ለኤች አይ ቪ/ኤድስ ተጨማሪ ዕፀ-መድኃኒት (ክፍል አንድ)

Views: 756
 1. መነሻ፡-

በኤች አይ ቪ/ኤድስ የተጎዳ ሰው፣ የሰውነቱ የበሽታ የመከላከል አቅም ይቀንሳል፤ በተለያዩ የበሽታ ዓይነቶች በቀላሉ ይጎዳል፡፡ በዚህ ዘመን የበሽታውን ጫና የሚቀንሱ ዘመናዊ መደበኛ መድኃኒቶች አሉ፡፡ ይህ መልካም ነው፡፡ ደግሞ በጥንቃቄ ተጨማሪ ዕፀ መድኃኒት (የተፈጥሮ መድኃኒት) መውሰድ እጅግ ይረዳል፡፡ በሌሎች በሰለጠኑት አገራት መደበኛው ሕክምና እራሱ ተጨማሪ ዕፀ መድኃኒት (በፋብሪካ ደረጃ የተመረቱትን)፤ እንዴት እንደሚወሰዱ ምክር ይሰጣሉ፡፡ በኛ አገር ይህ ስለሌለ በተቻለ መጠን ንቁ ጥንቃቄ አድርጎ እራስን መረዳት ነው፡፡

 1. የአጠቃቀም መመሪያ:-

1ኛ/ እዚህ ላይ የተነገረም ሆነ ሌሎች የተፈጥሮ መድኃኒትን (ዕፀ መድኃኒት) ስትጠቀሙ፤ በመደበኛው ሕክምና የሚደረገው ምርመራ፣ ክትትል እና መድኃኒት በምንም ምክንያት አይቋረጥም፡፡ የተነገረው ምክር ዋናውን ሕክምና ለመደገፍ ነው፡፡

2ኛ፣ የተነገሩት ድጋፍ ሰጪ ዕፀ መድኃኒት፤ ምግብ ወይም መጠጥ በማንኛውም አግባብ  የሚወሰዱበት የጊዜ ወሰን፣

 • በቀን ሁለት ጊዜ፣
 • በተከታታይ በየቀኑ፣
 • በተከታታይ በየሁለት ቀኑ፣
 • በሳምንት ሁለት ጊዜ፣
 • በየሳምንቱ፣
 • በወር ሁለት ጊዜ ወይም
 • በየወሩ አንድ ጊዜ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

የሚወሰዱበት መጠን፣

 • ለአዋቂ ሰዎች የተባለውን ያህል ቢሆን፣ ለህፃናት በግማሽ ያንሳል
 • ለእርጉዝ እናቶች የሚከለከሉትን አለመውሰድ ነው፡፡

የአወሳሰድ ጊዜ፡-

 • ጧት በባዶ ሆድ ቢሆን፣ (ከለሊት ማለዳ 11 ሰዓት እስከ ጧት 1 ሰዓት)
 • ጧት ከቁርስ በኋላ ቢሆን፣ (ከ 2 እስከ 3 ሰዓት)
 • ከምሳ በፊት ቢሆን (ከ 4 እስከ 5 ሰዓት)
 • ቀን ከምሳ በኋላ ቢሆን ( ከ 9 እስከ 11 ሰዓት)
 • ማታ ከእራት በፊት ቢሆን (ከምሽት 1 ሰዓት እስከ 3 ሰዓት)፣
 • ማታ ከእራት በኋላ ቢሆን (ምሽት ከ 4 እስከ 5 ሰዓት)

3ኛ/ በግልጽ ለመናገር የሰው ሰውነት “ወረተኛ ነው”፡፡ አዲስ ነገር ቶሎ ይቀበላል፤ ቶሎ የመሻል

ምልክት ያሳያል፡፡ ነገር ግን ይለማመዳል የሚል እሳቤ አለ፡፡ ስለዚህ አንድ ዓይነት ደጋፊ ዕፀዋት ለሳምንታት ወይም ለወራት ከወሰዱ በኋላ ደግሞ ሌላ አማራጭ መውሰድ፡፡ ከወር ወይም ከሁለት ወር በኋላ መልሶ በዙር ያንን የተውትን መውሰድ፡፡

4ኛ/ በአንድ ጊዜ የተቀያየጠ ዕፀ መድኃኒት ከመጠቀም ይልቅ፣ ለየብቻቸው መጠቀም ይሻላል፡፡

ምክንያቱም አንዳንዱ ዕፀ መድኃኒት ምንም እንኳን የቫይረሱን ጫና ቢቀንሱም፣ በዚያው ደግሞ

የ ሲዲ 4 ቁጥርን ሊቀንሱ ይችላሉ እና ነው፡፡ መቀየጥ ቢያስፈልግ ሁለት ዕፀ መድኃኒት ቢሆን በቂ ነው፡፡ ይህ ማለት መቀየጫውን ሳይጨምር ነው፡፡ ለምሳሌ በማር፣ በወተት ወዘተ ቢሆን፡፡

5ኛ/ እነዚህ ዕፀ መድኃኒት ለአንድ ዓይነት በሽታ ብቻ የተለዩ አይደሉም፡፡ ከቶውንም ለሁሉም ሰው

ጠቃሚ ናቸው፡፡ ዋናው ሥራቸውም እንዲህ ነው፤

 • ጎጂ ባክቴሪያዎች እንዳይራቡ ማገድ፣
 • ጨጓራ ምግብን በአግባቡ እንዲፈጭ ማገዝ፣
 • የደም ንጽህናን እና ሥርዓትን መርዳት፣
 • የጉበት ጤና እንዲጠበቅ መርዳት፣
 • የአንጀት ትሎችን ማስወገድ፣
 • የመተንፈሻ አካላትን ማጽዳት፣
 • የኩላሊትን የመሥራት አቅም ማገዝ፣
 • ሰውነት በቆዳ በኩል ቆሻሻን እንዲያስወግድ መርዳት፣
 • ከትልቁ አንጀት ውስጥ ቆሻሻ ነገሮች ቶሎ እንዲወገዱ ማገዝ፣
 • የልብን ሥራ ማገዝ እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

6ኛ/ ምንም እንኳን ይጠቅማሉ የተባሉት ዕፀ መድኃኒት ወይም ምግብ ጠቀሜታቸው የታወቀ ቢሆን፣

 • የሰውነት መቆጣት (አለርጂ) የሚያስከትሉትን እና
 • በደም ዓይነት የማይስማሙትን ነገሮች መለየት እና መተው ይገባል፡፡

7ኛ/ ማንኛውም ዕፀ መድኃኒትን ከዋናው መደበኛ መድኃኒት ጋር በአንድ ጊዜ መውሰድ አይገባም፡፡

ለዚህም ሲባል አስቀድሞ የአወሳሰድ ጊዜን በፕሮግራም መለየት ነው፡፡ እንዲሁም ከምግብ ጋር ካልተባለ በቀር ከቁርስ፣ ከምሳ እና ከእራት 2 ሰዓት ያህል አርቆ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ከላይ በተራ ቁጥር 2 ላይ እንደተጠቀሰው ከመደበኛ መድኃኒቱ 2 ሰዓት እና ከዚያ በላይ ማራራቅ ያስፈልጋል፡፡

8ኛ/ እዚህ ላይ በባሕላዊ ዘዴ እንዴት እንደሚዘጋጁ ነው የተነገረው፡፡ እነዚሁ ተክሎች በሌሎች ባደጉት  አገራት በፋብሪካ ደረጃ ተመርተው፣ በተለዩ መደብሮች ለምሳሌ (ሔልዝ ፉድ ስቶር) ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ያን ማግኘት የሚችሉት ሰዎች ባሉበት አገራት መከታተል ይችላሉ፡፡

 1. ከ ፊሊስ ኤ. ባልች መጽሐፍ የተወሰደ ማጣቀሻ አንድ

ፊሊስ ኤ. ባልች. በአሜሪካ እጅግ ታዋቂ የሥነ ምግብ (Nutritionist ) እና ዕፀ መድኃኒት (Herbalist )  ባለሙያ ናት፡፡ በመጽሐፏ በተፈጥሮም ቢሆን በተሻሻለ መልክ እና በፎርሙላ የተሰሩትን ነግራናለች፡፡  በእኛ አገር የፎርሙላ ምርቱን ስለማናገኝ  በባሕላዊ ዘዴ አጠቃቀሙን ለመንገር ከጥቂቱ እነሆ፡፡

ሀ. እሬት፣      እሬት ካርሲን (Carrisyn) የተባለ ንጥረ ነገር አለው፡፡ የቫይረሱን እድገት እና መስፍፍት የሚከላከል ነው፡፡

አጠቃቀም፡- እሬት ወፍራም የሆነውን አንዱን ጆሮ መቁረጥ፣ ማጠብ፣ እሾሁን ከላዩ ማንሳት፣

መሰንጠቅ እና የውስጡን ነጭ ሙዳ ነገር እየቆራረጡ ማንሳት፡፡ ይህን ማር ጨምሮ በመምታት እንዲላላ ማድረግ፡፡ አንድ የቡና ሲኒ ይበቃል፡፡ ይህን ማታ ከእራት በኋላ፣ መጠጣት፡፡ ጠዋት ተቅማጥ ያስከትል ይሆናል፡፡  በሳምንት አንድ ጊዜ፣ ወይም በወር አንድ ጊዜ ቢወስዱት ጥሩ ነው፡፡

ጠቀሜታው፡- ሆድን ያፀዳል፣ የአንጀት ትሎችን ያስወግዳል፣ ከትልቁ አንጀት ውስጥ ቆሻሻ ነገሮችን ይጠርጋል፡፡ ንጥረ ምግብ ወደ ሰውነት እንዲሰርግ ይረዳል፡፡

ለ. እርድ፣       ካሉት የዕፀዋት ምርት ለኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ቫይረስ ኩርኩሚን ዋነኛው ባለብዙ ጠቀሜታና ሁለገብ (Versatile) ነው፡፡ ቫይረሱን በማንኛውም የልክፍት ደረጃ ሳለ ባለበት ማቆም የሚችል ነው፡፡ ኩርኩሚን (Curcumin) ከእርድ ውስጥ ተጣርቶ የሚገኝ ዋናው የመድኃኒት ንጥረ ነገር ነው፡፡ ይህ የተጣራውን በአገር ውስጥ አናገኝም፡፡  ነገር ግን ንፁህ የእርድ ዱቄት በሱፐርማርኬት ውስጥ ይገኛል፡፡ ማንኛውንም የእርድ ዱቄት ግን ለዚህ ጉዳይ አለመጠቀም ነው፡፡

አዘገጃጀት፣ የእርድ ዱቄት በቤትም ማዘጋጀት ይቻላል፡፡ ደረቁን የእርድ ሥር፣ ማጠብ፣  መቀቀል፣መጩፍለቅ፣ ለፀሐይ ማስጣት እና ደጋግሞ በመውቀጥ ዱቄት ማድረግ፡፡ ወይም ቅመም በሚፈጭበት አነስተኛ ማሽን ማስፈጨት፡፡

አጠቃቀም፣ ከእርድ ዱቄቱ ግማሽ የሻይ ማንኪያ፡ በውሃ ላይ በጥብጦ፤ በቀን ሁለት ጊዜ፡ አንድም በባዶ ሆድ ይጠጣል፤ ሁለተኛም ከሰዓት በኋላ በመክሰስ ሰዓት ይጠጣል፡፡ ይህንን በሳምንት ሶስት ቀን ቢሆን ጥሩ ነው፡፡

ጠቀሜታው፣  የተዳከሙ ወይም የተጎዱ ሴሎች ወደ ልክፍት ተሻግረው  እብጠት እንዳይፈጠር ይከለክላል፤ እንዲሁም ለደም እና ለጉበት ጥራት ይረዳል እርድ፡፡   

ሐ. ጥቁር ራዲሽ፣(Black Radish) የፍየል ወተት ሥር፣(Dandelion)   የአህያ እሾህ (Milk Thistle)

አጠቃቀም፤   ሶስቱም ተዘውታሪ ምግብ ናቸው፡፡ ጥቁር ራዲሽ አትክልት ነው፡፡ በጥሬው ሰላጣ

ተሰርቶ ይበላል፡፡ ዘሩን ከውጪ አስመጥቶ መትከል ይቻላል፡፡ አሁን ገበያ ላይ የሚገኘው ሮዝ ቀለም ያለው ራዲሽ ነው፡፡ እሱም ቢሆን ጥሩ ነው፡፡ የፍየል ወተት እና የአህያ እሾህ ዱር በቀል ናቸው፡፡ የፍየል ወተት ሌላው ስሙ እፉዬ ገላ ነው፡፡ ቅጠሉ እንደ ቆስጣ ተሰርቶ ይበላል፤ ሥሩ ተቀቅሎ ወይም ተቆልቶ ተፈልቶ ይጠጣል፡፡ የአህያ እሾህ ፍሬው እንደሱፍ መሳይ ሆኖ ጠቆር ያለ ነው፡፡  ይህ ሱፍ መሳይ ፍሬው በሸክላ በትንሽ ታምሶ ይበላል፡፡

ጠቀሜታው፣  ጥቁር ራዲሽ፣ የፍየል ወተት እና የአህያ እሾህ በዓለም የታወቁ የጉበትን ጤና ለመመለስ እና የጉበትን በሽታ ለመከላከል የሚረዱ ናቸው፡፡ እንዲሁም  የደም ዥረትን ፅዳት ይጠብቃሉ፡፡

መ. ነጭ ሽንኩርት፣ ጥሬውን እንዳለ መብላት ወይም በዱቄት መልክ ማዘጋጀት እና በቀላል መጠቀም ይቻላል፡፡

አጠቃቀም፣ ነጭ ሽንኩርትን በሳምንት እስከ ሁለት ቀን ከምግብ ጋር ጥቂት ፍንካች መመገብ፡፡

ጠቀሜታው፣  በደም ዥረት ውስጥ የኤች አይ ቪ ቫይረስ ከሴል ወደ ሴል እንዳይተላለፍ ይረዳል፡፡

ሠ. ሮቦስ ሻይ፣ (Rooibos tea)  ሮኢቦስ የሚባል አነስተኛ ዛፍ ወይም ቁጥቋጦ በደቡብ አፍሪካ

ይገኛል፡፡  የሻይ ምርቱ ከዚህ ዛፍ ይዘጋጃል፡፡ ይህ ሻይ በደቡብ አፍሪካ፣ አሜሪካ እና በአውሮፓ ይገኛል፡፡  ጠቀሜታው የጎለ ስለሆነ ወደፊት አስመጪዎች ትኩረት ቢሰጡት ጥሩ ነው፡፡ ሲሆን ልባም የእርሻ ሰው ቢገኝ ተክሉን እዚሁ ቢያለማው ህዝብ ይጠቀማል፡፡

አጠቃቀም፣ በሻይ ከረጢት ውስጥ ያለውን በፈላ ውሃ ዘፍዝፎ አቆይቶ መጠጣት፡፡ በሳምንት ሶስት ቀን ቢጠጣ ጥሩ ነው፡፡

ጠቀሜታው፣  ኤች አይ ቪ ወደ ቲ ሴል እንዳይጣበቅ ያግዳል፡፡ ይህ ሻይ በተለያየ አለርጂ ለሚሰቃዩ ሰዎችም ይረዳል፡፡ እንደማንኛውም ሻይ ለብዙዎች ተስማሚ ነው፡፡

ረ. ቫይታሚን ኢ/ በኪኒን ወይም ዘይትማ  መልክ በካብሱል ሆኖ በተለያየ መጠን ይገኛል፡፡

አጠቃቀም፣ በቀን እስከ 8ዐዐ  ዓለምአቀፍ.ዩኒት (IU) መውሰድ ትመክራለች ፊሊስ፡፡ ይህም ባይሆን ሙዝ፣ አኩሪ አተር፣ አረንጓዴ ቅጠላ ቅጠል እና እንቁላል በቫይታሚን ኢ የበለፀጉ ናቸው፡፡

ጠቀሜታው፣  የኤች አይ ቪ ቫይረስ ተባብሶ ወደ ኤድስ ደረጃ እንዳይደርስ ያዘገያል፡፡  ይህ ቫይታሚን በደም ውስጥ አንሶ ቢገኝ፤ ለስጋት ይዳርጋል፡፡

 1. ይቅርባችሁ፡፡
 • ጥቁር ቡና፣
 • ጥቁር ሻይ፣
 • ለስላሳ መጠጥ
 • ማንኛውም የአልኮል መጠጥ፣
 • ስኳር እና በስኳር የተሰሩ ምግቦች፣
 • በፋብሪካ እጅግ የተቀናበሩ ምግቦች፡
 • ያልተጣራ ቧንቧ ውሃ
 • ሲጋራ እና ሌሎች አነቃቂ ወይም አደንዛዥ ነገሮች
 • በርበሬ (ለምን ብትሉ በዚሁ በመረጃ መረብ ላይ ፋሲካ እና በርበሬ የሚለውን አንብቡ)
 • በዘይት እጅግ የተጠበሱ ወይም የተቁላሉ ምግቦች፣
 1. የሚጠጡ ጥሩ አማራጮች ብዙ ናቸው፡
 • ለመጠጥ የተጣራ ቧንቧ ውሃ ወይም የታሸገ ውሃ መጠቀም፣
 • ማግኝት የምትችሉ የተጣራ የምንጭ ውሃ ተጠቀሙ፣
 • በተጣራ ውሃ የተዘጋጀ የማር ውሃ፣ የሱፍ ውሃ፣ የኑግ ውሃ ጥሩ ነው፤
 • ለሚጠጣም ሆነ ምግብ ለማዘጋጀት የተጣራ የቧንቧ ውሃ መጠቀም፡

ተዘውታሪ የዕፀዋት ሻይ ወይም እንደቡና ብዙ ዓማራጮች አሉ፣

 • የሳማ ቅጠል እንደ ሻይ(አሠራሩን በዚሁ በመረጃ መረብ ላይ አንብቡ)
 • ሌሎች እንደ ሻይ ተፈልተው የሚጠጡ
  • የአለኮ ሽፈራው ቅጠል፣
  • የከርከዴ አበባ፣
  • የኮሞሜላ አበባ፣
  • የጦስኝ ቅጠል፣
  • የመቅመቆ ሥር፣
  • የዘይቱና ቅጠል፣
  • የቡና ቅጠል ቁጢ እና የመሳሰሉት፤
 • እንደ ቡና ተቆልተው ተፈልተው የሚጠጡ
  • የፍየል ወተት ሥር፣
  • አኩሪ አተር፣
  • የጃክ ቢን ፍሬ፣
  • የቴምር የውስጡ ፍሬ እና የመሳሰሉትን፡፡
 • አረጓ የጤና ውሃ፣
 • የበሶቢላ እርጥብ ቅጠል እስከ አንድ ጭብጥ (5ዐ ግራም ያህል)፣ይታጠባል፣ ይወቀጣል ወይም ይፈጫል፡፡ በሁለት ብርጭቆ የፈላ ውሃ ለ 1ዐ ደቂቃ ተዘፍዝፎ ይቆያል፡፡ አንድ ኩባያ ይጨመቃል፣ በማር ወይም እንዲሁ ይጠጣል፡፡ በሳምንት ሶስት ቀን ጥሩ ነው፡፡
 • የሳማ እና የሰላጣ  ቅጠል ግማሽ ኪሎ ያህል በአንድነት መመዘን፣በደንብ ማጠብ፣በጥሬው መውቀጥ፣ ወይም በአትክልት መፍጫ መፍጨት፡፡ ሁለት ብርጭቆ ውሃ መጨመር እና መጭመቅ፡፡ አንድ ብርጭቆ አረጓ ውሃ ማጣራት፣ በማር አጣፍጦ አዘውትሮ በቀን አንድ ጊዜ ከምሳ በፊት /ከ4 እስከ 5 ሰዓት/ መጠጣት፡፡ ማጣቀሻ ሁለት  

ማጠቃለያ

ተጨማሪ ዕፀ መድኃኒት  ከታሰበ በሰፊው መጠቀም ይቻላል፡፡ በሌሎች አገራት ልማቱ፣ ምርምሩ ብዙ ነው፡፡ ይህ መነሻ ምሳሌ ይሁናችሁ፡፡  ይህን እና መሰል ጉዳዮችን በሰፊው አንብቡ፡፡ እራሳችሁን ተንከባከቡ፡፡ ጤና ገበያ ነው፡፡ ጤና ካለ ሁሉም ነገር አለ፡፡

ቸር ሰንብቱ፡፡

__________________________________________________________

ማጣቀሻ

ማጣቀሻ አንድ   PHYLLIS  A. BALCH, CNC, 2012,  Prescription for HERBAL HEALING, 2nd

EDITION, An Easy to Use A to Z Reference to Hundreds of Common Disorders and Their Herbal Remedies,  USA.

ማጣቀሻ ሁለት   በቀለች ቶላ፣ ሐምሌ 2ዐዐ9፣ ሕክምና በቤታችን፣ የቤት ውስጥ ባሕላዊ ሕክምና በተፈጥሮ መድኃኒት፣ 5ኛ እትም፣ አልፋ አታሚዎች፣ አዲስ አበባ፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com