ዜና

“በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ለውጡን ለመቀልበስ የሚሰሩ አሉ”

Views: 285

በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች (ቃሊቲ፣ ቂሊንጦ፣ ዝዋይ፣ ሸዋሮቢት) የለውጥ ኃይል እንዳለ ሁሉ፣ ለውጡን ለመቀልበስ የሚሰራ በኢህአዴግ ሥር ያለ ኃይል መኖሩን ምንጮች ለኢትዮ ኦንላይን አስታወቁ፡፡

ሀገራዊ የፖለቲካ ለውጡን ለመቀልበስ የሚሞክሩ ኃይሎች፣ የራሳቸውንና የቡድናቸውን ዓላማ እና ፕሮግራም ለማሳከት ከፍተኛ ገንዘብ መድበው ሰዎችን በማማለል ላይ ናቸው ሲሉ የማረሚያ ቤቱ የዜና ምንጫችን ገልጸውልናል፡፡

የኢትዮ-ኦንላይን የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የዜና ምንጮች እንደተናገሩት፣ የለውጡ ተፃራሪ የኢህአዴግ ኃይሎች ለውጡን ለማደናቀፍ የሚጠቀሙበት ዘዴዎች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዓውድን ተከትለው ነው ብለዋል፡፡

የማረሚያ ቤቱ አባላት ሰሞኑን ባደረጉት ውይይት፣ በከባድ ወንጀል (በሰው ግድያ) የሕግ ተጠያቂ የሆኑ ታራሚዎች እንዲያመልጡ ሁኔታዎችን በማመቻቸትና ልማደኛ ወንጀለኞችን በመገፋፋት ማረሚያ ቤቶችን ማወክ እና በተዘዋዋሪ ማኅበረሰቡን በፍርሃት ማራድ በታቀደና የገንዘብ ምንጭ ኖሮት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በሌላም በኩል፣ በማረሚያ ቤት ውስጥ የአደንዛዥ እጽ ዝውውር እንዲኖር፣ የገንዘብ ዝውውር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲሰራጭ በማድረግ ቅጥረኛ ኹከት ፈጣሪዎችን ማበራከት፤ የታራሚ ቤተሰቦች ስለማረሚያ ቤት የተዛባ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግና ስጋት መፍጠር እንዲሁም የተለያየ ሕገወጥ ድርጊቶች እንዲበራከቱ መሥራት ዋና ዋናዎቹ የለውጥ ተፃራሪ ኃይሎች ሴራዎች ናቸው ብለዋል፡፡

በከፍተኛ ወንጀል (የሰው ሕይወት ማጥፋት) በሕግ ተጠያቂ የተደረጉ ታራሚዎች እንዲያመልጡ ሁኔታዎችን የሚያመቻቹት፣ ታራሚው ገንዘብ ለማውጣት ወደ ባንክ እንዲሄድ በማድረግና ጥበቃ በማሳሳት ማስመለጥ አንደኛው ዘዴያቸው ሲሆን፤ ታራሚዎች ኹከት እንዲፈጥሩ ከአቅም በላይ ማበሳጨት፤ በለውጡ አማካኝነት ለታራሚዎች እየተከበረ ያለውን ሰብዓዊ መብት መጣስና ምሬት መፍጠር የሚሉ ነጥቦች በውይይቱ ላይ ጎልቶ መነሳቱን ተናግረዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com