የገንፎ አሰራር

Views: 521

በአኅጉራችን አፍሪቃ ገንፎ መደበኛ ምግብ ነው፡፡ የበቆሎ- ገንፎ፣ የገብስ- ገንፎ፣ … ከልዩ-ልዩ የእህል ዘሮች ጋር ተደባልቆና ተቀይጦ ይዘጋጃል፡፡ ይህ አመጋገብ ለጤና ተስማሚ ከመሆኑ ባሻገር ለአካል ጥንካሬ፣ ለኃይልና ሙቀት ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡
ፈረንጆች ‹‹you are what you eat›› የሚሉት ብሂል አላቸው፤ ሰው ማጀቱን ይመስላል እንዲል የሀገሬ ሰው፡፡ ወይም ‹‹ሆድን በጎመን ቢሸነግሉት፣ ጉልበት በዳገት ይለግማል›› እንዲል- የሀገሬ ገበሬ፡፡

የአኅጉራችን ሰዎችን የሰውነት ጥንካሬ ስንመለከት ከአመጋገባቸው ይትባህልና ልማድ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ለዚህ ነው የእግር ኳስ ጨዋታ ሜዳ ላይ ንክች ሲያደርጉን ፍንግል የምንለው፡፡ ሁሉ አዝዕርት እያለን የአመጋገብ ባህላችንን ማስተካከል ባለመቻላችን ደቃቆች ሆነናል፡፡ በጣም ምግብ መራጭ ህዝቦች ነን፡፡ ይህ ጎድቶናል፡፡

ገንፎን በሀገራችን ልዩ ልዩ አካባቢዎች ለምሳሌ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል፣ ደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ ጎላ ብሎ በአመጋገብ ልማዳቸው ውስጥ ቢኖርም፣ በአብዛኛው የሀገራችን ክፍል ግን የዘወትር ምግብ ከመሆን ይልቅ የልዩ ልዩ ማኅበራዊ ኹነቶች፣ የበዓላት እና አልፎ- አልፎ በምግብ ጠረጴዛ ላይ የሚቀርብ ምግብ ሆኗል፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ባሉ ማኅበረሰቦች አካባቢ የሚዘጋጀው የቡላ ገንፎ እጅግ ከፍተኛ ሙቀትና ኃይል ከመስጠቱ ባሻገር፣ ከአራስነት ለመጥናት እንደ መድኃኒትነት ሁሉ ያገለግላል፡፡ ይህን ባህል ወደ ሰሜኑም፣ ምስራቁም የኢትዮጵያ ክፍል ማዳረስ ይኖርብናል፡፡

ላጤዎችም ቢሆኑ፣ ብዙ ጊዜ ገንፎን ለምግብነት ሲመርጡት አይስተዋልም፡፡ እንደውም አንዳንዱ ‹‹እኔ አራስ ነኝ እንዴ-ገንፎ የምመገበው›› ሲልም ይስተዋላል፡፡
በእርግጥ አማራጭ የአመጋገብ ሥርዓት እንዳንፈልግ ከሚያደርጉን ምክንያቶች አንዱ የምግብ ፍጆታ አቅርቦታችን፣ ሲበስል የሚፈጀው ጊዜ እና የአዘገጃጀቱ ሂደቶች ውስብስብነት ናቸው፡፡

ሆኖም፣ ገንፎ ማዘጋጀት በጣም ቀላል ሥራ ነው፡፡
ግዴላቸሁም ገንፎ አዘገጃጀትን አሁን አብረን እንሞክረውማ?! በደንብ ትወዱታላቸሁ፡፡ መሞክር ማንን ገደለ፡፡ ለዚህ ክረምት ደግሞ ኃይልና ሙቀትንም እንድናገኝ ተመራጭ ምግብ- ገንፎ ነው፡፡

ገንፎ ለመሥራት ምን ያስፈልገናል?

1 የገንፎ እህል (ዱቄት)
2 ጨው
3 ትንሽ ቅቤ ወይም ዘይት
4 በርበሬ ወይም ሚጥሚጣ (እንደ ምርጫችን)

አዘገጃጀቱ

ጀመሪያ በድስት ውሃ እንጥዳና ልክ መፍላት ሲጀመር ትንሽ ጨው መጨመር፤
ውሃው ሲፈላ፣ ትንሽ በብርጭቆ ውሃ ቀንሰን እናስቀምጣለን፡፡
ቀጥሎ ሥራችን የሚሆነው ደግሞ ቀስ እያልን ዱቄቱን መጨመር እና በማማሲያ የጨመርነውን የገንፎ ዱቄት እንዳይጓጉልብን ተጠንቅቀን ማሸት- ማሸት-ማሸት ይሆናል፡፡

እንዳያርብንም የእስቶቭ መጠን መቀነስ ወይም ከእሳቱ ላይ እያወረድን በመድንብ ገንፎውን ማሸት ይኖርብናል፡፡

ቀጥሎስ፣ የገንፎውን መሐሉን ጎድጎድ አድርገን በብርጭቆ የቀነስነውን የፈላውን ውሃ ጠብ እናርግና ከድነን እንዲበስል እናደርገዋለን፡፡

እንደገና ደግመን እናሸውና ትንሽ ውሃ ጠብ እናደርጋለን፤ አሁንም ደግመን እንዲበስል እንከድነዋል፡፡

በነገራችን ላይ እንደበሰለ በሽታው ብቻ ማወቅ ይቻላል፡፡ እንዴት ካላችሁ እህል እህል የሚል ከሆነ ገና ነው ማለት ስለሆነ፣ ልክ እንደቅድሙ ውሃ ጠብ አድረግን- እንከድነዋለን፡፡ አለበለዚያም በማንኪያ ቀምሰን ማረጋገጥ እንችላለን፡
አሁን ገንፏችን በስሏል፤ ከዚህ በኋላ ለመመገብ ሰሃናችን ቅቤ ወይም ዘይት ዙያውን በመቀባት እናዘጋጅና የሰራነውን ገንፎ ወደ ሰሃናችን እንገለብጠዋለን፡፡

የገለበጥነውን ገንፎ በክብ ቅርፅ በማዘጋጀት መሐሉን ቀስ ብለን በማንኪያ እንከፍተውና ቅቤ ወይም ዘይት በማድረግ ቀጥሎ ደግሞ በርበሬ በመጨመር ማዋሃድ እና ትኩስ ትኩሱን- መመገብ፡፡

አቦ ደስ የሚል ምግብ ይሁንላቸሁ፡፡ ግን ወዳጅዎን መጋበዝዎትን እንዳይረሱ!!!

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com