ለሚመለከተው ሁሉ!

Views: 741

ይህቺን ትንሽ ታሪካዊ ማስታወሻ ያገኘኋት በአጋጣሚ ወመዘከር ቤተመጻሕፍት ውስጥ ሠነዶች ሳገላብጥ ነው፤ እናም ድንገት ይህ ማስታወሻ ቀልቤን ሳበው፡፡ ወቅቱም የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ ማለት በሚያስችል ሁኔታ ስለ ዓባይ ግድብ ከፍተኛ ቅስቀሳና የብሄራዊ አንድነት ስሜት ቀስቅሶ ስለነበር፣ የኔም ስሜት በተመሳሳይ ሀገራዊ ግለት ላይ ነበር፡፡

በመሆኑም፣ ጽሑፉን ማውጣት (መዋስ) የማይቻል ስለነበር፣ የህዳሴ ግድብ አስተባባሪ ጽ/ቤት የኮሙኒኬሽን ዴስክ ኃላፊዎችን ጽሑፉን ተመልክተው ለህዝብ ጆሮና አይን እንዲያበቁት ተማጸንኩ፡፡

ተማጽኖዬ፣ ጀግኖች አባቶቻችን ምን ያህል ለህዝባቸውና ለሀገራቸው ሌት ተቀን እንደሚጨነቁና እንደሚያስቡ ለማሳየት ነበር፡፡ ሆኖም፣ ባልገባኝ ምክንያት የህዳሴ ግድብ አስተባባሪ ኮሚቴ ኃላፊዎች ጉዳዩ በይፋ እንዲታወቅ እንደማይፈልጉ ተረዳሁ፡፡ ይህን ባወቅኩ ጊዜ የተሰማኝ ሀዘንና ቅሬታ አሁንም አላባራ!!! ይሁንና ጊዜውን ጠብቆ የእኚህ የብሄራዊ ጀግናችን ሃሳብና ፍላጎት ይኸው ዛሬ ወቅቱን ጠብቆ ይፋ ወጥቷል፡፡ እነሆ ተመልከቱት፡፡
(ኩራባቸው ሸዋረጋ)

ለክቡር ደጃዝማች ከበደ ተሰማ
የአዲስ አበባና የአውራጃዋ ገዥ
አዲስ አበባ

ክቡር ሆይ

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የወዳጅ መንግሥት አገሮችን ጐብኝተው ከአሜሪካን እስቲመለሱ አንድ መሰናዶ አሰናድቶ መጠበቅ ስለሚገባን አንድ ሀሳብ ለክብርነትዎ አቅርቤ የነበረውን አሁንም ደግሜ ማስታወሻ ላቀርብልዎ ግድ ሆነብኝ፡፡

ክቡር ከንቲባ ሆይ
ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለኢትዮጵያ አገራቸውና ህዝባቸው ዙሪያውን በማይናወጽ የወዳጆች ህንጻ መስርተው እኛን የሚጎዳ ነገር እንዳይደርስብን ሌት ከቀን እንቅልፍ አጥተው ስለሚጥሩ ምን ወሮታ ልናቀርብላቸውና ልናደርግላቸው እንችል ይሆን?

በዘመናቸው ብቻ የታቀደ ሀሳብና ከሀሳባቸውም አንዳንድ ነገሮች እንርዳ እንስራ ከማለት በስተቀር የሚጠቅም ስለሌለ፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ሆነን ለገንዘባችን ሳንሳሳ፣ ገንዘብ የሌለው በእርስቱ እርዳታ እያደረግን ከፍ ያለ ገንዘብ እንሰበስብና የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚጠቀምበት ሥራ እናቋቁም፡፡

ዘንድሮ ከአባ ሳሙኤል የሚነሳው ኤሌክትሪክ ለከተማው ብቻ ማገልገል ተስኖት እንዱስትሪዎች ወፍጮዎች በመቆማቸው የከተማው ሕዝብ ከመቸገሩም በላይ ማተሚያ ቤቶችም ሥራቸውን አቋርጠዋል፡፡

እንግዲህ ባለ እንዱስትሪዎች፤ ከፍ ያለ ታክስ ከፍለው ፈቃድ ተቀብለው የሚሰሩ ስለሆነ ኤሌክትሪክ ባለማግኘታችን ያልሰራንበት ጊዜ ተቀናሽ ይሁንልን ማለታችው ስለማይቀር፤ በእውነተኛው አስተያየት የተገመተ እንደሆነ ያልሰራበትን ጊዜ መቀነስ ስለሚገባ የማዘጋጀ ቤት ገቢ እባጀቱ የማይደርስ ይሆናል፡፡

መንግሥትም ኤሌክትሪክ በተቸገርክበት ጊዜ ውስጥ ያልሰራህበትን ምረንሀልም ቢባል ተመልሶ ጉዳቱ ያው ነው፡፡

ነገር ግን የኮኔለ ጽሕፈት ቤት በውሀ ችግር ኤሌክትሪኩ አቅም የሚያጣ መሆኑን ከዛሬ አራት አምስት ወር በፊት ለሕዝብ ቢያስታውቅ ኖሮ፣ ስለጥንቃቄ እህሉ ተፈጭቶ ዱቄቱን ያስቀምጥ ነበር፡፡

ነገር ግን በድንገት ማስታወቂያ በማውጣቱና ወዲያውም የማዘጋጃ ቤት ገቢ ከዚህ በላይ በተገለጸው ምክንያት ገቢው ሲጓደል በኮኔል በኩል ምንም የሚጐዳው ነገር የለም፤ የሚያስጠይቀውም ምክንያት ያለ አይመስለኝም፡፡

የኤሌክትሪክ ግልጋሎት አሁን ያለው እስከዚህ ሆኖ ሲታይ የእስከ ማእዜኑን ሀሳብ መወጠን ያስፈልጋል፡፡

ዛሬ የሰው ልጅ ጥበብ አለቅጥ በብዙ በተስፋፋበት ዘመን ያለጥበብም ቢሆን ዶማና ማረሻችንን ይዘን በጉልበት ብንጥርበት የአባይን ጅረት ለመገደብ የሚያውከን አይሆንም፡፡

የአባይንም ጅረት ለመመለስና እስራ ላይ ለማዋል ቁርጠኛ ሀሳብና ተስፋ እናድርግ የአባይ ጅረት እንደምን ሆኖ ከዚያ ከጅረቱ ወደ ላይ ሽቅብ ወጥቶ ሥራ ሊሰራ እንዳምን ይቻላል በማለት ልባችንን አናሰንፈው፤ ይቻላል እንበለው እንጂ፡፡

የአባይን ጅረት ገድቦ እስራ ላይ ለማዋል ከፍ ባለ ገንዘብ መሀንዲስ ማስመርመርና የአሰራሩን ሁኔታ በካርታና ከፍ ባለ መጽሐፍ የሥራውን ዝርዝር ያስፈልጋል፡፡

እንግዲህ በሙሉ ሀሳባችን የአባይን ጅረት መልሰን እስራ ላይ እንዲውል ስንነሳ ግብጸች ምንም የማይደሰቱበትም ቢሆን ውሀው ሥራውን ሰርቶ ተመልሶ ወደ አለበት መመለስ ያለበት ስለሆነ፣ በጣምም የሚጎዱ አይመስልም፡፡

የሆነ ሆኖ የአባይን ጅረት መልሶ ለኤሌክትሪክ እርሻ ጉዳይ እስራ ላይ እንዲውል ስናስብ በሚልያርድ የሚቆጠር ገንዘብ ማስፈለጉ እርግጥ ነው፡፡

ስለዚህ ለዚህ ጉዳይ ከአቅማችን በላይ የሆነ ገንዘብ እናዋጣ፤ ጥሬ ገንዘብ የሌለው ስለ አባይ ውሀ ግድብ እርስት ይሰጥ፡፡ እርስቱም ለዚህ ሥራ ለተመደቡት ቦርዶች አስተዳዳሪ ሾሞለት ጥቅሙን እየተቀበለ ለዚሁ ተብሎ ለታዘዘው ግምጃ ቤት ያስረክብ፡፡

ለአባይና ለጊቤ ጅረቶች ሥራ ቦርዱ ተመድቦ ኘሬዚዳንትና አባሎች ተመርጠው፣ የተለየም መሥሪያ ቤት ተከፍቶ ስራው በደንብ ሲቋቋም የፍል ውሀ ገቢ የኛም በከተማው ውስጥ የገዳም ቦታ ነው እየተባለ ሳይቀየስና የቦታው ስፋትና ጥበት ሳይታወቅ ቤተ ክህነት ይገባ የነበረው የቦታ ግብር ገቢ ወደዚሁ ሥራ እንዲውል፡፡ በኛም ስለ አባይ ግድብ ሥራ የገንዘቡ ልክ ይበቃል እስከተባለበት ጊዜ ድረስ አዲስ ቤተ ክርስቲያን መቆሙ እንዲታገድ ይህን ከዚህ በላይ የተገለጸው የሚመስል ሀሳብ ከኮሚቴው እየቀረበ ይገባል አይገባምን ይሚወሰኑ ኮሚሳዮኖች እንዲሁኑ ማለት ነው፡፡

ስለ አባይ ግድብ ገንዘብ የተቸገረ መሬት መርዳት ይችላል ያልንበት ምክንያት የአባይ ወንዝ ተገድቦ ሥራ በሚይዝበት ጊዜ የብዙ ሰው እርስት ማስነሳት የሚያስፈልግ ሳይሆን ስለማይቀር ማደራጀት ስለአለበት ነው፡፡

ስለዚህ ስለ አባይ ወንዝ ግድብ ምክንያት እርዳታ የተደረገው መሬት፣ እስከዚያው የአላባው ገንዘብ ወደ ራሱ ግምጃ ቤት ገቢ መሆን አለበት፡፡

የአባይም ባንክ ስራው የተስፋፋ አንድ ደንበኛ መሥሪያ ቤት እንዲኖረው ያስፈልጋል፡፡ በ%4 ጠቅላይ ግዛቶች የገንዘብ ስብሳቢ ኮሚቴ መምረጥና ቅርንጫፎች እንዲሆኑት፡፡

የአዲስ አበባው ግን ዋና ስራ አስኪያጆች ከግርማዊነታቸው ልጆች ውስጥ እንምረጥ አባሎችም ከሴቶቹም እንምረጥና ሶስት ቦርድ ይሁን አንዱ በወንድ አንዱ በሴቶች አንዱ በቤተ ክህነት ክፍል አድርገን እርዳታ እንጀምር፡፡

ሶስቱ ገንዘብ ሰብሳቢዎች በሶስት ወገን በየጠቅላይ ግዛቱ ለየብቻቸው የገንዘብ ስብሰባውን ሥራ ያቋቁሙ ሥራም ሲባል ባንድ ጊዜ ገንዘብ ስብሰባንም ሥራውን አንድነት ለመጀመር ባለመቻሉ መጀመሪያ የገንዘቡ አሰባሰብ ስራ ይጀመር ቀጥሎም የሚገደብበትን አስፈላጊ የሆነውን ስፍራ በአዋቂ ተጠንቶ መነሻው ይታወቅ፡፡ ቀጥሎም ይህ ፈሳሺ ውሀ ተችሎ ለማገልገል የበቃ እንደሆነ የቱን የቱን መሬት ማስነሳት ወይንም ስንት ጋሻ መሬቶች በግራና በቀኝ ያስፈልገን እንደሆነ በአዋቂ ተመርምሮ እንዲታወቅ ስለሚያስፈልግ ነው፡፡

በኤሌክትሪኩም በኩል አስፈላጊው ድርጅቶች አስቀድሞ ዝርዝር ጉዳያቸውንና የሚፈጁትንም መሣሪያዎች ማሳሰብ አስፈላጊ ይሆናሉ፡፡

ኤሌክትሪኩ ከሚነሳበት አንስቶ እስከ ከተማው ድረስ በኤሌትሪኩ ምሰሶ ግራና ቀኝ የተሰናዳ የመኪና መንገድ እንደሚያስፈልገው ሆኖ መስራት እንደሚገባው ሁሉ እንዲታሰብበት ነው፡፡

በጠቅላላው ስለ አባይ ወንዝ ሥራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ኘሬዚዳንትና አባል በተመረጠ ጊዜ ለዚሁ ሥራ ማቋቋሚያ ከሸዋ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ አንድ ጋሻ ለም እርስት ከግል እርስቴ እረዳለሁ፡፡ ሁለተኛም ሁለት መቶ ብር አለቀ ድረስ በወር በወሩ ከደሞዜ ላይ አምስት አምስት ብር እየከፈልኩ የምጨርሰው ሁለት መቶ ብር እረዳለሁ፡፡

ክቡር ሆይ፤
ይህ ነገር በክብርነትዎ በኩል ቢከፈት ፈር እንደሚወጣው አምናለሁ ምክንያቱም በ’7 ዓ.ም ስለ ግርማዊነታቸው ልደት በዓል የመጀመሪያ ግብዣ ሲያደርጉልን በዳስ ውስጥ ከመብሉም ከመጠጡም ይልቅ የነበረውን ጨዋታ ዛሬ ትዝ ይለኛል፡፡ በዓመቱ የተሰናዳ አዳራሽ አሰርተው ክብርነትዎ የመሰረቱት ግብም ሳታቋርጥዎ ምንም ክቡርነትዎ እንደነበሩበት ጊዜ ሹማምንቶችዎን በዙሪያው አቁመውን እንደተመልካች አስመስለው በግብዣው እንደሚያስደስቱን ጊዜ አይሁን እንጂ፡፡

አዳራሹ የሚያስገኘው ጥቅም ኪሳራውን በአጠፌታ የመለሰ ሆኖአል፡፡ ስለዚህ በዚህ ነገር ክቡርነትዎ ከባረኩት የተባረከ ሆኖ እስራ ላይ ውሎ ስራውና ሀሳቡ ተጀምሮ ለማየት እንዲያበቃኝ ልዑል እግዚአብሔር ቸር ፈቃዱ ይሁንልን ስል ይህን ማስታወሻ በፍርሃት ለክብርነትዎ አቀርባለሁ፡፡ ሰኔ % (6 ዓ.ም ታዛዥዎ

ታፊሰ ታቼ

Comments: 1

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

  1. ታፈሰ ታቸ ማን ናቸው?
    ዋናው ነገር ግን ድንቅ ህልም የነበራቸው ኢትዮዽያዉያን እንደነበሩ ሳይ በወገን ላይ ያለኝ ኩራት ከንቱ አለመሆኑን እረዳለሁ: ዛሬም ነገም እንዲህ ያሉ ብርቅ ሰወች እንዳሉና እንደሚኖሩ ሳስብ ልቤ በደስታ ይፈነድቃል

This site is protected by wp-copyrightpro.com