ዜና

በተንቤን ምሽት ከ3 ሰዓት በኋላ መንቀሳቀስ ተከለከለ

Views: 285

-የዜጎች የማንነት ጥያቄ ታፈነ

በትግራይ ተንቤን አፈና እና ድብደባ ቀጥሏል። በከተማዋ ላይ በይፋ የተጣለ ገደብ ባይኖርም የትግራይ ህዝብዊ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ሕዎሓት) ያደራጃቸው የደሕንነት አካላት ኗሪዎች ከምሽት 3 ሰዓት በኋላ ከተማ ውስጥ እንዳይንቀሳቀሱ ከልክለዋል።

ዛሬ አመሻሽ ከሁለት መቶ እስከ መቶ ሀምሳ የሚደርሱ የትግራይ ልዩ ኃይል አባላት በከተማዋ የሰልፍ ትርዒት ሲያስዩ ቆይተዋል። ይህም እነርሱን ለማስፈራራት እንደሆነ ኗሪዎች በተለይ ለኢትዮ ኦን ላይን ገልፀዋል።

አቶ ኃይለማርያም ህሉፍ የተባሉ የከተማው ኗሪ እንደገለፁት ህዝቡ “አገው ነን” የሚል የማንነት ጥያቄ እያነሳ ነው። ከ1983 ዓ.ም በፊት የተንቤን ነዋሪ የአገው ሕዝብ ማንነት እንደነበረው ኗሪዎች ገልፀዋል።

ዜጎች ይህንን የማንነት ጥያቄ በሰላማዊ ሰልፍ ለማቅርብ ቢሞክሩም አራት ጊዜ ተከልክለዋል።

ከዩኒቨርሲቲ በዲግሪ ተመርቆ ሥራ እንዳላገኘ የገለፀው ወጣት ፀጋይ ደስታ የብሔርነት ጥያቄ ሲያነሱ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል የትህነግ አመራሮች እንደሚያሰቃዩዋቸው ገልጿል።

ተንቤን ውስጥ በአገው ስም የእግር ኳስ ክበብ ለማቋቋም ሙከራ ተደርጎ ተከልክሏል። ከተማው ውስጥ ለአገው ተወላጆች የፖለቲካ ስልጣን እየተሰጠ አለመሆኑንም ኗሪዎች ገልፀዋል።

በጉዳዩ ላይ የከተማዋን ከንቲባ ወይዘሮ ወርቅ አበባ ገብረ መድህንን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com