“ህልም እንደፈቺው ነው”?

Views: 5535

“ህልም እንደፈቺው ነው” በሚል ማኅበረሰብ ውስጥ ስለህልም ምንነት እና ፍቺ
ለመጻፍ መነሳት ከተረቱ ጋር መጋፋጥ ይጠይቃል:: በርግጥ ህልም እንደፈቺው ብቻ ሳይሆን፣ እንደተመልካቹም እንደሚለያይ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ይናገራሉ:: እንዳለንበት የሥሜት ሁኔታ እና መንፈስ የምናየው ህልም እንዲሁም ፍቺው ሊለያይ እንደሚችል ተመራማሪወቹ አጽንዖት ይሰጣሉ:: ይህን ህልም እንደተመልካቹ እንደሆነ የሚገልጽ ኃሳብ ታዋቂው የሥነ-ልቦና ባለሙያ ካርል የንግ (Carl Jung) ህልም ፈቺዎችን፤ ህልም ለመፍታት ከመነሳታቸው በፊት ከግንዛቤ እንዲያስገቡ ደጋግሞ ያሳስባል::

በዚህ ጽሑፍ ህልም እንደፈቺው ነው እና ህልም እንደተመልካቹም ነው ከሚሉት ኃሳቦች ጀምረን እስከ ውስብስብ የህልም አፈታት ሂደት፣ ታሪክ እና የህልም ምንነት በመጠኑ ለማየት እንሞክራለን::

ህልም ምንድን ነው?

ህልም አዕምሮአችን በተፈጥሮአዊ መንገድ ሥራውን ሲሠራ የሚፈጠር ነገር ነው:: መካከለኛ በሚባል ዕድሜ (Average) ብናስበው ሠዎች ለ25 ዓመታት እንተኛለን፤ ከዚህ ውስጥ ሥምንት ዓመቱ በህልም ያልፋል ተብሎ ይታሰባል::

ህልም ተከታታይነት ያላቸው ምሥሎችን፣ ኃሳቦችን፣ ሥሜቶችን እና ፍንደቃዎችን በአዕምሮአችን ያለፈቃዱ በተወሰነ የእንቅልፍ ግዜ ሲከሰት የሚፈጠር ነው:: ህልም በብዛት በ “Random Eye Movement” (REM) ወቅት የሚታይ ሲሆን ይህ ደረጃ አዕምሮአችን ንቁ ሆኖ ሥራውን ከሚከውንበት ደረጃ ጋር ይቀራረባል:: በጥልቁ የእንቅልፍ ግዜ የምናየው ህልም ብዙም የሚታወስ ባለመሆኑ  በ(REM) ግዜ ያለውን ህልም ነው አስታውን ልንናገር የምንችለው:: የህልም ይዘት እና ጥቅም ሙሉ ለሙሉ የሠው ልጅ ተረድቶታል ማለት አዳጋች ነገር እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ:: ይሁን እንጂ በሳይንስ፣ በኃይማኖት እና በፍልስፍና የህልምን ምንነት ለመረዳት ከፍኛ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል::

                    የህልም ፍቺ:- 

ይህ ጥበብ ድብቅ የሆነውን የህልምን ትርጉም ለመፍታት የሚደረግ ጥረት ነው:: የተለያዩ ባሕሎች የየራሰቸው የሆነ የህልም አፈታት ዘዴ እና የጋራ የሆኑ ሥምምነቶች አላቸው:: በየራሰቸው መንገድ ባዳበሩት እውቀት ከትውልድ ትውልድ እያሸጋገሩ እዚህ ደርሰናል::

(Oneirology) ኦኒውሮሎጂ ህልምን በሳይንሳዊ መንገድ የሚያጠና የትምህርት ዘርፍ ነው:: ይህ ሳይንሳዊ መንገድ ህልምን ከመፍታት የሚለየው ህልምን በሚለካ (quantitative) መንገድ ሂደቱን ለመረዳት ይሞክራል እንጂ በህልም ውስጥ ያለውን ኃሳብ ወይም ይዘት መተንተን ወይም መፍታት አይደለም ግቡ:: በተጨማሪም፣ ኦኒውሮሎጂ ከኒውሮሎጂ (Neurology) ጋር በመጣመር በእንቅልፍ ወቅት የአዕምሮን እንቅስቃሴ (Wave) በመለካት ህልምን ለመረዳት የተለያዩ ሳይንሳዊ መንገዶችን በመጠቀም ሙከራ ያደርጋል::

የህልም ምንጩ እና የሚፈጠርበት ምክንያቱ ምን እንደሆነ ማወቅ ባይቻልም እንኳ ይህ ጥናት የአዕምሮን አሠራር ለመረዳት ጠቅሟል ይላሉ ይህን ሳይንሳዊ ክዋኔ የሚደግፉት ተመራማሪዎች:: ምሣሌዎችን ሲጠቅሱም አንዳንድ የአዕምሮ ህመሞችን በዚህ ዘዴ ተጠቅመው ሊደርሱበት እንደቻሉ ያስረዳሉ:: በተጨማሪም ሠዎች ስለህልማቸው ምንነት እና ስለሚያጋጥማቸው ቅዠቶች (Nightmares) ለመረዳት ትልቅ አስተዋጽዖም ማድረጉን ያነሳሉ::

ሲግመንድ ፍሩድ /1856 – 1939 እ.ኤ.አ

የቅድመ ሳይንስ ዘመን ብለን በምንጠራው ግዜ ሠዎች ስለ ህልም ያላቸው እውቀት እና የፍቺ ተሰጥዖ በማረጋገጫ ላይ የተደገፈ አልነበረም ይለናል- ፍሩድ:: ከሳይንስ መነቃቃት እና መታወቅ በኋላ ይህ ሚቲዎሎጂ የተጫነው አስተሳሰብ ወደ ሳይኮሎጂ ተሸጋግሯል:: ዛሬ ላይ ከጥቂቶች ምሁራን በቀር አብዛኛዎቹ ህልም የግለሰቡ ሥነ ልቡና ውጤት መሆኑን ተረድተዋል ማለት ይቻላል- ይለናል:: በተጨማሪም ይህ የሚቲዮሎጂ ዘመን ካለፈ በኋላ ሠዎች ለአዲሱ ሳይንሳዊ ትንታኔ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳሳዩ ፍሩድ ያምናል::

ፍሩድ የህልም ትንታኔውን ሲቀጥል ተኝተን የምናልመው ምስል ወይም ድርጊት በራሱ ነቅተን ስናስበው በቀላሉ የምንቀበለው አይደለም:: ነቅተን ስናጤን ከዛኛው የህልም ዓለም ጋር መዛነቅ ይፈጠራል፤ ህልሙ ካለፈ በኋላ በነቃው አዕምሮአችን የማስታወስና የመረዳት አቅማችን ደካማ በመሆኑ ግራ መጋባት እና በታየው ነገር ላይ ያለንን እምነት ይቀንሳል:: ከዛ አለፍ ሲልም ደግሞ ህልሙን ልንቃወመው ልንገደድ እንችላለን:: ይህ ዓይነት በህልም ዙሪያ ያለ የአረዳድ ችግር ለብዙ መቶ ዓመታት ቀጥሏል:: ፍሩድ እንደሚለን ከሆነ እሱ በኖረበትም ዘመን ይህ ጥያቄ የሚያረካ መልስ አላገኘም::

ከሁሉ ነገር በፊት በህልም ዙሪያ የነበረው መልስ ሳይሆን ጥያቄ ነው ይላል ምሁሩ ፍሩድ:: ታዲያ ይህ ጥንታዊ ጥያቄ በመሠረቱ ባለሁለት መልክ ነው፤ በመጀመሪያ የህልም አካላዊ ጠቀሜታ ነው:: ይህ ጠቀሜታ ባዮሎጂካል መሠረት እንዳለው ይታመናል:: በሁለተኛ ደረጃ እያንዳንዱ ህልም ከሌላ አዕምሮአዊ አስተጻምሮ ጋር ይያያዘል ይለናል ፍሩድ::

በዚህ አካላዊ የህልም ትንታኔ የሚስማማው ፍሩድ ብቻ ሳይሆን ብዙ የህክምና ባለሙያ የሆኑ አዋቂዎች ይስማማሉ:: በነሱ አረዳድ ከሆነ ህልም ውጫዊ በሆነ አካላዊ መነቃቃት ወደ ውስጣዊ ተሸጋግሮ ሰው በሚተኛበት ሰዓት የሚገለጥ ሁኔታ ነው:: ይህ መገለጥ ሊቋረጥም ሆነ ያለምንም መቋረጥ ሊቀጥል ይችላል::

                ካርል የንግ /1875 – 1961/

ወደ 60 ዓመት በሚጠጋ የምርምር ሕይወት በህልም እና በሥነ ልቡና ላይ ሲያደርግ የኖረው ስዊድናዊው ዶክተር ካርል የንግ “Symbols and the Interpretation of Dreams” በሚለው መጽሐፉ ላይ ስለ ህልም ይህንን ይላል:

“ህልም ፍቺን በተመለከተ ምንም ዓይነት ደንብ የለም፣ እንኳን ሕግ ይቅርና፤ በአጠቃላይ የህልም ጥቅሙ ካሣ ይመስላል:: ይህ የካሣ (Compensation) ጽንሠ ኃሳብ ተስፋ ሰጪ እና አመቺ መላምት ነው ብዬ እወስደዋለሁ” ይለናል::

በህልም አፈታት ሂደት ውስጥ ሁለት አዕምሮዎች ይጋጠማሉ፤ አንደኛው ህልም አስፈቺው ሲሆን፣ ሌላው ደሞ ፈቺው ነው:: ይህ የሁለት አዕምሮ ግጥሚያ በዘዴ መከናወን አለበት:: የሁለቱ አዕምሮዎች ተመሳሳይ መሆን የፍቺ ሂደቱ ላይ ትልቅ አስተወጽዖ ያመጣል:: የንግ ራሱ ወደ ውስጥ የሚያይ (Introvert) በመሆኑ ሲግመንድ ፍሩድ ደግሞ ወደ ውጭ የሚያይ (Extrovert) ነውና ወደ ውስጥ የሚያዩ ራሳቸውን መግለጽ የሚቸገሩ ታማሚዎች እሱ ጋር ሲሄዱ ለነሱ ብዙም ቁብ ባለመስጠት ራሳቸውን በሚገልጹት ታማሚዎች ላይ ግዜን በማጥፋት ውስጣውያኑን ይበድላል ብሎ የንግ ፍሩድን ይከሰዋል:: ይህ የአዕምሮ አለመጣጣም ትልቅ የፍቺ ክፍተት እንደሚፈጥር በአጽንዖት ያስጠነቅቃል::

የንግ ሁለት መሠረታዊ አሠራሮችን ለህልም ፍቺ ጥበብ ይመክራል፤ አንደኛው ነባራዊ (Objective) ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ሥሜታዊ (Subjective) ናቸው:: በነባራዊው የህልም አፈታት ዘዴ ሠውየው ሰውየውን ነው የሚወክለው:: ለምሣሌ በህልም እናት ከታየች እናት ነች ትርጓሜውም ላይ፤ ፍቅረኛም ከሆነች ፍቅረኛ..ወዘተረፈ…..በሥሜታዊ አፈታት ዘዴ ደግሞ የሚታየው ነገር በሙሉ ከዐላሚው አንጻር ነው የሚፈታው:: የንግ ነባራዊው የህልም አፈታት ዘዴ አስቸጋሪ እንደሆነ እንደሚያምን ይነግረንና ጥሩ አስታዋሽ አላሚ ከተገኘ ግን በደንብ የሚሠራ ዘዴ እንደሆነ ይከራከራል::

በህልማችን ውስጥ ዓይነተኛ (archetype) ከሆኑና ከሚገለጹት ውስጥ በሴት ውስጥ ያለ ወንዴነት (animus) በወንድ ውስጥ ያለ ሴትነት (anima) እና ጥላ (Shadow) እንዲሁም ሌሎች ይጠቀሳሉ:: ታዲያ እነዚህ በህልም ሲገለጡ በአኃዝ ወይም በምልክት ዓይነት ነው:: በሽማግሌ ሰው፣ በወጣት ልጃገረድ ወይም ትልቅ ሸረሪት፤ ብቻ እንደየ ሁኔታው ይገለጻሉ:: ይህ የሚወክለውም በውስጣችን በነቃው አዕምሮ ውስጥ ያለን የተሸሸገ ዝንባሌን እንደሆነ የንግ ያብራራል::

የንግ የሁልግዜም መከራከሪያው ከሆኑ ኃሳቦች አንዱ እና ዋነኛው ህልምን ለመፍታት ከመነሳታችን በፊት ህልሙን ስለምንፈታለት ሰው ግላዊ ሁኔታ በቂ እውቀት ሊኖረን ይገባል የሚለው ነው:: ህልም እንደፈቺው ነው ብቻ ሳይሆን እንደተመልቹም ነው እንደ ማለት::

እኛ’ና ህልም እና ፍቺ

ኢትዮጵያውያን ከህልም እና ከፍቺው ጋር ጥልቅ ቁርኝት እንዳላቸው መናገር ከእውነታው መራቅ አይሆንም:: በክርስትናውም ሆነ በእስልምናው እምነት በተመሠረተ የህልም ትርጓሜ እና ፍቺ በመንተራስ ብቻ አብዛኛው ሕዝብ ከሁለቱ ቤተ እምነቶች የኑሮውን ፍልስፍና እንደመቅዳቱ የቁርኝቱ ዐቢይ ማሳያ አድርገን ልንወስደው ያስችለናል:: ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን መሪዎች (ነገሥታት) እና ቤተሰቦቻቸው ከህልም ጋር ያላቸውን ጥልቅ መተሳሰር ስናይ ለአባባላችን ሌላ ደጋፊ ምክንያት ይሆነናል::

ህልም የኢትዮጵያን የታሪክ ሂደት እንደቀየረ ማሳያ አድርገን ከምንወስዳቸው አጋጣሚዎች አንዱ የንጉሥ ዳግማዊ ምኒልክ ታሪክ ነው:: አለቃ ለማ በልጃቸው መንግሥቱ ለማ አማካኝነት በተደረሠ መጽኃፋቸው “ትዝታ ዘ አለቃ ለማ” ላይ ከሠሜን ወሎ የሆነች አንድ ህልም ፈቺ ጨረቃ በፈካች ሌሊት ስለመውለድ ያየችውን ህልም ለነገሥታት ቤተሰብ ቅርብ ለሆነች ሴት በመናገሯ እና ሴትዮዋ ጉዳዩን በቁም ነገር በመውሰዷ ለንጉሥ ምኒልክ አባት ንጉሥ ኃይለመለኮት አንዲት ሴትን አስተዋውቃ እንድትጸንስ ታደርጋለች:: ከ9 ወር በኋላ ንጉሥ ምኒልክ በፈካች ጨረቃ ለሊት እንደተወለደም አፈታሪኩ ይናገራል::

የዳግማዊ ምኒልክ ንግሥና ብቻ በህልም እንዳልተገኘ የኢትዮጵያ ታሪክ ይነግረናል:: ቅዱስ ተ/ኃይማኖት ለሁለት ክ/ዘመን ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር የነበረውን የዛግዌ ሥርወ መንግሥት ወደ ቀድሞው የሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት የመለሰው በህልም ይህ እንዲፈጸም እግዜር ማዘዙን ለዛግዌ መሪዎች ካሳመነ በኋላ ነበር:: ይህም ትልቅ የታሪክ ምዕራፍን ዘግቶ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል::

ኢትዮጵያውያን ህልምን የሚተረጉሙት በባሕላቸው አረዳድ እና በኃይማኖታዊ እሴት ታግዘው ነው:: ይህን ባሕል ወኃይማኖት ጋብቻን መሠረት ባደረገ መልኩ ህልምን ዓለማዊ እና መንፈሳዊ ብለው ይመድቧቸዋል- የህልም አዋቂዎች:: መንፈሳዊውን ህልም ደግሞ ለሦስት እንደገና ይከፍሉታል:-

  • ጥሩ
  • መጥፎ
  • አካላዊ …. በሚል

  

   በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን ህልም የሰውን ድብቅ ባህሪ ገላጭ ነው ብለው ያምናሉ:: ለምሣሌ:- አንድ የሚያውቀውን ሌላ ሰው በህልሙ የሸረሪት ድር ሲያደራ ካየው፣ ያ ሰው ይቅር ባይ አይደለም ማለት ነው ተብሎ ይታሰባል:: ሰውየው ስለራሱ ያልተናገረው ባኅሪው በህልም እንደተገለጠ ይታሰባል- እንዲህ ዓይነት ህልም ሲታይ:: ይህ ብቻ አይደለም ህልም ሠዎችን ማስጠንቀቂያ እንደሆነም ተደርጎ ይታመናል:: ለምሣሌ:- አንድ ሠው በጨለማ ሲሄድ በህልሙ ራሱን ካየ፣ ያ ሰው ሊጠነቀቅ ይገባዋል ማለት ነው መልዕክቱ::

ቤተልሔም ለገሠ የተባለች ኢትዮጵያዊ ደራሲ ሥነ ልቡናዊ፣ ኃይማኖታዊ እና ባሕላዊ የሆነውን የህልም አረዳድ ሰብስባ “የህልም ፍቺ” የተሰኘ መጽሐፍ አሳትማለች:: ከአያቷ ባገኘችው እውቀት ተመርታ ህልም መፍታትን የተካነችው ይህች ጸሐፊ፣ እዚህ መጽሐፏ ውስጥ የተለያዩ ምልክቶችን እና ፍቺያቸውን አካታለች፤ የተወሰኑትን ልጥቀስና ጽሑፌን ላጠናቅ::

ውሻ:- ታማኝነትን፣ የተጨቆነ ወሲባዊ ሥሜትን በሥነልቡናዊ ፍቺው ይወክላል፤

ውሻ ሲጪኽ:- ውርደትን ይወክላል በባሕላዊ ፍቺው፤

ውሻ ሲያባርር:- የሠይጣንን መከታተል ይወክላል በኃይማኖታዊ ፍቺው፤

ውሻ ወተት ሲጠጣ:- ጦርነትን ይወክላል በባሕላዊ ፍቺው፤

ዐየሩ ሲጨፈግግ:- በህልም ዐየር ሲጨፈግግ ያየ ሰው፣ በዓለማዊ እና በመንፈሳዊ ዓለም መካከል መያዙን (trapped መሆኑን) ይወክላል፤ መንፈሳዊ ፍቺው::

ለህልም ፈቺዋ ቤተልሔም የህልም ምልክቶች (Symbols) ቋሚ ሳይሆኑ፣ እንደየ ሁኔታው እና እንደየ ዐውዱ ተለዋዋጭ ናቸው::

ህልም እንደፈቺው ነው፤ የህልም ምልክቶች ተለዋዋጭ ናቸው፤ ህልም እንደፈቺው ብቻ ሳይሆን፣ እንደተመልካቹም ነው… ወዘተረፈ… እያልን እዚህ ደርሰናል፤ ታዲያ ህልምን መረዳት ከባድ መሆኑን ከመረዳት የዘለለ ነገር ካልተረዳን ይህ ጽሑፍ ጥሩ ነው ማለት ነው ማለት እችላለሁ- ደረቴን ነፍቼ!!! በነቃ አዕምሮአችን ይህን ያህል ከተረዳን ራሱ ማለፊያ ነው:: የበለጠ ለማወቅ በርትታችሁ ዐልሙ:: ይህ ነው ማሳረጊያ መልዕክቴ!!!

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com