ጥበብ ሳይጠብ

Views: 600

ጥበብ ምንድን ነው?

አንዳንድ ጥያቄዎች አሉ ለመጠየቅ ቀላል የሆኑ፤ በጠያቂው ልቦና ምላሹም ቀላል የሚመስል፤ ግን ለመመለስ አንደበትን ለመክፈት ዝግጅት ሲጀመር ማጣፊያው የሚያጥረን፤ ከእንደዚህ ዓይነት ጥያቄዎች አንዱና ዋነኛው ነው ከላይ የተቀመጠው ጥያቄ:: የመለስነው የመሰለን ግን በበቂ ሁኔታ ያልመለስነው፤ ያወቅነው የመሠለን ግን ያላጠናቀቅነው ዕውቀት፤ እንደው በደፈናው በጋራ ተስማምተን ያለፍነው ጥያቄ ነው:: ታላቁ መጽሐፍ ላይ ኄኖክ “ጥበብ ሆይ ማደሪያሽ የት ነው?” ሲል መጠየቁም የዚህ ግርታ ተጋሪ በመሆኑ ይመስላል:: እውቁ ደራሲ ሰለሞን ደሬሳም ‹‹አንዳንድ ጥያቄ አለ፣ አስር ጊዜ ተጠይቆ፤ አስር ጊዜም መልስ ተሰጥቶበት፤ እንደገናም፣ አስር ጊዜ የሚጠየቅ፡፡›› ያለው ይህንኑ ሳይሆን አይቀርም፡፡

 ከግርታው መልስ ከብዥታው ባሻገር

     የጥበብ ትርጉሙ ሠፊ፣ አሻሚ እና አከራካሪ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ:: አስማሚ እና ሁሉን አካታች የሆነ የትርጓሜ ወሰን እንደሌለ ከመስማማት ውጪ በሌላ ጥበባዊ ብያኔ ላይ ሥምምነት እስካሁን የለም:: በየዘመኑ ያለውን ተለዋዋጭ እና አዳዲስ የጥበብ ዓይነቶች መቀላቀላቸው ሲታከል ደግሞ ጥቂቶች እንኳ የተስማሙበት ትርጓሜ ጊዜያዊ ሆኖ ይገኛል:: ይህን ስንለው ቀላል፣ በልማድ እና በደመነፍስ የምንግባባበት ቃል፤ የተለያየ ፍቺ የተለያዩ ምሁራን እና የጥበብ ሠዎች ሰጥተውት እናገኛለን:: ምን ያህል አካታች እና አግባቢ መሆናቸውን ማረጋገጥ ባንችልም ጥቂት ትርጓሜዎችን ግን ከዚም ከዛም ጽሑፎች ላይ ዕንይ:-

     ከሣቴ ብርሀን ተሠማ የ “ዐማርኛ መዝገበ ቃላት” ባሉት የቃላት ፍቺ መጽሐፋቸው ተሠማ ኃ/ሚካዔል ግጽው፤ ጥበብን እንዲህ ይፈቱታል:- በአዕምሮ ብልህነት፣ ጥበብ፣ ፍልስፍና በአዕምሮ ላይ እየተሣለ ልዩ ልዩ ጥበብን መጠበብ፣ መፈልሰፍ፣ ማንኛውንም የብልኻት ሥራን አራቆ መሥራት፣ ተራቀቀ፣ ተጠበበ፣ ጥበበኛ ሆነ፤ ብለው አስቀምጠዋል::

ዊኪ ኮትስ (Wiki quote) የተባለው ድህረ ገጽ ደግሞ ጥበብን እንዲህ በሚል ትርጓሜ ይሰጠዋል:-

“Art is the process or product of deliberately arranging elements in a way that appeals to intellect, sense or emotion. It encompasses a diverse range of human activities, creations and modes of expression, including music and literature. The meaning of art is explored in a branch of philosophy known as aesthetics.”

በግርድፉ ሲተረጎም “ጥበብ ለአእምሮአችን፣ ለመረዳታችን እና ለሥሜታችን ይኹነኝ ተብሎ የተቀናበረ ኃሳብ ውጤት የሚሆንበት ሂደት ነው:: እጅግ ብዝሀነት ያላቸውን የሠው ልጆች እንቅስቃሴ፣ ፈጠራ እና የገለጻ ዓይነቶች፣ ሙዚቃ እና ሥነ-ጽሑፍን ጨምሮ የጥበብ ግዛት አባላት ናቸው:: የዚህ ሠፊ ጽንሰ ኃሳብ ትርጓሜ እና ምንነት የፍልስፍና ትምህርት ክፍል በሆነው ሥነ-ውበት ውስጥ በጥልቅ ይመረመራል::” ይለናል ዊኪ ኮትስ:: ወደ ዊኪፒዲያ ትርጓሜ ስንሄድ ደግሞ ይህን እናገኛለን:-

” የጥበብ ትርጓሜ ከ እስከ ቢዘረዘር፤ የደራሲው ምናብ፣ ጽንሠ ሐሳብ ወይም ክሂል እንዲሁም የሠው ልጆች እንቅስቃሴ፤ የምሥል ወድምጽ ፈጠራ በያዘው ዕምቅ ውበት ሳቢያ እና በሚያስተጋባው ኃያል ሥሜት የተነሳ የሚፈጠረውን መሥተጋብር ማድነቅ እና እውቅና መሥጠትን ጠቅሎ ይይዛል:: እነዚህ ጥበባዊ እንቅስቃሴዎች በደፈናው የጥበብ ሥራን፣ ጥበባዊ ሂስን እና የጥበብ ታሪክ ጥናት ብሎም የጥበብ ሥርጭትን ያካትታሉ::” ብሎ ይፈታዋል::

የጥበብ ፋይዳ

“የጥበብ ነጻነት” (Freedom Of Art) የሚለው ጽንሰ ሐሳብ በዘመናዊው ማኅበረሰብ ውስጥ እንደተፈጠረ እና እንደሚቀነቀን ብዙ ጸሐፍት ይስማማሉ:: ይህ ገዢ ኃሳብ በብዙ ከምንጋራቸው የ19ነኛውና የ20ኛው መቶ ክ/ዘመን የምዕራባውያን የጥበብ ውጤቶች ላይ ተጽዕኖ ፈጥሮ አልፏል:: በ18ተኛው መቶ ክ/ዘመን በምዕራባውያን ለነበረው የሥነ – ውበት እና የሠብዐዊነት እንቅስቃሴ አርነት (Autonomy) ዋነኛ ማዕከላዊ ጭብጥ እንደነበር ታሪክ ምሥክር ነው::

የዚህ ማዕከላዊ ጭብጥ ዋነኛ መገለጫው ደግሞ ሥነ – ውበት በገዛ ራሱ ልምምድ በሚሰጠው ሥሜት እንጂ በሌላ ማንኛውም ውጫዊ መለኪያ ሊዳኝ አይገባም የሚለው ኃሳብ ነው:: ሕጉም የሚሠራው ከራሱ ከጥበብ ብቻ ነው:: ስለዚህ አንድ የጥበብ ሥራ ልዩ እና የራሱ እሴት ፈጣሪ ባለቤት ነው ማለት አለብን እንጂ በሌላ ውጫዊ መለኪያ ዋጋ ወጥቶለት ሊረክስ አይገባም ይሉናል ይህን ኃሳብ የሚያቀነቅኑ ፈላስፎች እና የጥበብ ሠዎች::

የጥበብ ሥራ፤ በተፈላጊ ጥቅም ያልተገዛ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ግብረገባዊ ወይም ሌላ ውጫዊ ጠቃሚ ወይም ጎጂ ኃሳብ የማይጫንበት ነጻ መንገድ ነው:: ዐርነት ያለው (Autonomous) ጥበብ የጸደቅኩ ነኝም ምክንያታዊነቴም በሌላ ውጫዊ አካል የተረጋገጠ ነው ብሎ አያውጅም፤ ብለው አሳብያኑ ይሟገቱለታል ለዚህ ዐይነተኛ የጥበብ መንገድ::

ጥበብ በፍጹም ነጻነት ውስጥ ሆኖ፣ ዐርነት በወጣ መልኩ ሲተገበር ከላይ በጠቀስነው መልኩ እንደሆነ አሳብያኑ እና ይህን መንገድ የሚከተሉ ጥበበኞች ሲከራከሩ ኖረዋል:: በዚህ ከፍታ ደረጃ የተሠሩም ይሁኑ ከዚያ በመለስ የተሰሩቱ የጥበብ ውጤቶች የሚዘረዘር ማኅበራዊ ፋይዳ እንዳላቸው ያስቀመጡ ጸሐፍት እንዳሉ ግን መርሳት የለብንም:: የጥበብ ፋይዳ በብዙ መልኩ የተገለጸ ቢሆንም የተወሰኑትን መርጠን ዕንይ:-

ጥበብ ለማኅበራዊ ሂስ፣ ለሚዲያ ትችት’ና
እውናዊነትን ለመጻረር (Against reality)

    በምዕራባውያን የጥበብ ታሪክ ውስጥ፣ የአትኩሮት ነጥብ (Focal Point) የነበሩ ብዙ አጋጣሚዎች እንደነበሩ ታሪክን አጣቅሰን መናገር እንችላለን:: ለምሣሌ:- የፈረንሳይ ዐብዮት የጥበብ ሥራ ምርት ላይ እና ዐመለካከት ላይ ጉልህ አሻራን ትቶ አልፏል:: በአውሮፓ ውስጥ በ19ኛው ክ/ዘመን ለመጣው የጥበብ ንቅናቄ እና የሠው ልጅ የማያቋርጥ እድገትም ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክቷል ይህ ዐብዮት::

በ20ኛው ክ/ዘመን የተከሰተው የቴክኖሎጂ፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እንዲሁም የሳይንስ ዐብዮት፤ ጥበብን በተለየ ደረጃ እና ይዘት እንዲሠራ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርጓል:: ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የጥበብ ባለሙያዎች የጥበብ ሥራዎቻቸውን ማኅበረሰብን የሚለውጡበትን መሣሪያ መፍጠሪያ ቤተ ሙከራ አድርገው ይቆጥሩታል::

ይህ ዓይነቱ የጠቢቦች አመለካከት የዘመናዊ ጥበብ መሠረት ብቻ ሳይሆን ቀጣዩንም የጥበብ መንገድ የተለመ አጋጣሚ ተደርጎ ይቆጠራል:: በዚህ ዘመን ያሉ የጥበብ ሠዎችም ይህን ቀዳማይ መርሆ ተከትለው በጥበብ የማመጽ (የመቃወም) መንገዳቸውን ቀጥለዋል::

በጥበብ ሥራዎች ማኅበረሰብን መታዘብ፣ መገሰጽ፣ አቅጣጫ ማመላከት፣ ያለፈውን እያነሱ ማስታወስ እና መጪውን መጠቆም እንደሚቻል ያሳዩን የጥበብ ሥራ ውጤቶች መዘርዘር እንችላለን:: የሚዲያዎችን ሚዛናዊ አለመሆን እና ወገንተኝነት በመውቀስ ተቋማቱን በተለያየ ግዜ የሸነቆጡ የጥበብ ሥራዎችንም እንዲሁ ማስታወስ ይቻላል:: ነባራዊውን ሁኔታ እየተጻረሩ የተሻለ ነገ እንዲፈጠር መስበክን ወይም የትላንትን መልካም ግዜ (Nostalgia) እያስታወሱ ታዳሚን ማንቃት የጥበብ ሥራ የሚጠቀስ ዋነኛ ፋይዳ እንደሆነ መስማማት ይቻላል::

/ከማኅበራዊ ሂስ (የጥላሁን ገሠሠ ዘፈን የሆነውን “አርቆ ማሰቢያ እያለን አእምሮ እንደምን ተሳነን ለማክበር ቀጠሮ” ከአገር ውስጥ የጥበብ ሥራ በዐይነተኝነቱ መጥቀስ እንችላለን፣ ) /ከሚዲያ ትችት (የመሀመድ ሠልማን “ፒያሣ ማህሙድ ጋር ጠብቂኝ” የሚለው መጽሐፍ ላይ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥንን “ቁጩ” ብሎ የገለጸበት ጽሑፍ ዐይነተኛ ምሣሌ ነው::)

ከነባራዊው ሁኔታ ጋር ግጭት (ፍቅር እስከ መቃብር “ገባር ሥርዓትን መቃወም፣ የመደብ ልዩነቱን መሸንቆጥ “ሀብታም ደኃ” የሚለው ልዩነት፣ ልጅን ለቤ/ክ አገልጋይነት ያለ ልጁ ምርጫ የሚሰጥበትን መንገድ መተቸት፤ በበዛብህ ታሪክ ውስጥ የተገለጸውን፤) እና ሎሎች መሰል የጥበብ ሥራዎችን መጥቀስ ይቻላል…./

ባልጠበበ መልኩ አሻሚ ትርጉም ያለው ጥበብ ሲሠራ ከላይ በጥቂቱ ለመዳሠስ የሞከርነውን ይመስላል ከፊል ገጽታው:: ስለ “ጠበበው ጥበብ” እና ፋይዳው አሁን በዚህ ዘመን ለምንኖር ሠዎች ተጽፎ መቅረብ አለበት ትላላችሁ? እየኖርነው፣ እየጻፍነው፣ እያነበብነውም እንዴት ይሆናል? ሁካታ፣ ረብ የለሽነት፣ ገበያ ተኮር፣ ለብ ለብ፣ ውል አልባ እንዲሁም ፋይዳ ቢስ የሆነን የጥበብ (ጥበብ ከተባለ ማለት ነው) ሥራን በየቀኑ እየተነፈሳችሁት ነውና ነጋሪ ስለማያሻችሁ ሠፊውን የጥበብ መንገድ ከግርግሩ ወጣ ብላችሁ እንድታስቡት አስታወስኳችሁ!!!

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com