ለእኛ- ለላጤዎች የዳቦ- ፍርፍር!

Views: 680

ሠላም እንዴት ሰነበታችሁ- ቤተሰብ?! መቼም አብዛኛዎቻችን ወንደ/ሴተ-ላጤዎች፣ ብዙ ጊዜ ቁርስ ላይ መርጠን ከምናዘጋጀው የምግብ ዓይነት የፍርፍር- ዘሮች በቀዳሚነት የሚሰለፉ ይመስለኛል፡፡

አንድም በአዘገጃጀት ቀለል ማለቱ፤ አንድም በቤት ውስጥ በቀላሉ በሚገኙ የምግብ ፍጆታ ስለሚዘጋጁ፤ አንድም … ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ የፍርፍር- ዘርን የምንመርጠው፡፡ እንጀራ- ፍርፍር፣ እንቁላል ፍርፍር፤ ሥጋ- ፍርፍር፤ … ፍርፍር!

ፍርፍርን በተለያየ መንገድ ልናዘጋጀው እንችላለን፡፡ ለዛሬ የዳቦ ፍርፍር አዘገጃጀትን አብረን በማብሰል ብንቋደስ ምን ይመስላችኋል?!

በመጀመሪያ፡- የዳቦ ፍርፍር ከማዘጋጀታችን በፊት ይህን ለማድረግ ምን ምን ያስፈልጉናል የሚለውን እንለይ፡፡

  1. 1 ተለቅ ያለ ሽንኩርት፤
  2. 2 ቲማቲም፤
  3. 2 ዳቦ (ዳቦው በተቻለ መጠን ትኩስ ባይሆን ይመረጣል፤ ምክንያቱ ምን መሰላችሁ? ትኩስ ከሆነ ለመፈርፈር ስላማይመች ነው)
  4. 2 ቃሪያ (እንደአሰፈላጊነቱ ነው)፤

አዘገጃጀቱን ደግሞ እንይ፡-

የዳቦ ፍርፍር አዘገጃጀት በጣም ቀላል ነው፤ ሰዓት ቆጣቢም፤ ወጪ ቀናሽም ነው፡፡

በመጀመሪያ፡- ድስታችንን ወይም መጥበሻችንን እንጥዳለን፤ ይህንን ካደረግን በኋላ ሽንኩርት እናበስላለን ወይም እናቁላላለን፤ በመቀጠል ደግሞ ዘይት እንጨምራለን፤ ቀጥሎ ደግሞ ትንሽ በርበሬ መጨመር፤ እዚህ ጋ መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡

በርበሬውን እናቁላለን ብለን እንዳያፍነን እና የዘይት ፍንጥርጣሪው እንዳይፈጀን- ላጤዎች መጠንቀቅ አለብን፡፡

በጣም ጥሩ!

አሁን ያደቀቅነውን ቲማቲም አስከትለን መጨመር፤ እዚህ ጋር አንድ ነገር ልብ በሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ምንም ዓይነት ውሃ አንጨመርም፡፡ ለምን ካላችሁ መልሱ ቀላል ነው፤ ዳቦውን ስንጨምር እንዳይጨማለቅ ስለሚረዳ ብቻ ነው፡፡ እንዲያ ከሆነ የምግብ ፍላጎታችንን በቀላሉ አጣፍጠን እንጨምራለን ስንል፤ የምግብ ፍላጎታችንን እንዳይዘጋ!

ቲማቲም ጨምራችሁ አይደል? ጎበዝ! ምናልባት ቤታችን ውስጥ ካለ ቁንዶ በርበሬ በትንሷ ማንኪያ ግማሽ ጨምረን፤ ትንሽ ጨው ደግሞ አስከትለን፤ ካስፈለገን ቃሪውን ከትፈን ጨምረን፤ (ካላስፈለገን ደግሞ ትተን) ከምድጃችን ላይ እናወርደውና. ዳቦውን በጉርሻችን ልክ እየቆራረስን ጨምረን፤ ማደበላቅ፡፡ በቃ! አሁንማ የቀረን ነገር ቢኖር ለመመገብ ዝግጁ መሆን ብቻ ነው፡፡ በሚቀጥለው ይህን አዘጋጅተው ወዳጅዎን መጋበዝ ይችላሉ፡፡

መልካም ምግብ!

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com