በአዲስ አበባ አስተዳደር የ‹‹ሃሳቢያ ቡድን›› ሊቋቋም ነው

Views: 157

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ ጽ/ቤት፣ ‹‹ስለ አዲስ አበባዬ›› የተሰኘ ሃያ አንድ ዓባላት ያሉት ‹‹የሃሳቢያን (ቲንክ-ታንክ) ቡድን›› ለማቋቋም ውጥን እንዳለው ገለጸ፡፡ ከነዋሪው ለነዋሪው የሚበረከት የበጎ አገልግሎት ተግባርን ተቋማዊ ለማድረግ እየሰራሁ ነው፤ በከተማዋ በዝቅተኛ ህይወት ላይ የሚገኙ አረጋዊያንና ህፃናት በዋናነት ታሳቢ ናቸው ብሏል፡፡

በመስተዳድሩ የሥራ ውጥን ላይ፣ ሃያ አንድ ዓባላት የሚኖሩት የሃሳቢያን ቡድን፣ በሀገር ውስጥ እና በውጪ አገራት በመንቀሳቀስና ተሞክሮ በመቅሰም፣ አዲስ አበባን የት እናድርሳት? በምን መንገድ? እንዴት? በሚሉ ነጥቦች ላይ ሃሳብ ያፈልቃል፤ የአተገባበር ሥልት ይነድፋል ተብሏል፡፡

የሃሳቢያን ቡድን አባላት የሚሆኑት ምሁራን፣ በሀገር ውስጥና በውጭ አገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ለአንድ ዓላማ መቀራረብን እንዲፈጠር እንደሚሰራ ታውቋል፡፡

‹‹የዚህ ተግባር ዋና ዓላማ ሃሳቢያንን ወደ መንግሥት ማምጣትና ሙያዊ ሥራ እንዲሰራ ማስቻል ነው›› ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ ቱሪዝምና ኪነጥበብ ቢሮ ኃላፊ ተባባሪ ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ‹‹እነማን በቡድኑ ውስጥ እንደሚካተቱ ገና አልተወሰነም›› ሲሉ ለኢትዮ-ኦንላይን ገልጸዋል፡፡

‹‹ሆኖም፣ የትምህርት ዝግጅት፣ ብዝኃነት፣ ከተማዋን በደንብ ማወቅ፣ በሰዎች ዘንድ ያላቸው አዎንታዊ ተቀባይነት እና በዓለማቀፍ መድረክ ያላቸው ቦታ ታሳቢ ይደረጋል›› ያሉን ፕ/ር ነብዩ፣ ‹‹ምሁራኑ ኑሯቸው የትም አገራት ቢሆን፣ በከተማዋ እድገት ላይ አዎንታዊ አስተዋጽዖ ማበርከት እስከቻሉ ድረስ ሊካተቱ ይችላሉ›› ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ የሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት በድምቀት እንዲከበር እንደሚሰራ ገልፀው፣ የዘመን መለወጫ በዓላትን ለማክበር ከጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ ጋር እየሰሩ እንደሆነም አሳውቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ቱሪዝምና ኪነጥበብ ቢሮ ም/ል ኃላፊ አቶ ሠርጸፍሬ ስብሃት ለዘጋቢያችን እንደተናገሩት፣ በቅርቡ ለአንድ ሳምንት የሚዘጋጀው ‹‹ካርኒቫል››፣ የአዲስ አበባ መገለጫዎች የሆኑ ማንነቶች የብሄር ብሄረሰብ አልባሳትን ጨምሮ በአለባበስ፣ በቁሳቁስ፣ እና በሌሎች የጠቀሜታ ዋጋ (ህሴት) ተወክሎ ይቀርባል፡፡

የአዲስ አበባ ማንነት ልክ በከተማዋ እንደሚከወኑት ሠርጎች ሁሉ፣ ኅብራዊነት ነው ያሉት አቶ ሠርጸፍሬ ስብሃት፣ ‹‹ካርኒቫሉ››ም የአዲስ አበባን ብዝኃ- ማንነት የሚያመላክት ይሆናል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሕይወትና ማንነት ኅብራዊነት ነው፤ ይህ ደግሞ ከፖለቲካው የላቀ ነው፤ አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ ቤት፣ የአፍሪቃ መዲና፣ ዓለማቀፋዊ የፖለቲካ መናገሻ ከተማ ናት በማለት ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ ጽ/ቤት ዛሬ ግንቦት 21 ቀን 2011 ዓ.ም ፍላሚንጎ ፊት ለፊት በሚገኘው ህያት ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የከንቲባው የፕረስ ሴክሬተሪ ወ/ሪት ፌቨን ተሾመ እንደገለጹት ከግንቦት መጨረሻ እስከ ሐምሌ መጀመሪያ በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚተከሉት 4 ሚሊዮን ችግኞች፣ አንድ ሚሊዮን ችግኝ በአዲስ አበባ ከተማ የሚተከልና አግባብ ባለው ክትትል የሚጸድቅ ይሆናል በማለት አሳውቀዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com