ዜና

ኖህ ሪል ስቴት መካከለኛ ገቢዎች ላይ ትኩረት አድርጓል

Views: 2039

– 200 መኖሪያ ቤቶችን በመጪው እሁድ ያስረክባል
ሃብቴ ታደሰ
ከተቋቋመ ስድስት ዓመታትን ያስቆጠረው ኖህ ሪል ስቴት በመጪው እሁድ ግንቦት 25 ቀን 2011 ዓ.ም ተገንብተው የተጠናቀቄ 200 የመኖሪያ ቤት አፓርትመንቶችን ለባለቤቶች ያስረክባል፡፡

ኖህ ሪል ስቴት በዛሬው እለት በቤስት ዌስተርን አዲስ ሆቴል በሰጠው መግለጫ፣ በአዲስ አበባ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለማቃለል እና መካከለኛ ገቢ ያለውን የህብረተሰብ ክፍልን ታሳቢ ያደረገ ነው የተባለለት በጉርድ ሾላ አካባቢ የተገነባው ኖህ ጋርደን (phase one) የመኖሪያ አፓርትመንት፣ የኩባንያው ኃላፊዎች እና ቁልፋቸውን የሚቀበሉ የአፓርትመንቱ ባለቤቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የምርቃት ሥነ ስርአቱ እንደሚካሄድ ገልፆል፡፡

ኖህ ጋርደን በመዲናችን በአዲስ አበባ ውስጥ ካሉ በኖህ ሪል ስቴት ከተገነቡ 21 ፕሮጀክቶች አንዱ መሆኑን የገለጹት የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ብዙነህ ታደሰ፣ የመኖሪያ አፓርትመንት ብዛታቸው 200 የሚሆኑ ባለአራት ፎቅ የመኖሪያ ቤቶችን የያዘ እንደሆነ፣ ግንባታውም መካከለኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍልን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ የተለየ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

ኖህ ሪል ስቴት እስከ አሁን ድረስ ከ4 ሺህ በላይ የሚሆኑ ለንግድ እና ለመኖሪያ ቤት የሚያገለግሉ ቤቶች እና ረዣዥም ሕንፃዎችን እየገነባ ለባለቤቶች ሲያስተላልፍ ቆይቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፣ ኩባንያው ስታዲየም ለገሃር አካባቢ 35 ፎቅ የሚረዝም ሰማይ ጠቀስ ህንፃም መገንባት መጀመሩ ታውቋል፡፡
ኩባንያው፣ ለመካከለኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለማድረግ፣ የመጨረሻውን ቀላል አማራጭ ማቅረቡን የሚናገሩት ኃላፊዎቹ፣ አንድ ቤት ፈላጊ አነስተኛ የቅድሚያ ክፍያን ከፍሎ፣ በተቀሰኑ አመታት ደግሞ ከፍሎ የሚጨርሰውን አማራጭ በመጠቀም ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት ባለቤት መሆን ይቻላል ተብሏል፡፡

የኖህ ሪል ስቴት የሽያጭ ኃላፊ አቶ አብይ ኃይለማሪም ለኢትዮ-ኦንላይን እንደገለጹት፣ አንድ ቤት ፈላጊ በመሃል አዲስ አበባ የኮንዶሚኒም ቤት ለመግዛት ቢፈልግ ክፍያውን መቶ በመቶ መክፈል የሚጠበቅበት ሲሆን፣ ከኖህ ሪል ስቴት ለመግዛት ግን 15 ከመቶ የቅድሚያ ክፍያ በመክፈል እና ቀሪው በረዥም ጊዜ የሚከፈል በመሆኑ ተመራጭ ያደርገዋል ይላሉ፡፡

በሌላም በኩል፣ ቤቶቹ ያላቸው ጥራት እና ተጨማሪ አገልግሎቶችም በኮንዶሚኒየም ቤቶች ውስጥ የማይገኙ እንደሆነ ግንዛቤ ውስጥ መግባት ይኖርበታል በማለት ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው ፕሮጀክቶችን ጥራት ባለው መልኩ እና በከፍተኛ የግንባታ ፍጥነት ሰርቶ በማጠናቀቅ ለደንበኞቹ በማስረከብ ላይ እንደሚገኝ በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ተገልፆል፡፡

በተመሳሳይ ኖህ ጋርደን (ምዕራፍ ሁለት) የመኖሪያ አፓርትመንት ተጨማሪ 1400 ቤቶች ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ በአያት አካባቢ በሚያካሂዱት ግንባታ ደግሞ 740 መኖሪያ ቤቶች በሚቀጥሉት ሁለት አመታት ውስጥ ተጠናቀው ለባለቤቶች ይተላለፋሉ፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ ኖህ ሪል ስቴት በንብረት አስተዳደር ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራ ሮክ ስፕስ የተባለ ኩባንያ ማቋቋሙን ገልፆል፡፡ ኩባንያው በአጠቃላይ ለ3 ሺህ ሠራተኞች የሥራ ዕድል የፈጠረ ግዙፍ ድርጅት ነው፡፡

ኖህ ሪል ስቴት በግሬት አቢሲንያ ኩባንያዎች ባለንብረቶች የተመሠረተ የግል ኩባንያ ነው፡፡ ግሬት አቢሲንያ ከሚያቅፋቸው ኩባንያዎች መካከል አቢሲንያ ውኃ፣ አቢሲንያ ቡና፣ አቢሲንያ ሻይ እንዲሁም ቴክኖ ፕሪንተርስ ይካተታሉ፡፡ ፕሪጋት ጁስን ጨምሮ ልዩ ልዩ ለስላሳ መጠጦችን በማምረት ላይ የሚገኙት የግሬት አቢሲንያ እህት ኩባንያዎች የሆቴል ንግድ ሥራንም እየተቀላቀሉ ነው፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com