ዜና

ዘምዘም ምን ይዞ እየመጣ ይሆን?

Views: 1717

በእስላማዊ መርህ፣ የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ከስምንት ዓመታት በፊት ካፒታል በማሰባሰብ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት እያደረገ፣ በመጨረሻ ላይ የታገደው ዘምዘም ባንክ የምሥረታ ሒደቱን በአዲስ መልክ ለማስቀጠል ዝግጅት መጀመሩ ታውቋል፡፡ የኢትዮ ኦንላይን ጸሐፊ እስላማዊ ባንክ አሰራር እና መጪው ጊዜ በኢትዮጵያ ከባንክ አሰራር ያለውን ሁኔታ በተመለከተ የሚከተለውን አሰናድቷል፡፡

ከኢትዮጵያ ብሐራዊ ባንክ፣ ባንክ ሱፐርቪዥን አገልግሎት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ማለት በእስልምና የፋይናንስ መርሆዎች መሠረት የባንክ አገልግሎቶችን ማለትም ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰብ፣ ብድር መስጠትን እና ሌሎች አገልግሎቶችን ከወለድ ነፃ በሆነ መልኩ በትርፍ/ኪሳራ መጋራት ላይ ተመስርቶ መስጠት ነው፡፡

የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ምንም ዓይነት ወለድ መክፈል ሆነ በመቀበል ላይ ያልተመሰረተ የፋይናንስ አገልግሎት ሲሆን፣ በቅድሚያ በሚደረግ የውል ስምምነት መሠረት ከደንበኛው ጋር የትርፍ ክፍፍል የሚደረግበት፣ ኪሳራ ሲከሰት ደግሞ፣ ባንኩ እና ደንበኛው ባዋጡት የገንዘብ ልክ ያጋጠመን ኪሳራ የሚጋሩበት የባንክ አሰራር መሆኑን ከኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

ይህ የባንክ አገልግሎት በሸሪዓ መርህ መሠረት ባንኩ እና ደንበኛው በተፈቀዱ ሥራዎች ላይ ብቻ የሚሳተፉበት አማራጭ የባንክ አገልግሎት ነው፡፡ ከወለድ በተጨማሪ በኃይማኖቱ የተወገዙ እንደ ወሲብ፣ አልኮል መጠጥ ያሉ ንግዶችም በፋይናንስ አገልግሎቱ የታቀፉ አይደሉም፡፡

አሁን አሁን፣ የወለድ አልባ ባንክ አገልግሎትን ተጠቃሚ ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ እና ይህን ፍላጎት ማሟላት አስፈላጊ በመሆኑ፣ አገልግሎቱን በሚፈለገው መልኩ ተደራሽ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎትም ለኢኮኖሚ እድገት የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡

አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ በመላው አለም አገልግሎቱን የሚሰጡ ተቋማት አጠቃላይ ሀብት ከ230 ቢሊየን ዶላር በላይ መድረሱ ለዚህ እንደ ማሳያ ነው፡፡ ከወለድ አልባ ባንክ አገልግሎት መርሆ የሚሰጡ አገልግሎቶች በተለመደው የባንክ አገልግሎት የሚሰጡትን ማለትም ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰብ፣ ብድር መስጠትን፣ የሃዋላ አገልግሎት እና ዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎን ያጠቃልላሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ አገልግሎቶች ከወለድ ነፃ ሆነው፣ በትርፍ/ኪሳራ መጋራት ወይም በአገልግሎት ክፍያ መሠረት የሚሰጡ ናቸው፡፡

ዘምዘም ባንክን በዋና አደራጅነትና ሊቀመንበርነት የሚመሩት ዶ/ር ናስር ዲኖ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፣ ቀድሞም ያላግባብ የታገደው የዘምዝም ባንክ ምሥረታ አሁን በብሔራዊ ባንክ አዎንታዊ ምላሽ በማግኘት የምሥረታ ሒደቱን ለማስቀጠል መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

የዘምዘም ባንክን ምሥረታ በድጋሚ ለማቀላጠፍ ላለፉት አሥር ወራት ጉዳዩን በማንቀሳቀስና የተከለከለበትን ምክንያት በማስመርመር በመጨረሻ መግባባት ላይ መደረሱን ያስረዱት ሊቀመንበሩ፣ በሳምንቱ መጀመርያ ላይ አደራጆቹ ከአዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶ/ር ይናገር ደሴ ጋር ያደረጉት ውይይት ስኬታማ ነበር ብለዋል፡፡

በቅርቡ በሚሊኒየም አዳራሽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ (እስላማዊ ከወለድ ነፃ ባንክ ማቋቋም እንደሚቻል መናገራቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ወደ አክሲዮን ሽያጭ መግባት የሚያስችላቸውን ደብዳቤ እየጠበቁ መሆናቸውንም ከአደራጁ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በምሥረታ ላይ የነበረው የዘምዘም ባንክ ቢሮ መከፈቱን የጠቆሙት ዶ/ር ናስር፣ ‹‹አሁን ላለንበት ደረጃ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ብሔራዊ ባንክ ያደረጉት ዕገዛ ከፍተኛ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ ውሳኔ በፊት ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለብሔራዊ ባንክ ገዥ ተከታታይ ደብዳቤዎች በመጻፍ፣ በምሥረታ ላይ የነበረው ዘምዘም ባንክ የታገደበት ምክንያት አግባብ አለመሆኑን የሚገልጹ መረጃዎችን ሲያቀርቡ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ያቀረቡዋቸው መረጃዎች ለወራት ተመርምረው ክልከላው ተገቢ አለመሆኑን መገንዘብ ተችሏል ብለዋል፡፡

ዘምዘም ባንክ 500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል በሟሟላት እንደሚቋቋም ከብሔራዊ ባንክ እንደተፈቀደ ወደ አክሲዮን ሽያጭ እንደሚገባም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በኢትዮጵያ እንዲጀመር የዘምዘም ባንክ አደራጆች ብዙ መድከማቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ራሱን ችሎ ባንክ ለማቋቋም ባይችሉም ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በባንኮች እንዲሠራበት የሚያስችለውን መመርያ እንዲወጣ አስደርገዋል፡፡ ይህንን ክንውናቸውን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ በጻፉት ደብዳቤ፣ ‹‹ልፋታችን ፍሬ አፍርቶ እ.ኤ.አ. በ2008 የፀደቀው የባንክ ቢዝነስ አዋጅ የወለድ ነፃ የባንክ አሠራርን ዕውቅና የሰጠ ሆኖ ወጥቷል፤›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡

አዋጁ ከፀደቀ በኋላ ዘምዘም ባንክን ዕውን ለማድረግ ተጨማሪ ሦስት ዓመታትን በፈጀ ያላሰለሰ ጥረት፣ ከ137 ሚሊዮን ብር በላይ የተከፈለ ካፒታልና 337 ሚሊዮን ብር የተፈረመ ካፒታል ማስመዝገብ ችሎ የነበረ መሆኑን አደራጆቹ ያወሳሉ፡፡ በወቅቱ ዘምዘም ባንክ 6,800 የአክሲዮን ባለድርሻዎች የነበሩት ሲሆን፣ ከእነዚህ ባለአክሲዮኖች ውስጥ 83 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛውን የአክሲዮን ድርሻ የገዙት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች መሆናቸውን፣ 60 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ሴቶች እንደነበሩ አደራጆቹ ይገልጻሉ፡፡

ዘምዘም ባንክ መሥራች ጉባዔውን በማድረግ የቦርድ አባላቱን እ.ኤ.አ. በ2011 መርጦ ነበር፡፡ ይሁንና ብሔራዊ ባንክ አነስተኛ የተከፈለ ካፒታል መጠን ከ75 ሚሊዮን ወደ 500 ሚሊዮን ብር ከፍ በማድረግ፣ በተጨማሪም ዘምዘም ባንክ ሲንቀሳቀስበት ከነበረው ዓላማ ውጪ በወለድም ጭምር እንዲሠራ የሚያስገድድ መመርያ በማውጣት፣ እንቅስቃሴያቸውን እንዲያቋርጡ እንዳደረገ ይታወሳል፡፡

በወቅቱ የዘምዘም ባንክ የምሥረታ ሒደት እንዲቋረጥ የተደረገበትን ምክንያት በተመለከተ ለብሔራዊ ባንክ ገዥ ባስገቡት ደብዳቤ፣ ‹‹ይህ የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ አግባብ እንዳልሆነ ለማስረዳት የብሔራዊ ባንክ ባለሥልጣናትን ጨምሮ ብዙ የመንግሥት አካላትን ለማነጋገር የቻልን ቢሆንም፣ ይህን የፖለቲካ ውሳኔ ማስቀልበስ ሳይቻለን ቀርቷል፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ ንግድ ባንኮች የወለድ አልባ ባንክ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸውን ፍቃድ ለማግኘት እና አገልግሎቱን ለመስጠት የሚችሉት፣ በባንክ ሥራ አዋጅ ቁጥር 592/2000 አንቀጽ 22(2) የተፈቀደ ከመሆኑም በላይ፣ ይህንኑ ለማስፈጸም መመሪያ ቁጥር SBB/51/2011 ወጥቷል፡፡

ከዚህም ባሻገር ንግድ ባንኮች በኢንቨስትመንት መመሪያ ቁጥር SBB/12/1996 የተቀመጠውን ገደብ ጠብቀው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህም መመሪያ የወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የመከለሱ ሥራ በሂደት ላይ ይገኛል፡፡

በዚህ መሠረት፣ ባንኮቹ አገልግሎቱን ለመስጠት ማሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች በግልጽ የተቀመጡ ሲሆን፣ ባንኮች “ወለድ”ን  አስመልክቶ ከወጣው የብሔራዊ ባንክ መመሪያ ቁጥር በስተቀር ሌሎችን መመሪያዎች ተከትለው አገልግሎት መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ከመደበኛው የባንክ አገልግሎት በተጎዳኝ በባንክ ቅርንጫፍ ነገር ግን በተለየ መስኮት የሚሰጥ ነው፡፡ ባንኮቹ አገልግሎቱን በእስልምና የፋይናንስ መርሆዎች እና የአደጋ ተጋላጭነት በሚቀንስ መልኩ ለመስጠት የሚያስችል የውስጥ አደረጃጀት እና የአሰራር ሥርአት መፍጠር ይገባቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎትን ከአምስት አመት በፊት በመጀመር ንግድ ባንክ እና ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ቀዳሚ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ ባንኮች ወለድ አልባ አገልግሎትን በመስጠት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ አሁን ደግሞ ሙሉ በሙሉ የወለድ አልባ ባንክ አገልግሎትን ለመስጠት ብቻ መሰረት አድርጎ ሥራ የሚጀምረው ዘምዘም ባንክ እየመጣ ይገኛል፡፡

እስካሁን ከሚታወቀው የባንክ አሰራር በተለየ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ የባንክ አገልግሎት፣ የአገሪቱ የባንክ ኢንደስትሪ ውስጥ አዲስ ነገር ይፈጥራል የሚሉ ወገኖች፣ ባብዛኛው ሃይማታዊ ፍልስፍናን የሚያንጸባርቁ አሰራሮችን የሚከተል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ የተለየ አስተያየት የሚሰጥ ቢሆንም የአገልግሎቱ መጀመር የባንክ ተጠቃሚዎችን ቁጥር እንዲጨምር እና ወደ ባንክ የሚመጣውም ገንዘብ እንዲበራከት ያግዛል ይላሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፣ የዚህ አገልግሎት መጀመር ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያለው እና ለአማራጭ የባንክ አገልግሎት በርም የከፈተ ነው፡፡ በሚከተሉት እምነት ምክንያት ወደ ባንኮች የወለድ አልባ አገልግሎት መቅረብ ያልቻሉ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የባንክ አገልግሎት እንዲያገኙ እና ባንክ ያላወቀውን ከፍተኛ ገንዘብም ወደ ባንክ እንዲመጣ በማድረግ፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ግልጋሎት እንዲሰጥ ያስችላል፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የአገልግሎቱ መጀመር ጠቃሚ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በሌሎች አገሮችም ኃይማታዊ መንፈስ እንዳይኖረው ተደርጎ የሚሰራበት ነው የሚሉ አሉ፡፡ ከዚህ የተለየ ሃሳብ ያላቸው ሌሎች ደግሞ ወለድ አልባ አገልግሎት በባንክ ኢንደስትሪው ውስጥ አዲስ የሚባል አሰራርን ከመፍጠር በቀር የተለየ ነገር ያመጣል ብለው አያምኑም፡፡

አንዳንዶች ግን የተለየ አቅጣጫ ሊይዝ ይችላል ብለው ስጋታቸውን የሚገልጹ ብዙ ናቸው፡፡ ሆኖም አገልግሎቱ ግን አሁን ያለውን የባንኮች ውድድር ወደ ሌላ አቅጣጫ ይወስደዋል የሚሉ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት በዘር እና በሃይማት ተቧድነው የሚሰሩ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ መደረግ አለበት በማለት ይመክራሉ፡፡

ድሮም ቢሆን ለወለድ አልባ አገልግሎት ህግ ሳይወጣም በፊት ገንዘባቸውን ያለወለድ የሚያስቀምጡ ብዙ ዜጎች እንዳሉ የሚጠቁሙት አስተያየት ሰጪዎች፣ እንዲህ አይነት ልምድ ያላቸው አስቀማጮች፣ አገልግሎቱን ወደሚሰጠው ባንክ ብቻ ሊያጋድሉ ይችላሉ፤ ይህም ደግሞ የባንክ ኢንደስትሪው ተወዳዳሪነት ላይ ተጽዕኖ ያሳርፋል ይላሉ፡፡

ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ብቻ ተከትሎ አያገለግልም፤ አገልግሎቱ የማንኛውም ሃይማኖት ተከታዮች እንዲጠቀሙበት የሚያስችል ነው፡፡ መንግስት ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት የሚል ስያሜ የሰጠውም ኃይማኖታዊ አመለካከቱ እንዳይኖር ለማድረግ ነው ተብሏል፡፡

አስካሁን ሲገለግል በቆየው የባንክ አሰራር እና አገልግሎት ምቾት ያጣው ክፍል፣ አዲሱን አገልግሎት ሊጠቀም ዕድሉን የሚያገኝበት በተለየ ሁኔታ እየተመቻቸለት ነው፡፡ በሁለቱም የባንክ አገልግሎት አይነቶች መጠቀም የሚፈልግ ሰው አይጠፋም፡፡ ሊከለክለው የሚችል ነገርም እንደሌለ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ከወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት መካከል በግንባር ቀደምትነት ከሚጠሩት የፋይናንስ አገልግሎቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡ በመጀመሪያ የሚጠቀሰው ‹‹ሙራሃባ›› ሲሆን፣ የተገዛን ሸቀጥ በትርፍ መሸጥ አሰራር ነው፤ ‹‹መድራባ›› ተብሎ የሚጠራው ደግሞ፣ የካፒታል እና የጉልበት ሽርክና ውል በሚል ይታወቃል፡፡ በመቀጠል በሦስተኛነት የሚገኘው ‹‹ኢስቲስና››፣ የግንባታ ውል የሚመለከት ሲሆን፣ ‹‹ኢጃራ›› የኪራይ ውል፣ ‹‹ሙቫራክ›› ድግሞ የካፒታል እና የጉልበት ሽርክና ውል ሆኖ ባለካፒታሉ ጭምር የሚተዳደርበት እንደሆ ይጠቀሳል፡፡ ነ

ከወለድ አልባ አገልግሎት ጋር ተቀራራቢ አሠራር በኢትዮጵያ ውስጥ ቢኖርም፣ ሁለቱ የማይገናኙበት አካሄድ አላቸው፡፡ በወለድ አልባው አሠራር መሠረት ወለድ ነክ የሆኑ አገልግሎቶች ቦታ የላቸውም፡፡ “ሃራም” ተብለው የተቀመጡ የባንክ አገልግሎቶች በመኖራቸው፣ በመደበኛው እና በተለመደው የባንክ ሥራ ውስጥ አንዳንዶቹ እዚህ አይኖሩም፡፡ በወለድ አልባው ባንክ ውስጥ ሃራም ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ በወለድ ብድር መስጠት እና መቀበል አንዱ ነው፡፡ በእስላሚክ የባንክ ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ የባንክ አገልግሎቶች፣ ተፈፀሚ የሚሆኑት ባንክ ሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ወገኖች መካከል፣ በገዢ እና ሻጭ፣ በአከራይ ተከራይ መካከል የሚፈጸሙ ስምምነቶች እንዲከናወኑ በማድረግ ከዚህ ሂደት የሚገኘውን ትርፍ ተቋዳሽ እንዲሆን በማድረግ ጥቅም ያገኛል፡፡

የመጀመሪያው “ሙድራብ” የተባለው የአገልግሎት ዘርፍ ሁለት ወገኖች መካከል፣ በገዢና ሻጭ፣ በአከራይና ተከራይ መካከል የሚፈጸሙ ስምምነቶች እንዲከናወኑ በማድረግ ከዚህ ሂደት የሚገኘውን ትርፍ ተቋዳሽ እንዲሆኑ በማድረግ ጥቅም ያገኛል፡፡

“ሻረክ አል አኮድ” የተባለው ሌላኛው የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ደግሞ በኮንትራት መልክ የሚፈጸም የትብብር ሥራ ነው፡፡ በዚህ ስምምነት ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ሆኑ ወገኖች በጋራ ቀዋሚ ሀብታቸውን እና የሰው ኃይላቸውን በማቀናጀት ትርፍ ለማግኘት የሚሰሩበት ነው፡፡ ባንኩ በመሃል ሆኖ ስምምነቱን ያስፈጽማል፡፡

“ሙራባሃ” በሚባለው የወለድ አልባ ፋይናንስ አገልግሎት፣ ሸቀጦች ወይም ዕቃዎች ለገበያ የሚቀርቡበት ነው፤ ከተሸጠው ሸቀጥ የሚገኘው ትርፍ በሚገባ በግልጽ ተሰልቶ የሚቀመጥ ይሆናል፡፡ ከሽያጩ የሚገኘው ትርፍ በግልጽ ተደንግጎ ሊቀመጥ የሚችለው ከሽያጩ በመቶኛ ተቀንሶ ነው፡፡

በዚህ አገልግሎት ውስጥ ሸቀጡን በመግዛት በቅድሚያ ቃል የተገባበት ካልሆነ፣ የአገልግሎቱ ዓይነት ሙራባህ (ordinary murabaha) ይባላል፤ ይህም ማለት፣ በቅድሚያ ሸቀጡን ለመግዛት የቅድሚያ ቃል የተገባለት ሆኖ፣ ስምምነቱ የሚፈጸመው በተቋም ደረጃ ከሆነ ግን፣ የባንክ ሙረሃባ (banking murabaha) ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህም ግዢውን ለመፈጸም ትዕዛዞች በቅድሚያ ተፈፃሚ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡

የሙራባህ ፋይናንስ አገልግሎት ተዓማኒ ከሚባሉ የኮንትራት ስምምነቶች ውስጥ ዋነኛው ሲሆ፣ ግንኙነቱ መሠረት ያደረገው ግልጽነትን በተከተለ መንገድ የሚፈጽም፣ የሸቀጡ የመግዣ ዋጋ እና ወጪው በተጨማሪም የጋራ ወጪዎችን በግልጽ ያስቀመጠ ነው፡፡

“ኢጃራህ” በተባለው የፋይናንስ አገልግሎ አይነት ሥራ ላይ የሚውለው ደግሞ፣ ንብረቶች በኪራይ መልክ መያዣ የሚሆንበት ኮንትራት ሲሆን፣ በኪራይ የተያዘው ንብረት በጊዜ ገደብ የሚቀመጥ እና በቀነ ገደቡ መሰረት ተመላሽ የሚያደርግ ነው፡፡

“ኢጃራህ ሙንታሂ ቢታምሊክ” የተባለው ደግሞ፣ ኢጃራህ ከተባለው ጋር የሚመሳሰል ሲሆን፣ በኢስላሚክ የፋይናስ ተቋማት ውስጥ የሚሰራበት ነው፡፡ ይህ የአሰራር ሂደት በሊዝ መልክ የሚፈጸም ስምምነት ያለው ነው፡፡ በዚህ ስምምነት መሰረት የንብረቱ ባለቤት በኪራይ መልክ ንብረቱን ለተከራይ ቃል ተግባብተው የሚስተላልፉበት ነው፡፡

“ሳላም” (selam) ተብሎ የሚታወቀው ፋይናንስ አገልግሎት ደግሞ ለየት ያለ አሰራር ነው፡፡ ሳላም የተባለው የገንዘብ ዝውውር የሸቀጦች ግዢ የሚካሄበት ሲሆን፣ ሸቀጦቹ ለግብይት ሲቀርቡ ወዲያውኑ ክፍያ የሚፈጸምበት ነው፡፡ ይህ አሰራር ከሽያጭ አሰራር አይነት የሚመደብ ሲሆን፣ በዚህም የሸቀጡ ዋጋ፣ ስምምነት ሲፈጽም የሚከፈለው ገንዘብ እና የተሸጠው ዕቃ  የሚቀርብበት ነው፡፡ በዚህ አሰራር ሻጩ “አልሙስላም ኢላሂ” ገዢው ደግሞ “አልሙስላም” ወይም “ራብ አል ሳላም” ተብለው ይጠራሉ፡፡ ሰላም በሌላ በኩል ሳላፍ ተብሎም ይጠራል፡፡

“ፓራቤል ሳላም” የሚባለው ፋይናንስ አገልግሎት አሰራር ውስጥ ሻጭ ከዚህ በፊት ስምምነት ከፈጸመበት የሳላም ግኑኝነት ሌላ የተለየ ስምምነት ውስጥ ሲገባ ተግባራዊ የሚደረግ ነው፡፡ በዚህ ስምምነት መሰረት በሦስተኛ ወገን የተያዘውን ሸቀጥ በመጀመሪያው ስምምነት ወቅት የተደረሰበትን መግባባት ተከትሎ ሌላ አዲስ የስምምነት ግዴታዎችን ባሟላ መልኩ ለሦስተኛ ወገን የሚተላለፍበት አሰራር ነው፡፡ በዚህ አሰራር ሻጩ በውል ስምምነቱ መሰረት ግዴታውን ማሟላት ይጠበቅበታል፡፡

ሁለተኛው፣ ይህ ስምምነት “ፓራቤል ሳላም” ወይም “ሳላም ሙዋዚ” ተብሎ ይጠራል፡፡ በዚህ የስምምነት አይነት የሚጠቀሰው ምሳሌ አንድ ተቋም በአንድ ጎን የተወሰነ መጠን የጥጥ ምርት በሳላም የአሰራር መሰረት ከገበሬዎች ይገዛል፡፡ ገዢው የመጀመሪያውን ኮንትራት በመያዝ ሌላ አዲስ የሳላም ስምምነት ለማድረግ ከጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ጋር የጥጥ ምርቱን ሊያቀርብለት ውል ያስራል፡፡ አዲሱ የሳላም ስምምነት ሲፈጽም ለፋብሪካው የቀረበው የጥጥ ምርት መጠን በግዢ ከተቀበለው መጠን እና ደረጃ ጋር አመጣጥኖ ወደ ሌላኛው ወገን ማስተላለፍ ይቻለዋል፡፡

የኢስትስና ፋይናንስ አገልግሎት ደግሞ የሽያጭ ወጪ ስምምነት ሲሆን፣ የተወሰነ ዕቃን ለማምረት ወይም ለመገንባት የሚፈጸም ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ዋናው ግደታ በአምራቹ ወይም በገንቢ (ኮንትራክተር) ላይ ሆኖ ሥራው ሲጠናቀቅ ለደንበኞች የሚቀርብበት ነው፡፡

“ፓራራል ኢስቲስና” ሌላኛው የኢስቲስና አካል ሲሆን በተለይ ዘመናዊ አሰራር ተደርጎ “አል ኢስቲስና አልሙዋዝ” ተብሎ ይጠራል፡፡ አገልግሎቱ ተፈፀሚ የሚሆነው በሁለት የተለያዩ ስምምነት ላይ ተንተርሶ ነው፡፡ በመጀመሪው ስምምነት ኢስላማዊ የፋይናንስ ተቋማት የሚያንቀሳቅሱት፣ የአምራቹን፣ የገንቢውን ወይም የአቅራቢውን የአቅም ሁኔታ መሰረት አድርጎ ውል የሚታሰርበት ከመሆኑም በላይ፣ በስምምነቱ መሰረት የደንበኞችን ጥያቄ እንዲያሟላ ማድረግም ግዴታው ይሆናል፡፡

በሁለተኛው ስምምነት ተቋሙ የሚንቀሳቀሰው፣ ግዢውን የሚፈጽመውን ወገን መሰረት አድርጎ ሲሆን፣ በዚህም አምራቾች፣ ገንቢዎች ወይም አቅራቢዎች በመጀመሪያው ስምምነት ወቅት በገቡት ቃል መሰረት ስምምነታቸውን እንዲፈጽሙ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ሂደት የተገኘ ትርፍ የሚረጋገጠው በሁለቱ ውሎች መካከል ስምምነት ላይ ከተደረሰው የዋጋ መጠን መካከል የተፈጠረውን የዋጋ ልዩነት በማስላት ይሆናል፡፡

በወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡት የተለያዩ አገልግሎቶች ውስጥ ሳላም ከሚባለው በቀር ሌሎቹ ገንዘብ በቀጥታ የሚሰጥባቸው እና የሚቀርብባቸው አይደሉም፡፡ ባንኩ ለሚፈልገው ኢንቨስትመንት የሚያስፈልገውን ዕቃ ራሱ ገዝቶ የሚያስተላፍበት ወይም በጋራ የሚያስተዳድርበት ሲሆን፣ ሳላማ ግን ለእርሻ ምርት ሥራ የሚውል አገልግሎት በመሆኑ፣ ለምርት ማምረቻው ቅድሚያ ገንዘብ ተሰጥቶ በዚህ አገልግሎት የሚጠቀመው አካልም እዳውን በጥሬ ገንዘብ ሳይሆን በአይነት የሚመለስበት ነው፡፡

በወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የተለየ አመለካከት እንዳላቸው የገለጹ የኢኮኖሚ ባለሙያ፣ ያለወለድ አገልግሎት መስጠት ማለት ምንም አይነት ገቢ አይገኝበትም ማለት እንዳልሆነ ይገልጻሉ፡፡

እንደሚታወቀው፣ ባንክ ማትረፍ ያለበት ተቋም በመሆኑ፣ ትርፍ ሊያስገኙለት የሚችሉ ሥራዎችን ይከተላል፡፡ የዘምዘም ባክ መምጣት፣ እንደሚታሰበው ወደ ኢኮኖሚው ውስጥ በርካታ ገንዘብ ፈሰስ ሊያደርግ ይችላል የሚል ዕምነትን ከማጠናከሩም በላይ፣ ምንአልባት በእምነቱ ምክንያት ገንዘብ ከባንክ አልወስድም የሚለው ክፍል፣ አሁን ወለድ የሌለው የባንክ አገልግሎት በተቋም ደረጃ ሊጀመር ነው ብሎ ወደተጠቀሰው ባንክ ሊመጣ ይችላል ተብሎ ስለሚጠበቅ፣ ተጨማሪ በርካታ ገንዘብ ወደ ባንክ ይመጣል ተብሎ ሊታሰብ ይችላል፡፡

ኢስላሚክ ባንኮች በሚገኙባቸው አገሮች የሚገኙት ወለድ አልባ ባንኮች የተቋቋሙበት ዋና አላማ ኢኮኖሚያዊ ፍላጎትን እና የአቅርቦትን መርህ በመከተል ነው። በአገራችንም ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ፍላጎትን ብቻ መሰረት አድርጎ ቢቋቋም፣ ሁሉም ሰው ደጋፊ ሊሆን የማይችልበት ዕድል የጠበበ ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ እንደአለመታደል ሆኖ በአገራችን ውስጥ ከኢኮኖሚያዊ ፍላጎት በላይ ፖለቲካዊ ፍላጎት ስለሚበዛ እንዲሁም፣ በልዩነት ላይ ብዙ ስለተሰራ በሌላው ማህበረሰብ ዘንድ ጥርጣሬ እና ስጋትን ይፈጥራል በማለት ፍርሃታቸውን የሚገልጹ ወገኖች በርካቶች ናቸው፡፡

አገራችን በአሁኑ ሰዓት በዘር፣ በቋንቋ እና ልዩነት መፍጠር በሚቻሉ እሴቶች ሁሉ በስፋት ስለተሰራ አሁን ደግሞ የዚህ ባንክ መመስረት የኃይማኖት ልዩነትን እንደሚያጦዘው መገመት ቀላል ነው የሚሉ አሉ። እንደነዚህ አይነት ኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎች መከናወን ያለባቸው በተረጋጉ እና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት በሰፈነባቸው አገሮች ነው። የግጭት መንስኤዎች በሙሉ ከነመፍትሄያቸው በጥናት ተቀምመው ስለሚቀመጡና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው ብቻ እንዲጎላ ስለሚደረግ ህብረተሰቡን የሚያሰጋ ነገር የለውም። በተለይ በዚህ አገር የማክሮ ኢኮኖሚክ መናጋት የሚፈጥርበት ሁኔታም ሊከሰት እንደሚችል ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡

በመጨረሻም፣ “እስላማዊ ባንኪንግ ለሁሉም ሃይማኖት ተከታዮች ጠቃሚ ነው” በሚል ርዕስ የቀድሞ የፓርላማ አባል እና ፖለቲከኛ የሆኑት አቶ አብዱራህማን አህመዲን ባሰፈሩ ሃሳብ “ከዘምዘም ባንክ መስራቾች ጋር አብሬ ሰርቻለሁ፡፡ ሂደቱንም፣ አላማውንም አውቀዋለሁ፡፡ እስላሚክ ባንኪንግ ለእኛ ሀገር ነው እንጂ ለአብነት በጎረቤት ኬንያ እንዲሁም በእንግሊዝ ሀገርም ሳይቀር ይሰራበታል፡፡ አዲስ አይደለም ይላሉ፡፡

እንደ አቶ አብዱራህማን ገለፃ፣ “ብዙዎችን የሚያሸብራቸው “እስላሚክ” የሚለው ቃል ይመስለኛል፡፡ ከዚያ ውጪ ለየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ የሚጠቅም የባንክ አሰራር ነው፡፡ በክርስትና እምነትም አራጣ ክልክል ነው፡፡ ከእስልምና አኳያ ደግሞ አላህ በቁርዓን ካስጠነቀቃቸው ነገሮች አንዱ አራጣ በመሆኑ ሙስሊሞች አራጣን ይፈራሉ፣ ይጠነቀቃሉ፡፡ ከእስልምና መስመርም ያወጣል ባይ ናቸው፡፡

እንደ እሳቸው እምነት፣ እስላማዊ ባንክ ከሌሎች ባንኮች የሚለየው የአራጣ መንገዶችን ስለሚዘጋ ነው፡፡ ለአስቀማጮች ወለድ አይከፍልም፣ በወለድ አያበድርም፡፡ የእስላማዊ ባንክ ደንበኛ እና ባንኩ በጋራ ይሰራሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ በሌሎች ባንኮች አንድ ሰው ብድር ወስዶ በሚሰራው ስራ ቢከስርም ቢያተርፍም ኃላፊነቱ የራሱ ነው፡፡ ካተረፈ እሰየው፣ ቢከስር ለወሰደው ገንዘብ ከነወለዱ ይከፍላል፡፡ በእስላማዊ ባንክ ግን ገንዘብ አበዳሪው ባንኩ እና ተበዳሪው ትርፍንም ኪሳራንም ስለሚጋሩ ለነጋዴ ጠቃሚ ነው፡፡

እስላማዊ ባንክ ዘካን ለመሰብሰብ ያመቻል የሚሉት አቶ አብዱራህማን በጽሑፋቸው፣ እያንዳንዱ ሙስሊም ለአንድ ዓመት ከቆየ ገንዘቡ/ሀብቱ ላይ በየዓመቱ ዘካ (2.5  በመቶ) የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡ ሙስሊሞች ሀብታቸውን አስልተው ይህንን ግዴታቸውን ጊዜውን ጠብቀው ለመወጣት ይቸገራሉ፡፡ ይህ ገንዘብ በእስላማዊ ባንክ አማካይነት በአንድ ቋት ይሰበሰብና ለበጎ አድራጎት ተግባር እንዲውል ማድረግ ያስችላል፡፡ ዘምዘም ባንክ ይህንን የዘካ ገንዘብ በመሰብሰብ ሁሉም ዜጎች በነፃ የሚታከሙበት ሆስፒታል፣ ዜጎች ሁሉ የሚማሩበት ት/ቤት፣ የአረጋውያን መጦሪያ ማዕከል፣ አባት እናት የሌላቸው ህፃናት (የቲሞች) ማሳደጊያ፣… ለመስራት ነበር በማለት ያስረዳሉ፡፡

በሌላም በኩል፣ ሙስሊሞች ሌላው የሚፈሩት ገንዘባቸው በፈጣሪ በተጠሉ በዝሙት፣ በአራጣ፣ በመጠጥ፣ በሀሺሽና በቁማር፣ … ከመጡ ገንዘቦች ጋር እንዲነካካ አለመፈለጋቸው ነው፡፡ ይሄም በሌሎች እምነቶችም ጭምር የሚወደድ ተግባር አይደለም፡፡ አንዳንዶቻችሁ በግንዛቤ እጥረት ዛሬ ብታጣጥሉትም ነገ ከነገ ወዲያ እንደምትወዱት ጥርጥር የለውም ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ይህንን አገልግሎት በይፋ የፈቀዱት፣ አንደኛ በየቤቱ የተቀመጠው የሙስሊሞች ገንዘብ ወደ ስራ እንዲገባ ለማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛ አራጣን በመፍራት በሀገሪቱ ሀብት ተጠቃሚ ያልሆኑት ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ነው፡፡ አራጣን በመፍራት (ከአንዳንድ ደፋሮች በስተቀር) ብዙዎቹ ሙስሊሞች የኮንዶሚንየም ቤት ተጠቃሚ እንዳልነበሩ ስንቶቻችሁ ታውቃላችሁ? ለምሳሌ እኔ እና ቤተሰቤ አልተመዘገንብም፡፡ እስላሚክ ባንኪን ከመጣ ይህንን እድል እናገኛለን በማለት አቶ አብዱራህማን አህመዲን ጽሑፋቸውን ይቋጫሉ፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com