ዜና

የአዲስ አበባ ባለ-አደራ ም/ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ

Views: 246

የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት(አ/አ/ባ/ም/ቤት) ግንቦት 16 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ፣ ጊዜያዊውና በህዝብ ያልተመረጠው የከተማው አስተዳደር በሺዎች የሚቆጠሩ “ህገ ወጥ” ቤቶችን ከሁለት ሳምንት በኋላ እንደሚያፈርስ የገለፀውን አስመልክቶ ጥልቅ ወይይት ካደረገ በኋላ ተከታዩን የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡

በቅድሚያ፣ ከተማዋ ውስጥ ሕገወጥነት እንዳይስፋፋና ነዋሪዎቿ ስርአትን ተከትለው የመኖሪያ ፍላጎታቸውን ማሟላት እንደሚገባቸው የምክር ቤታችን አቋም መሆኑን አፅንኦት መስጠት እንፈልጋለን፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን፣ ጊዜያዊው መስተዳድር “ህገ ወጥ” ቤቶችን ለማፍረስ ከተያዘው እቅድ ጋር በተያያዘ፡-

1.የማፍረሱ እንቅስቃሴ ግልጽነት የጎደለው እና ጥናት ላይ ያልተመረኮዘ የጅምላ እንቅስቃሴ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ አፈርሳቸዋለሁ የሚላቸው ከ30 ሺ በላይ አባወራዎች የሞኖሩባቸው ቤቶች እያንዳንዳቸው መቼህግ እንደተገነቡ? እንዴት እንደተገነቡ? ማን እንደገነባቸው? “ህገ ወጥ” የተባሉት ቤቶች ሲገነቡ የከተማዋ አስከባሪዎች ለምን ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንዳልቻሉ ለህዝብ መረጃ ባልቀረበበት ሁኔታ፣ እንደ ድንገት በዘመቻ ተነስቶ ዜጎችን ከሰላማዊ ኑሮአቸው ለማፈናቀል የተያዘው እቅድ በነዋሪዎች እና በጊዜያዊ አስተዳደሩ መካከል ያለውን ጥርጣሬ የበለጠ የሚያሰፋው ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ “በምርጫ እሸነፋለሁ” በሚል ስጋት ውስጥ ያለ ጊዜያዊ አስተዳደር መሆኑን ግምት ውስጥ ፣ ይህ እንቅስቃሴ ሕጋዊ ሽፋንን የተለበሰ መንግስታዊ የመሬት ወረራ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

2.ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንደሚለው ቤቶቹ ሕገ ወጥ ናቸው ቢባል እንኳን፣ ዓመቱን ሙሉ ጠብቆ የክረምት ወቅት መባቻ ላይ ስናስገባ“አፈርሳለሁ” ብሎ መነሳቱ ፍጽሞ ሰብአዊነት እና ኃላፊነት የጎደለው አፈጻጸም ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

3.ጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ ዜጎች ህይወት መስርተው ከሚኖሩበት ቤታቸው ለማፈናቀል ሲነሳ በጊዜያዊነት እና በቋሚነት ሊቋቋሙ የሚችሉበትን መፍትሄ አለመቀየሱ፣ አሁንም ዜጎች በየእምነት ተቋሙ እንዲጠለሉ እና ጎዳና ላይ እንዲወድቁ የሚያደርግ ነው፡፡

ስለሆነም፣ የአ/አ/ባ/ም/ቤት ተከታዩን ምክረ ሃሳብ ለጊዜያዊ አስተዳደሩድረስ ያቀርባል፡-

1.ጊዜያዊ አስተዳደሩ አዳዲስ ህገ ወጥ ቤቶች እንዳይሰሩ በፅናት እየተከላከለናዓለም ህግ እያስከበረ እስከቀጣዩ ምርጫ ሁኔታዎች ባሉበት እንዲቆዩ

2.በሀገሪቷ ሕገ መንግስትም ሆነ ሀገራችን በተቀበለችው እና በፈረመቻቸው አቀፍ ሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ መሠረት፣ ቤቶች ከመፍረሳቸው በፊት ዜጎችን መጠለያ የማግኘት መብታቸው ቅድሚያ እንዲሰጠው እንዲሰጠው አበክረን እናሳስባለን፡፡

ይህ ሳይሆን ቀርቶ ግን፣ በማን አለብኝነት በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ በህዝብ ያልተመረጠው አስተዳደር የኃይል እርምጃ የሚወስድ ከሆነ፣ የአ/አ/ባ/ም/ቤት ገለልተኛ ተመልካች ለመሆን ከህዝብ የተቀበለው አደራ ስለማያስችለው ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሆን ወደ ቀጣዩ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንደሚገባ ያስታውቃል፡፡

የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት
አዲስ አበባ
ግንቦት 21 ቀን 2011 ዓ.ም

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com