ዜና

ታይፎይድን እንከላከል!

Views: 6722

መነሻ:-

በዚህ ዘመን በጣም በሰለጠኑ አገራት የታይፎይድ በሽታ የለም፡፡ የስልጣኔ ጉድለት ያለብን እኛ የታይፎይድ ጢባጢቢ ሆነናል፡፡ በሽታው በንጽህና ጉድለት የተነሳ በቀላሉ ተላላፊ ከመሆኑም በላይ ዘመናዊ መድኃኒትን እየተለማመደ ስለመጣ በአንድ ሰው ላይ እንኳን ብዙ ጊዜ ይመላለሳል፡፡ በጊዜ ካልታከሙት ወደ አደጋ ይወስዳል፡፡ በብዙ ታዳጊ አገራት በዕፀዋት ተዋጽኦ ምርምር እያደረጉ አመርቂ ውጤት አግኝተዋል፡፡ በሽታውን ለመከላከል ትጋት ያስፈልጋል፡፡ የተፈጥሮ መድኃኒቶች ዘመናዊ መድኃኒቱን ለማገዝ አማራጮች ከመሆናቸውም በላይ የበሽታውን ባክቴሪያ ከሰውነት ለማስወገድ የተሻለ ሆነዋል፡፡

 1. ታይፎይድ ምንድን ነው?

ታይፎይድ በአማርኛ የአንጀት ተስቦ ይባላል፡፡ አንዳንዴም የታይፎይድ ንዳድ (Typhoid fever,) ተብሎ ይጠራል፡፡ ብዙ ጊዜ በቀላሉ የሚጠራው ግን ‹‹ታይፎይድ›› ተብሎ ነው፡፡

‹‹ሜዲካል ኒዉ ቱዴ›› እንደሚገልፀው ታይፎይድ በባክቴሪያ (በጀርሞች) ልክፍት የሚመጣ ነው፡፡ የባክቴሪያውም ዓይነት ሳልሞኔላ ታይፊ (Salmonella typhimurium (S. typhi)) ወይም  (Salmonella enterica) የሚባል ሲሆን፣ ከቀላል እስከ ከባድ የበሽታ ምልክቶችን ያስከትላል፡፡ ይህም ለባክቴሪያው በመጋለጥ እና እስከ በሽታው መከሰት ከ 6 ቀናት እስከ 3ዐ ቀናት ይቆያል፡፡ ብዙ ጊዜም ትኩሳቱ በየቀኑ እየጨመረ ይሄዳል፡፡

የበሽታው ባክቴሪያ የሚኖርው እና የሚራባው በአንጀት እና በደም ውስጥ ነው፡፡ ታይፎይድ የሚተላለፈው በበሽታው ከተለከፈ ሰው ሰገራ በመነሳት ነው፡፡ በዚህ ሰገራ የተበከለ ምግብ እና ውሃ  መመገብ እና መጠጣት ዋነኛው የበሽታው ምንጭ ሲሆን፣ የግል እና የአካባቢ ንፅህና ጉድለት የበሽታው መሰራጫ መንገድ ነው፡፡ የበሽታው ምልክቶች ከሌሎች ብዙ በሽታ ጋር በተለይም ከታይፈስ (ተስቦ) እና ከወባ በሽታ ጋር ተመሳሳይ ሊሆኑ ስለሚችሉ በምርመራ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ 1

 1. የበሽታው ምልክቶች፣
 • ትኩሳት እና ጤና ማጣት፣
 • መዳከም፣
 • የሆድ ውስጥ ህመም፣
 • የሆድ ድርቀት፣
 • የራስ ህመም፣
 • ቀለል ያለ ትውከት ይኖራል፡፡

ጥቂት ሰዎች በሰውነት ቆዳ ላይ ቀላ ያሉ ነጠብጣቦች (እንደ ማጉረብረብ)  ይታይባቸዋል፡፡ አልፎ አልፎ እንደመቀባዥር፣ እንደ መደንዘዝ ያደርጋል፡፡ ለምግብ ፍላጎት ማጣት፣ የአፍንጫ ነስር ሊከሰት ይችላል፡፡  ተቅማጥ ግን ብዙም አይኖረውም፡፡

የታይፎይድ በሽታ ክፋቱ፡- 

 • አንዳንዶች የበሽታው ባክቴሪያ በውስጣቸው እያለ ምንም የበሽታ ምልክት ሳያሳዩ ይኖራሉ፤ ነገር ግን በሽታውን ወደ ሌሎች ያስተላልፋሉ፤
 • አንዳንዶች ከታከሙ እና የበሽታው ምልክት ከጠፋ በኋላም፣ የበሽታው ባክቴሪያ በውስጣቸው ይቆያል፤ ተደጋግሞም ሊያማቸው ይችላል፣
 • ቀደም ሲል ጥቅም ላይ የነበሩትን መድኃኒት እየተለማመደ በመምጣቱ ለህክምናው ፈታኝ ሆኗል፡፡
 1. ዘመናዊ ሕክምና

ለታይፎይድ በሽታ አፋጣኝ ተገቢ ዘመናዊ ሕክምና ማግኘት ያስፈልጋል፡፡  በዘመናዊ ሕክምና የሚሰጠውንም መድኃኒት በአግባብ መውሰድ የግድ ነው፡፡

 1. ባሕላዊ (ሀገር በቀል) ሕክምናው

በዘመናዊ ሕክምና የሚሰጠውን መድኃኒት ለማገዝ እና በሽታው እንዳያገረሽ የሚረዱ የተፈጥሮ የባሕል ሕክምና ዘዴን ለመጠቀም የሚከተሉትን ልብ በሉ፡፡

ምስል አንድ፡- የቆላ ዳማ ከሴ

የዳማከሴ ዓይነት በዋናነት የቆላ እና የደጋ በመባል ይለያሉ፡፡ ሆኖም ብዙ ዓይነታ ዱር በቀል ወይም ጓሮ ትክሎሽ የሆኑም አሉ፡፡ ዳማከሴ ለብዙ በሽታ የታወቀ መድኃኒት ሲሆን፣ ብዙ ጊዜ ለምች የውሃውን ጭማቂ ይቀቡታል፤ ለጉንፋን ቅጠሉን ቀቅለው ይታጠኑታል፤ ለሆድ ህመም ጨምቀው ውሃውን ይጠጡታል፡፡ አሁን እየታወቀ የመጣው የታይፎይድ ፈውስነቱ ነው፡፡ አንድ ጭብጥ የዳማከሴ ቅጠል ይወቀጣል፣ በአንድ ብርጭቆ የፈላ ውሃ ተዘፍዝፎ አንድ ሰዓት ቆይቶ ይጨመቃል፡፡  አረንጓዴ ጭማቂ መሥራት ማለት ነው፣

ምስል ሁለት፡- በሶብላ እርጥብ ቅጠል

የበሶቢላ ቅጠል ሸምጥጦ፣ አንድ ጭብጥ እና የጤና አዳም ቅጠል በትንሹ በአንድ ላይ መውቀጥ፣ በአንድ ብርጭቆ የፈላ ውሃ ለአንድ ሰዓት መዘፍዘፍ እና መጭመቅ፣ አንድ ማንኪያ ማር ማከል፣ አረንጓዴ ጭማቂ መሥራት፣  (በሶቢላ በሚገርም ሁኔታ ለብዙ በሽታ መድኃኒት ነው)

ምስል ሶስት፡- የግራዋ ለጋ ቅጠል

አንድ በቁጥር ከ 5 እስከ 8 የሚደርሱ የግራዋ ለጋ ቅጠል፣ ማጠብ፣ ከዚያም በቡና ሙቀጫ መውቀጥ ወይም በአትክልት መፍጫ መፍጨት፡፡ በአንድ ብርጭቆ ለብ ያለ ንፁህ ውሃ መጭመቅ፣ በላዩ አንድ ማንኪያ ማር ማከል፣ አረንጓዴ ጭማቂ መሥራት፡

የዳማከሴ፣ የበሶብላ ወይም የግራዋ አረንጓዴ ጭማቂው አወሳሰዱ

 • ዘመናዊ መድኃኒት ጠዋት እና ማታ እየወሰዱ ከሆነ፣ የዚህን ጭማቂ እኩለ ቀን እና እኩለ ለሊት ይጠጡ፤ ከመደበኛው መድኃኒት አርቀው ማለት ነው፡፡
 • ዘመናዊ መድኃኒት ከጨረሱ በኋላ ከሆነ ጠዋት እና ማታ እስከ አንድ ሳምንት ይጠጡ፡፡ 2

ማሳሰቢያ፣ ነፍሰ ጡር እና ጡት የሚያጠቡ እናቶች የግራዋ ውሃ እንዳይጠጡ፡፡

ግራዋን የጠላ ጋን ከማጠብ ያለፈ ዋጋ አልሰጠነው ይሆናል፡፡ ነገር ግን የታይፎይድ በሽታ እንዳያዳግም አድርጎ ከሰውነት ውስጥ ያስወግዳል፡፡ በአፍሪካዋ ጋና አገር የተደረገ ጥናት ይህን እጅግ ያረጋግጣል፡፡ 3     ከዚህም በላይ በጋና አገር ግራዋ እንደጎመን ተሠርቶ ለምግብነት ይውላል፡፡

በሌላዋ የአፍሪካ አገር ካሜሩን ቀደምት የህዝብ እውቀትን መሠረት ያደረገ ጥናት በማድረግ የሴጣን መርፌ (Bidens pilosa)  ብቻውን፣ ወይም ከሐረግሬሳ ቅጠል ጋር ወይም ከፓፓያ ቅጠል ጋር ተጨምቆ የታይፎይድ መድኃኒትነቱን አረጋግጠዋል፡፡4  

እኛ አገር በአረምነቱ የሚታወቀው የሴጣን መርፌ ‹‹የምች›› መድኃኒት መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ በዚህ አዲስ ጥናት የታይፎይድ መድኃኒት መሆኑ መረጋገጡ መልካም ነው፡፡ የሴጣን መርፌ ከአናቱ ላይ በቀላሉ የሰው ልብስ ላይ የሚጣበቁ እሾኻም ነገሮች አሉት፡፡ አንድ ሰው በመንገድ ዳር የሴጣን መርፌን ማየቱን ያስተውል ይሆናል፤ ነገር ግን እቤቱ ደርሶ ልብሱን ሲፈትሽ ተሰግስገው ያገኛቸዋል፡፡  በዚህ ፀባዩ የተነሳም በግድ ዘመዴ የሚል ስያሜም አለው፡፡

አንድ ጭብጥ ያህል ቅጠሉን መልቀም እና በውሃ ማጠብ ከዚያም መውቀጥ፣ በአንድ ኩባያ ውሃ ለ 5 ደቂቃ ማፍላት፤ ሲበርድ ማጥለል፣ በማር ወይም እንዲሁ መጠጣት፡፡ ምሬት የለውም፡፡ ከላይ ለእነ በሶቢላ እንደተነገረው ለሳምንት ወይም ከዚያም በላይ መጠጣት ነው፡፡

ስለ እፅዋት የአፍሪካ ፖርታ የተባለ ድረ ገጽ ላይ የሴጣን መርፌ በብዙ የአፍሪካ፣ ኤስያ እና የሐሩር ክልል በሆነው አሜሪካ ውስጥ ለብዙ በሽታ መድኃኒትነት ጥቅም ላይ መዋሉ ተገልጿል፡፡  ሥሩ፣ ቅጠሉ እና ዘሩ (ያው መርፌው)   ለፀረ ባክቴሪያ፣ ለተቅማጥ፣ ለወባ፣ ለጉበት፣ የሚፈሰ ደም ለማቆም፣ ለራስ ምታት፣ ለጆሮ መነፍረቅ፣ ለዚህ እና ለመሳሰሉት ጥቅም ይሰጣል፡፡ ከሰሐራ በታች ባሉት ያፍሪካ አገራት ለጋ ቅጠሉ በአትክልትነት ተሰርቶ ይበላል፡፡5

ስለዚህ በዚህ ጽሑፍ ላይ የሴጣን መርፌ ወይም በግድ ዘመዴ ለታይፎይድ ይጠጣል መባሉ ምንም አግራሞት የሚፈጥር አይደለም፡፡ የሚገርመው እስከዛሬ ባለማወቃችን እንደ አረም ስናስወግደው መኖራችን ነው፡፡

 1. ምግብ እና መጠጥ

5.1 በታይፎይድ የተነሳ በሕክምና ላይ እያሉ እና ከሕክምናው በኋላ ለጥቂት ወራት

እንዲህ ቢያደርጉ መልካም ነው፡፡

 • የታሸገ ውሃ፣ ወይም የተጣራ ንፁህ ውሃ በቀን እስከ 2 ሊትር ወይም ከዚያ በላይ መጠጣት፣ (ቢቻል የማር ውሃ፣ የሱፍ ውሃ፣ የኑግ ውሃ፣ )
 • የተለያዩ ፍራፍሬዎች አጥቦ እና ልጦ ጭማቂ ማዘጋጀት እና ወዲያው መጠጣት
 • የአጃ፣ የኦትስ፣ ወይም የገብስ ሾርባ መውሰድ፤
 • ሥጋ እና አትክልትን አብስሎ ሳያቆዩ ወድያው መመገብ፣
 • ነጭ ሽንኩርት ከምግብ ጋር ማዘውተር፣
 • ለምግብ ዝግጅት እና ለእቃ ማጠቢያ የተፈላ ወይም የተጣራ ውሃ መጠቀም፣
 • ከበሽታው እስኪድኑ ግማሽ ሎሚ በአንድ ብርጭቆ ውሃ ላይ መጭመቅ እና አንድ ማንኪያ ማር አክሎ በቀን እስከ 3 ጊዜ መጠጣት፣
 • የ በሶቢላ ሻይ፣ የ በግድ ዘመዴ ሻይ፣ ማዘውተር ባክቴሪያውን ለማዳከም ብሎም ለማስወገድ ይረዳል፡፡

5.2   የሚከለከሉ ምግቦች፡-

ከበሽታው እስከሚድኑ ድረስ  የሰውነት በሽታ መከላከል አቅም እንዳያዳክሙ እና ለባክቴሪያው ምግብ ሆነው፣ በሽታውን እንዳያጠናክሩ እነዚህን ባይመገቡ ይመከራል፡፡

 • ጥሬ አትክልት፣ ጥሬ ሥጋ፣
 • ተሠርተው ያደሩ ምግቦች፣
 • ያልተፈላ ወይም ያልተጣራ ውሃ፣
 • ያልተፈላ ወተት
 • በፍሪጅ ውስጥ የቆዩ ምግቦች እና መጠጦች
 • ለስላሳ መጠጦች እና
 • ስኳር ያላቸው ምግቦች እና መጠጦች፣
 1. መከላከያው ፡-

ታይፎይድን ለመከላከል መልካሙ ነገር

 • በምግብ ማዘጋጀት ሥራ ላይ የተሰማሩት በየጊዜው የጤና ምርመራ እና ክትትል ማድረግ ይኖርባቸዋል፤ አለቆቻቸው እና አሠሪዎች ለዚህ ጉዳይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው፡፡ ለተመጋቢዎች የሚያቀርቡላቸው ምግብ፣ ሰዎችን በታይፎይድ ባክቴሪያ እየበከለ እንደሆነ ወይም ንጽህናው የተጠበቀ ምግብ እንደሆነ ማረጋገጥ አለባቸው፡፡
 • መዳኑ እስኪረጋገጥ ድረስ በበሽታው የተያዘ ሰው ለሌሎች ምግብ ማዘጋጀት የለበትም፣
 • ምግብ ለማዘጋጀት እና ለመጠጥ የተጣራ ውሃ መጠቀም፣
 • ሁሉም ሰው እጅን ዘወትር በተለይም ምግብ በማዘጋጀት እና በመመገብ ጊዜ መታጠብ፣
 • ጥሬ አትክልት እና ፍራፍሬን በአቼቶ (በቬኒገር) እና በውሃ ማጠብ፣
 • የግል እና የአካባቢን ጽዳት መጠበቅ፣
 • የሽንት ቤት እና አካባቢውን ንጽህናን በተገቢው መጠበቅ፣
 • ከሽንት ቤት ሲመለሱ እጅን በተገቢ መታጠብ፡፡

በትምህርት ተቋማት እና በዩኒቨርሲቲ ጊቢ ውስጥ በዚህ በሽታ የሚጎዱ ተማሪዎች ብዙዎች ናቸው፡፡ አግባብነት ባላቸው ቦታዎች ላይ የውሃ ማጣሪያዎችን መግጠም እና ተማሪዎችን እና በዚያ የሚገኙትን ማህበረሰብ መታደግ የበሽታው መከላከያ አንድ ሙያ ነው፡፡

                                                                                   

ማጣቀሻ፡-

 1.  Tim Newman  2017  University of Illinois-Chicago, School of Medicine

Medicalnewstoday        https://www.medicalnewstoday.com/

 1. በቀለች ቶላ፣ ሐምሌ 2ዐዐ9፣ ሕክምና በቤታችን፣ የቤት ውስጥ ባሕላዊ ሕክምና በተፈጥሮ

መድኃኒት፣ 5ኛ እትም፣ አልፋ አታሚዎች፣ አዲስ አበባ፡፡

 1. Bekoe et al.; IJTDH, 23(4): 1-13, 2017; Article no.IJTDH.31448  Herbal Medicines Used in the

Treatment of Typhoid in the Ga East Municipality of Ghana

International Journal of TROPICAL DISEASE & Health

http://dspace.knust.edu.gh/bitstream/123456789/11026/1/Bekoe2342017IJTDH31448_P.pdf

 1. Tsobou et al. 2013,- Plants Used Against Typhoid Fever in Bamboutos, Cameroon

www.ethnobotanyjournal.org/vol11/i1547-3465-11-163.pdf

 1. Plant Resources of Tropical Africa( PROTA)

https://uses.plantnet-project.org/en/ PROTA)

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com