ለእኛ- ለላጤዎች! የመንዲ ምግብ አሰራር

Views: 1103

እነሆ ‹‹ሰው›› ነንና ቃል በገባነው መሠረት፣ ለእስልምና ሃይማኖት እህት-ወንድሞቻችን፣ ለፆም ማፍጠሪያ (መግደፊያ) ይሆን ዘንድ፣ የሚከተለውን የ‹‹መንዲ›› ምግብ አሰራር በመከተል- (ኢንሽ አላህ) አብረን እናበስላለን፡፡

ታዲያ- ቤተሰብ! ፆም ላይ ናችሁና- ከፈጢር በፊት ሽታው አውዶዎት ምራቅዎትን እንዳያበዛው- ጠንቀቅ ማለቱ ጥሩ ነው፡፡ መልካም ፆም- ቤተሰብ!!!

የሚያስፈልጉን ነገሮች፡-

1 የበግ እግር ወይም ታፋ

2 ሽንኩርት

3 ቀረፋ እና ቁርንፉድ

4 ቃሪያ

5 1 ሊትር ወይም ግማሽ ሊትር ዉሃ

6 ጨው

7 ዘይት

8 ካሮት

9 ሩዝ

10 መከለሻ

11 ሚጥሚጣ

እስቲ አሰራሩን እንመልከት፡-

መጀመሪያ የበጉን ስጋ እናጥብና መጠነኛ ዱቄት እንነሰንስበታለን ፤ቀጥለን ደግሞ በሹካ ስጋውን እንበሳሳዋለን፡፡

ከዚህ በኋላ ያለው ሥራችን መጥበሻችንን እናግልና ግማሽ ስኒ ዘይት እንጨምራለን፡፡ ቀጥለን በመካከለኛ መጠን የተከተፈ ሽንኩርት፣ ከዛም 4 ወይም 6 ፍሬ ቁርንፉድ እና ቀረፋ መጨመር፡፡ ቃሪያንም አስክተሎ ጨምሮ በሚገባ ማዋሃድ ይኖርብናል፡፡

ይህንን ካደረግን በኋላ፣ የሚቀጥለው ሥራችን፡- ስጋውን ወደ መጥበሻችን አድርገን 1 ወይም ግማሽ ሊትር ውሃ እና ግማሽ ማንኪያ ጨው ጨምረን እንዲበስል እንከድነዋለን፡፡ በመብሰል ሂደት ውሃውም ምጥጥ ይኖርበታል፡፡

በሌላ በኩል በጎርድጓዳ ሳሃን 2 ማነንኪያ ቂቤ፣ በትንሷ ማንኪያ መከለሻ እና አነስተኛ መጠን ሚጥሚጣ ጨምረን መዋሃድ ይኖርብናል፡፡

ስጋውን ከመጥበሻ አውጥተን በዝርግ ሰሃን ላይ አድርገን በመጥበሻ ላይ የቀረውን ሶስ በማንኪያ እያነሳን ስጋውን መቀባባት ያስፈልጋል፡፡

ቀጥለን ደግሞ በጎድጓዳ ሰሃን ያዘጋጀነውን ውህድ ስጋውን ከቀባነው በኋላ፣ ቡናማ ከለር እንዲያመጣ ወደ ‹‹ሆቭን›› እንከተዋለን፡፡

ታዲያ ይህን አድርገን እንጨርስ እንጂ፣ ለስጋው የሚያስፈልግ ሌላ ሶስ ማዘጋጀት ይኖርብናል፡፡

ለዚህም መጥበሻችንን ጥደን ግማሽ ሲኒ ዘይት መጨመር፤ ከዚያም ውስጡ ሽንኩርት እንጨምራለን፡፡ ለጥቆ ቁርንፉድና ቀረፋውን እና  በአራት ማዕዘን የተከተፈውን ካሮት ወደ መጥበሻችን እጨምረዋለን፡፡

አሁን ደግሞ አነስ ያለ 2 ኩባያ ሩዙን ጨምሮ ከዛም 3 ኩባያ ውሃ እና ትንሽ ጨው ጨምሮ፣ እንዲበስል ቢበዛ ለ1 ሰዓት ያህል ከድኖ መተው፡፡

ሩዙ ሲበስል በዝርግ ሰሃን ያዘጋጀነውን ስጋ እና ሩዙን ጎን ለጎን በማስቀመጥ፣ ሎሚ ካለን በስሱ ቆርጠን ሰሃኑ ላይ ማስቀመጥ፡፡ አሁን የአፍጥር ሰዓት ደርሷል፡፡ መንፈሳዊ ግዴታችንን ተወጥተን፣ መጀመሪያ ከወደ ተምሩ- ቀመስ፤ ቀጥሎ ሾርባ- ጎንጨት፣ ከብስኩቱም ቀማምሰን ስናበቃ ከትንሽ እረፍት በኋላ ሱፍራ ላይ ቁጭ ብለን- መመገብ፡፡ መልካም ምግብ!!!

ቤተሰብ- ወደዳችሁት?! ለሚቀጥለው ወዳጅዎን መጋበዝ ይችላሉ፡፡ እንዴት ደስ የሚል መንዲ እንደሆነ የሰራና የተመገበ ያውቀዋል፡፡ ስለተከታተላቸሁን እናመሰግናለን ብትነግሩን የምትሉት የምግብ አሰራር ካለ ‹‹ኮሜንት›› ወይም ከወደዱት ደግሞ ‹‹ሼር›› አድርጉት፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com