ህይወት ራሷ እያፈላሰፈችው፣ እያንፈላሰሰችው፣ እያንገሸገሸችው ጣፋጩን ከእሬት እያጣመ ደግሞ ሲኖር፣ በመኖር ሂደት ላይ ዘመን አይሽሬ አድርጎ የሰው ዘር ከሰጠን እውቀት፣ ክህሎት፣ ጥበብ ላይ ዓባይን በማንኪያ እንዲሉ በጥቂቱ እየጨለፍን በሃሳብ መንደራችን እየተጓዝን ዜኖች ጋ ደርሰናል፤ እነኾ፡-

ዜኖች

 • ጥላቻ አንድ ቀን ፍቅር የመሆን እድል አለው፡፡ ስሜታዊነት ግን ፍቅርም ጥላቻም ሳይሆን የሚቀር ከንቱ ነገር ነው፡፡
 • የሴቶች አእምሮ ከማፍቀር ብቻ ይልቅ ያፈቀሩትን የራስ ንብረት የማድረግ ፍላጎት ተፈጥሮ የቸራቸው በመሆኑ በመፈቃቀር፣ ለሚመጡ እውነቶች እምብዛም ትኩረት አይሰጡም
 • በሂማሊያ ተራሮች ላይ ያለች አንዲት ወፍ ነበረች ወፏ አካሏ አንድ ቢሆንም ጭንቅላቷ ግን ሁለት ነበረ፡፡ አንድ ቀን አንደኛው ጭንቅላት ጣፋጭ ፍሬ አግኝቶ ሲመገብ ሲያየው ሌላኛው በጣም ቀና፡፡ ደግሞም ተበሳጨ፡፡ በነጋታው በእልህ የመረረ ፍሬ አግኝቶ መብላት ጀመረ፡፡ ይሄኔ ሌላኛው ጭንቅላት እባክህ እኔና አንተ የተለያየ ጭንቅላት ቢኖረንም አካላችን አንድ ነውና ይሄ የምትበላው ፍሬ መርዝነት አለውና ይገድለናል ሲለው ያኛው ጭንቅላት ግን ቅናቱ ማስታዋሉን ነስቶት ስለ ነበር ዝም ብሎ መብላት ጀመረ ከሰዓታቶች በኋላ ሁለቱም ላይመለሱ አሸለቡ፡፡
 • ንስሀ የሚያሰገባኝ በውስጤ የማይሞተው ተስፋ እንጂ የነፍሴ ሀጢያት አይደለም (ጆንሰን ሳሙኤል)
 • ነፃነት! እና ማህበራዊ ነፃነት! ስነ ልቦናዊ ነፃነት፡፡ ግላዊ ቢባልም ሶስተኛው ነፃነት የሰው ልጅ ከውስጡ ከሚነሳ ግጭት (conflict) ነፃ የሚሆንበት (normal freedom) ነው፡፡
 • ነፃነት መንግስት የሚሰጥህ ሳይሆን በመንግስትህ ውስጥ በሚኖርህ ድምፅና በዚያ ላይ ተመስርተህ ከመንግስትህ ጋር በሚኖርህ ስምምነት ላይ የሚፈጠር ጉዳይ ነው፡፡
 • ሀይማኖቶች የተለያየ ባህሪና መልክ እንዳላቸው! እንዲሁም ባላቸው ታሪካዊ ግንኙነት፣ በፈጣሪ መኖር፣ በአለም አፈጣጠር፣ በሰው ልጅ ፍላጎትና ነፃነት በትንቢት ሚና፣ በህግ ትርጓሜ፣ በሰው ልጅ ባህሪያትና ደስታ ዙሪያ የየራሳቸውን አቋምና ልዩነትን ይዘው ለዘመናት ዘልቀዋል፡፡
 • የእግዚአብሔር እውቀትና ፈቃድ በእኛ አላዋቂነት ሊፈተን አይችልም፡፡ ጥረታችን ሁሉ ከቃላት ያለፈ እውቀት አያስተርፍልንም (ሜይሞናይደስ)
 • ፍቅር ከምናየው ነገር ነጥሮ ወደ ውስጣችን የሚገባ ነው ወይስ ውስጣችን የተቀመጠና እሱን የሚስበው ነገር ሲመጣ ከእኛው ወደዚያኛው ነገር ደርሶ (ነጥሮ) የሚመለስና መላ አካላችን የሚመራ ነገር ነው?

በእውቀትና በአላዋቂነት መካከል ለረዥም ጊዜ የኖረ (ፍቅር) ብቻ ነው፡፡

 • በምትመርጠው ፍቅር ውስጥ የራስን ውበት ትፈጥራለህ ከፈጠርከው ውበትም ጋርም በፍቅር ትወድቃለህ እንግዲህ ዘላለማዊ ሊያደርግህ የሚችለውን ውበት መርጠህ በፍቅር ወድቀሃልና የፍቅርንም ተፈጥሮ እንዲሁ ትረዳለህ፡፡
 • መምህር መንገዱን አሳይቶን የሚመለስ እንጅ ከእኛ (ላይ) እጃችንን ይዞ ሲሰራ የሚኖር ማለት አይደለም፡፡
 • የሰውን ልጅ መክፈት የሚቻለው በፍቅር፣ በጥበብ፣ በስቃይና፣ በፀሎት ብቻ ነው
 • በጋራ ለዘመናት ከምናምናቸው እውነቶች ውጭ እውነት አንደ ግለሰቡና ማህበረሰቡ እምነት፣ ምልክት፣ የዘመን አስተሳሰብ ፍላጎትና ባህል የምትለያይ ነገር ስትሆን ተጨባጭ የሆነችና ለማንኛውም ሰው በአንድ ጊዜና ቦታ አንድ የሆነች ነገር ናት፡፡
Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com