ለምግብ ዋስትና! ትኩረት ያጡ ተክሎች “ጃክ ቢን” (Jack Bean)

Views: 438

ቁጥር 2    “ጃክ ቢን” (Jack Bean)

ጃክ ቢን ደረቅ ፍሬው

 መነሻ:-

ከዚህ በፊት “ትኩረት ያጡ ተክሎች- ለምግብ ዋስትና” በሚል ርዕስ ሥር የሳማ ቅጠል ለምግብ ዋስትና እጅግ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው አውስተን ነበር፡፡ የዛሬው ርዕስ ጃክ ቢን ነው፡፡

ጃክ ቢን Jack Bean  የእንግሊዘኛ ስሙ ነው፡፡ በሳይንሳዊ ስሙ ካናቫሊያ ኢንሲፎርሚስ (Canavalia ensiformis) ይባላል፡፡ ሌላ ስያሜ ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ አሁን አልተሰጠውም፡፡ ወደፊት እርሻው የተስፋፋ ዘመን ስያሜ ያገኝ ይሆናል፡፡

የእንግሊዘኛ መጠሪያው የተሰየመው ከጃክ ፍሩት ጋር በማመሳሰል ይመስላል፡፡ በዓለም ላይ ከፍራፍሬ ተክሎች እጅግ ትልቅ ፍራፍሬ የሚገኘው ከጃክ ፍሩት ዛፍ ነው፡፡ እናም ደግሞ በዓለም ላይ እጅግ ትልልቅ የሆኑ ጥራጥሬዎች ውስጥ ጃክ ቢን አንዱ ነው፡፡ ከትልቅነቱ የተነሳ ጃክ የሚል ቅጽል አገኘ ማለት ነው፡፡

ጃክ ቢን በሞቃት አካባቢ እና በከፍተኛ በረሐ ላይ የሚለማ ሐረግ ተክል ነው፡፡ የአፈር ልምላሜ ባነሰው እና አሲዳማ አፈር ላይ እንኳን ይለማል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ቆላ አካባቢዎች በከተማ ውስጥ በራሱ ይበቅላል፡፡ በድሬዳዋ ከተማ በየአጥሩ ላይ ይታያል፡፡ አዳማም ይገኛል፡፡ ነገር ግን ለሰዉ የምግብ እህል አይመስለውም፡፡  ከምርምር ጣቢያ ያደረሰውም የለም፡፡ ለምግብነትም፣ ለገበያም አልደረሰም፡፡ ጃክ ቢን ገና ትኩርት አላገኘም፡፡

በዓለም ላይ ሜክሲኮ እና ብራዚል በከፍተኛ መጠን ያመርቱታል፡፡ አፍሪካ ውስጥ እነ ናይጄሪያ፣ ታንዛኒያ በመጠኑ ያመርታሉ፡፡

ጃክ ቢን በተተከለ ከ6ኛ ወር ጀምሮ ማፍራት ይጀምራል፡፡ የፍሬ ማቀፊያው ከአንድ ስንዝር ይበልጣል፡፡ ረዥም ከመሆኑ የተነሳ አንዱ ፍሬ ማቀፊያ ከ 1ዐ እስከ 2ዐ ፍሬ ይይዛል፡፡  ከአንድ ፍሬ ሓረግ ላይ ብቻ ደርሶ ያፈራው ቢሰበሰብ በአንድ ጊዜ አንድ ኪሎ ይለቀማል፡፡ ዓመቱን ሙሉ ያፈራል፡፡  በየጊዜው ቢለቀም ደግሞ እስከ 1ዐ ኪሎ ምርት ይገኛል፡፡  ስለ ዕፀዋት ለህፃናት እና ለታዳጊዎች መጽሐፍ ላይ የጃክ ቢን አቻ ጥራጥሬዎችም ተገልፀው ነበር፡፡ ማጣቀሻ 1

እነዚህ እንደ ጃክቢን ትልልቅ የሆኑ መሰል ጥራጥሬዎች አባጮማ እና ዘማች አደንጓሬ ይባላሉ፡፡ አሁን አባጮማ የተባለው የቦሎቄ ዓይነት በወለጋ፣ በወላይታ እና በጥቂት ቦታዎች ገበያ ላይ ይገኛል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ በጥቂት ሱፐር ማርኬት ውስጥም ይገኛል፡፡ በኪሎ ከ 1ዐዐ እስከ 15ዐ ብር ይሸጣል፡፡ በኛ አገር ዘማች አደንጓሬ እና ጃክቢን እንኳን ለገበያ እና ለሱፐር ማርኬት ሊቀርቡ ቀርቶ የምርምር ደጃፍ ላይ አልደረሱም፡፡

ጃክ ቢን የአንዱ ፍሬ ማቀፊያን (ዝንቡጡ)    ይዘት ለማሳየት

መገኛ አገሩ፡-

ጃክ ቢን መገኛ አገሩ ሃዊ ደሴቶች ናቸው ይባላል፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ ጥናት ደቡብ አሜሪካ መሆኑም ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት እንደመጣ ወደፊት በጥናት ይታወቅ ይሆናል፡፡

የሚስማማው አካባቢ፡-

በቆላ በረሃ ውስጥ ጥሩ እርጥበት ካገኘ እድገቱ ፈጣን እና ምርታማ ነው፡፡ አበቃቀሉ እንደ ሐረግ ነው፡፡ ቅጠሉ ወፈር ይላል፡፡ ፍሬዎቹ ባቄላ የሚያክሉ ሆነው ክብና ነጭ ናቸው፡፡ በቂ ውሃ ካገኘ በተተከለ በ6ኛው ወር ውስጥ የመጀመሪያውን ምርት መስጠት ይጀምራል፡፡ ጃክ ቢን የፍሬ ማቀፊያው ዝንቡጡ ረዥም ነው፡፡ ከአንድ ስንዝር ይበልጣል፡፡ በመሆኑም ከ 1ዐ እስከ 2ዐ ፍሬ ይይዛል፡፡ ምርቱ በጣም ብዙ ነው፡፡ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ብዙ ምርት ይሰጣል፡፡ ለምሳሌ የምስራች ምርቱ ከአንድ ፍሬ ላይ ደርሶ ያፈራው ቢሰበሰብ በአንድ ጊዜ አንድ ኪሎ ይለቀማል፡፡ ሐረጉ እያደገ ሲሄድ ምርቱም ይጨምራል፡፡ ዓመቱን ሙሉ ያፈራል፡፡ በየጊዜው ቢለቀም በአንድ አመት ውስጥ ከ1ዐ እስከ 15 ኪሎ ምርት ይገኛል፡፡  አጥር ላይ፣ ዛፍ ላይ፣ በረንዳ ላይ ወይም የቤት ግርግዳ ላይ ታኮ ማደግ ይችላል፡፡ ከጥላ ይልቅ ፀሐይ ይወዳል፡፡ ከሁለት እስከ ሶስት ዓመት ድረስ ጥሩ ምርት እየሰጠ ሊቆይ ይችላል፡፡

 ክብካቤ፡-

ሙቀትን ይወዳል፤ ድርቀን ይቋቋማል፤ አንዳንዴ ጥገኛ ተውሣክ ስለሚያጠቃው በየጊዜው የተፈጥሮ መድኃኒት ለምሳሌ የኒም ቅጠል ወቅጦ የውሃውን ጭማቂ መርጨት ነው፡፡ ከአቅም በላይ ከሆነ በባለሙያ አሣይቶ መድኃኒት ማስረጨት ነው፡፡

ጃክቢን ቅጠሉ እና ዝንቡጥ

ጃክ ቢን ለምግብነት፡-

1. ዝንቡጡ

ጮርቃ (ለጋ) ሳለ ዝንቡጡ እንደ ፋሶሊያ ተቀቅሎ ከሌሎች አትክልት ጋር ተሰናድቶ ይበላል፡፡

2. ፍሬው እሸት ሳለ

ከለጋነት በላይ ከሆነ እና የውስጡ ፍሬ ገና እርጥብ ወይም እሸት ሳለ ተቀቅሎ የላይኛው ልጣጭ ተነስቶለት ተሰናድቶ ይበላል፡፡ ጣፋጭ ነው፡፡ በእሸት ደረጃ ሳለ ጣዕሙ ከባቄላ ጋር ይመሳሰላል፡፡

3. ነጩ ደረቅ ፍሬው

ከደረቀ በኋላ፣ ፍሬው ወይም ዘሩ በውሃ ይዘፈዘፋል፤ ይጎነቁላል፤ የላይኛው ገለባ ይነሳለታል፤ ተቀቅሎ፣ ተቀምሞ ከሌሎች አትክልት ጋር ተሰናድቶ ይበላል፡፡

4. ደረቅ ፍሬው ለዳቦ ይሆናል

ደረቅ ፍሬውን ለአንድ ለሊት ውሃ ውስጥ ዘፍዝፎ ማሳደር፡፡ ከዚያም ልጣጩን አሽቶ መለየት እና ማንሳት፡፡ በፀሐይ ሙቀት እስከ 2 ቀን ማድረቅ፡፡ የደረቀውን በሸክላ ምጣድ ላይ ለብ ባለ ሙቀት ካመሱት በኋላ በ7 ኪሎ ስንዴ ላይ 3 ኪሎ ጃክ ቢን ቀይጠው ቢያስፈጩት ጥሩ ዳቦ ወይም ብስኩት ለመጋገር ያስችላል፡፡

5. የጃክ ቢን ወተት ይሰራበታል፡-

ከጥራጥሬ ወገን የሆነው አኩሪ አተር ጥሩ የአኩሪ ወተት ይሰራበታል፡፡ የአኩሪ ወተት ብዙም አልተስፋፋም እንጂ ሙከራው ነበር፡፡ እንዲሁ እንደ አኩሪ አተር ከደረቀው የጃክቢን ፍሬ ጥሩ ወተት ማዘጋጀት ይቻላል፡፡ የጥራጥሬ ወተት፣ የላም ወተት ጋር ተመሳሳይ አይደለም፡፡ የንጥረምግብ ይዘቱ ከላም ወተት ጋር አንድ አይደለም፡፡ ነገር ግን የላም ወተት በማይገኝበት ቦታ ወይም የላም ወተት  ለማይስማማቸው ሰዎች የአኩሪ አተር ወተት ወይም የጃክቢን ወተት ተፈላጊ ይሆናል፡፡

የአኩሪ አተር ወተት ከሚዘጋጅበት ሂደት የጃክቢን ወተት የማዘጋጀት ሂደት ቀላል ነው፡፡

የጃክቢን ወተት ዝግጅት ሂደት፡-

  • ለምሳሌ 1ዐዐ ግራም ጃክቢን  በፈላ ውሃ ውስጥ ለ 3ዐ ደቂቃ ይንተከተካል፣
  • በቀዝቃዛ ውሃ ተዘፍዝፎ ያድራል፣
  • ጠዋት ሲያጥቡት የላይኛው ጠንካራ ሽፋን ወይም ልጣጭ ይነሳል፡፡

እንደዚህ ማለት ነው፡፡

ጃክ ቢን ፍሬው እና ልጣጩ

 • ቀጥሎ በጁስ መፍጫ ይፈጫል ወይም እቤት ውስጥ በሚገኝ ወፍጮ ይለነቀጣል፣
 • ሽርክት እና ወተት ይኖረዋል፣
 • ሽርክቱና ወተቱ በአንድ ላይ እንደገና ለ 4ዐ ደቂቃ ይፈላል፣
 • በወንፊት እና አቡጀዲ ይጣራል፣ ሽርክቱ ለብቻ ይቀራል
 • ወተቱ ላይ ሁለት ማንኪያ ስኳር እና ጨው በሁለት ጣት ተመጥኖ ይደረግበታል፣
 • በቃ ሁለት ብርጭቆ የጃክቢን ወተት ተሰራ ማለት ነው፣
 • ሲጠጣ ጣዕሙ እንደ አኩሪ አተር ወተት ነው፡፡
 • እስከ አንድ ቀን ሳይረጋ ሊጠጣ ይችላል፣ በማቀዝቀዣ ውስጥ ለቀናት ሊቆይ ይችላል፡

ካስፈለገ ተቀምሞ እንደ ሱፍ ውሃ እንጀራ ሊፈተፈትበት ይችላል፡፡

የጃክ ቢን ወተት

ወተቱን በፍሪጅ ማቆየት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ያለ ፍሪጅ እንደ ወተት እየረጋ ይሄድና እስከ ሶስት ቀን ይቆያል፡፡ በ4ኛው ቀን እየበሰለ ስለሚሄድ ከላይ ውሃ ያጠላል፡ ከሥር ወፈር ብሎ ይገኛል፡፡ ይህም አንድ ላይ ይመታ እና ተቀምሞ ለእንጀራ ማባያ ይሆናል፡፡

6. ሽርክቱም ምግብ ይሠራበታል

ከወተት ተጠልሎ የቀረው ሽርክት፣ ሌላ ምግብ ይሠራበታል፡፡ ለምሳሌ በቲማቲም ሱጎ ለዳቦ ማሳያ ይሠራበታል ወይም ከእንቁላል ጋር እንደ ብስኩት ይሆናል፡፡

ከወተቱ የወጣው ሽርክቱ እና ከእንቁላል ጋር የተጋገረው

7. የጃክቢን ሻይ፣

ፍሬው ከውስጡ ከወጣ በኋላ የደረቀው ማቀፊያው (ቅርፊቱ) በፀሐይ ይደርቃል፣ ይሸከሸክና መጠኑ አነስ- አነስ ይላል፡፡ ከዚህ ላይ አንድ የሾርባ ማንኪያ በሁለት ኩባያ ውሃ የጃክ ቢን ሻይ ይፈላበታል፡፡ በማር ወይም በስኳር ይጠጣል፡፡ ያለምንም ማጣፈጫም መጠጣት ይቻላል፡፡

የነጭ ቦሎቄ፣ የኩላሊት መሳይ ቦሎቄ፣ እና የሌሎችም ቦሎቄ ወይም አደንጓሬ ቅርፊት ተፈልተው እንደሻይ ሲጡት ለጤና በረከት አላቸው፡፡ በዚሁ ዓይነት የጃክቢን ቅርፊት እንደሻይ ተፈልቶ ሲጠጣ ብዙ የጤና ጥቅም አለው፡፡ ለምሳሌ ያሸናል፤ ለኩላሊት ይረዳል፤ ለዓይነት ሁለት ስኳር ታማሚ ይረዳል፤ የደም ኮልስትሮል ለማስተካከል ይረዳል፡፡ ሆኖም እርጉዝ እና የሚያጠቡ እናቶች፣ እንዲሁም ህፃናት ይህን ሻይ መጠጣት የለባቸውም፡፡ ኢ ሄልዝ የተባለ የመረጃ መረብ በዚህ ላይ በቂ ገለፃ አለው፡፡ ማጣቀሻ 2

8. የጃክ ቢን ቅጠል፣

ለጋ ቅጠሉ እንደ እስፒናች በስሎ፣ ተጠባብሶ ከሌሎች አትክልት ጋር ተሰናድቶ ይበላል፡፡

9. ለእንስሳት መኖ

ለጋ ወይም ጠንካራውን ቅጠሉን እየቀነጠቡት ለዶሮዎች መኖ ይውላል፡፡ ከደረቀ በኋላ ፍሬው በደንብ ይታመስና በወፍጮ ቤት ይከካል፡፡ ከሌሎች መኖ ጋር ተመጣጥኖ ተደባልቆ ለዶሮ፣ ለበግ፣ ለፍየል፣ ለላሞች ወይም ለሌሎች የቤት እንስሳት መኖ ይሆናል፡፡ የፍሬ ማቀፊያውም ለመኖ ሊቀናበር ይችላል፡፡

10. ጃክ ቢን ለመድኃኒትነት

 • በካንሰር የመያዝ ችግርን ይቀንሳል፤ ምክንያቱም አንቲ ኦክሲደንት የተባለ ንጥረነገር ስላለው፤
 • ለሆድ ውስጥ ጤናን ያጎለብታል፤ አሰር የተባለ ነገር ስላለው ድርቀትን ይከላከላ፤
 • ክብደትን መቀነስ ለሚፈልጉት ይረዳል፤ አነስተኛ ስብ ስላለው ነገር ግን ብዙ አሰር ስላለው ትንሽ ሲበሉት ያጠግባል፡፡
 • ለልብ ጤና መልካም ነው፤ መጥፎ ኮልስትሮልን በመቀነስ እና የደም ግፊትን በማስተካከል፤
 • ጡንቻን ያጠነክራል፤ ፕሮቲኑ ጡንቻን ያዳብራል፤ ይህም ለጡንቻ ጥንካሬ ይረዳል፤
 • የበሽታ መከላከል ሥርዓትን ያበረታል፤ ይህም በቂ ቫይታሚን ሲ ስላለው ነው፤
 • ለቆዳ ጤና እና ውበት ይረዳል፡፡ ማጣቀሻ 3

ማሳሰቢያ

እንደማንኛውም ጥራጥሬ በአግባብ በስሎ ነው የሚበላው፡፡ ጥሬው አይበላም፡፡

ሌላው ጥቅሙ፡-

በስርዓት ተይዞ፣ መስመር እየተሰጠው ካደገ፣ እንደ ወይን ሐረግ  በግቢ ውስጥ ወይም በረንዳ ላይ ጥሩ ጥላ ይሆናል፡፡

ማጠቃለያው፡-

የምግብ ጉዳይ አገራዊ ነው፡፡ ጥቂት የእህል ዓይነት ላይ ተወስነን አልዘለቅንም፡፡ አገራችን በረሐው እና ቆላው ሰፊ ነው፡፡ ይህ እና በተመሳሳይ በቆላ እና በረሐ ሊለሙ የሚችሉ እስከ አሁን ትኩረት ያልተሰጣቸው ላይ ትኩረት ማድረግ አለብን፡፡ ይህ እህል በሌላው አገራት ለምሳሌ በታንዛኒያ፣ በኡጋንዳ፣ በደቡብ አሜሪካ አገራት በጣም ይመረታል፤ ለምግብነት ይውላል፡፡ማጣቀሻ 4

ለአርሶ አደሩ እና አርብቶ አደሩ እንዲህ የተሻለ እህል ዘሩ ከቴክኖሎጂው ጋር አማራጭ ቢቀርብላቸው ተስፋ ነበር፡፡ የእርሻና ተፈጥሮ ሐብት በዚህ እና መሰል ጉዳዮች ላይ ንቃት ቢያድርበት መልካም ይሆናል፡፡

በእርሻ ሥራ ላይ እውቀት እና ፍላጎት ያላችሁ ባለሐብት ይህ ጥቆማ መነሻ ይሁናችሁ፡፡ ወደ ቆላማው የአገሪቱ ክፍል ብትሄዱ ሰፊ ማሳ አለ፡፡ ወደ ገበያ ብታመጡት ከተሜው ጃክ ቢን ቢያገኝ- ጮማ ለምኔ ይላል፡፡

ማጣቀሻ፡-

 1. በቀለች ቶላ፣ 2ዐዐ7 ዓ.ም ስለ ዕፅዋት ለሕፃናት እና ለታዳጊዎች፣ 2ኛ እትም፣ አልፋ አታሚዎች አዲስ አበባ፣
 2. https://www.emedicinehealth.com/bean_pod/vitamins-supplements.htm
 3. https://www.healthbenefitstimes.com/jack-beans/
 4. Nakaaya Karoli, Jakaya O. Sumari and Hasheem Marealle (2017). Utilization of jack beans (Canavalia ensiformis) for human consumption in Tanzania. International Journal of Agriculture and Food Security. ISSN: 0812-3497 Vol. 3 (3), pp. 039-049, March 2017. Advanced Scholars Journals. (http://advancedscholarsjournals.org/journal/ijafs/articles/f-jack-)
Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com