በርበሬአችን እና የአፍላቶክሲን ችግሮች

Views: 1162

(በርበሬ! አፈር አይንካሽ ዛሬ!)

የጓዳችን ዋና ቅመም የሆነው በርበሬ፣ የዶሮን ወጥ ከሚያደምቁትና ከሚያጣፍጡት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የዶሮ ወጥ ደግሞ ፋሲካን ከሚያደምቁት ውስጥ አንዱ የምግብ ዓይነት ነው፡፡ በርበሬ ሌሎችም ብዙ አጃቢ ቅመማት አሉት፡፡

ምስል አንድ፡-

(በግራ ደርቆ የተቀነጠሰ በርበሬ በቀኝ የበርበሬ ዱቄት)

የበርበሬን ጥቂት አጃቢዎቹን እንጥቀስ፣  እርጥብ ቅመማት ነጭ እና ቀይ ሽንኩርት፣ ዝንጅብል፣ በሶቢላ፣ ሮዝመሪ፣ ደረቅ ቅመማት  ኮረሪማ፣ ጦስኝ፣ ከሙን፣ ነጭ አዝሙድ፣ ጥቁር አዝሙድ፣ ድንብላል፣ አብሽ፣ ቅርንፉድ፣ ቀረፋ፣ የጤናዳም ፍሬ እና ጨው ናቸው፡፡  እንደ ፍላጎት ከነዚህ የሚቀነሱም፣ ሌሎች የሚጨመሩም ይኖራሉ፡፡ ወደ ኋላ የዚህን አሰራር አመላክታለሁ፡፡

በርበሬ ላይ የዓለም ጥናት

ከ ቺሊ፣ ጣሊያን፣ ፖርቹጋል እና እንግሊዝ የተውጣጡ ተመራማሪ ሳይንቲስቶች አንድ ጥናት በርበሬ ላይ በቅርቡ አድርገው ነበር፡፡ በመላው ዓለም ላይ ከተደረጉ ጥናቶች ከመቶ በላይ የሚሆኑትን ቃኙ፡፡  ይህ ጥናት የተደረገበት አብዛኛው በርበሬው ከእርሻ ተለቅሞ ደርቆ፣ ነገር ግን በሚከማችበት፤ በሚጓጓዝበት፣ በፋብሪካ ውስጥ እና በመሳሰሉት ደረጃ ተበክሎ የተገኘ ነው፡፡ በእኛ አገር የተደረገውንም ጥናት አካተውበታል፡፡ የእኛ አገር በርበሬ ደርቆ የተቀመጠ ሳይሆን፣ በየደረጃው ውሃ እየጠጣ የሚጓጓ በመሆኑ የብክለቱ መጠን ከፍ ብሎ መታየቱ አልቀረም፡፡

ጥናቱ ላይ  እንዲህ ይብራራል፤ የበርበሬ ዛላው ወይም ዱቄቱ እንደሌሎቹ የእርሻ ምርት ለሻገታ ልክፍት (fungal infection) የተጋለጡ ናቸው፡፡ ቀጥለውም የሻገታ ልክፍቶቹ አንድ ዓይነት ወይም ብዙ ዓይነት ማይኮቶክሲንስ የተባሉ የሻገታ ምርዝ ብክለት (mycotoxin contamination)  ያስከትላሉ፡፡  የበርበሬ ዛላ ምርቱ በሚሰበሰብበት ጊዜ እና ከተሰበሰበ በኋላ፣ በሚደርቅበት ወቅት እና ምርቱ የሚጓጓዝበትን ጊዜ ጨምሮ፣ ብዙ ጊዜ የሚያጠቁት የተለያዩ የሻገታ ዝርያዎች አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አስፐርጊሉስ እና  ፐኒሲሉም የሚባሉት በካይ ዝርያዎች (Aspergillus and Penicillium species) በዋናነት ይገኛሉ፡፡ ማይኮቶክሲንስ ማለት የብዙ ዓይነት የሻገታ ልክፍቶች በአንድነት የሚጠሩበት ጥቅል ስም ሲሆን ከእነሱም ውስጥ ቀደምት ጥናቶች የሚነግሩት በኢንዱስትሪ የተቀነባበረ በርበሬ

 • በአፍላቶክሲን (aflatoxins (AFs),
 • አችራቶክሲን ochratoxin A (OTA), ፣
 • ፉሞኒሲንስ fumonisins (FBs), ፣
 • ዜራለኖን zearalenone (ZEN), ፣
 • ትሪቾቴሴነስ trichothecenes (TCTs ፣ እና
 •  ፓቱሊን patulin (PAT) ሊበከል ይችላል፡፡

ለሻገታው (ፈንገስ) እጅግ መራባት እና ለማይኮቶክሲንስ መፈጠር አካባቢያዊ ክስተቶች ትልቁን ሚና ይጫወታሉ፡፡ እነዚህም ለምሳሌ የእርጥበት ሁኔታ፣ የሙቀት መጠን፣ የአሲድ አልካላይን ሚዛን፣ (pH)   እና የንጥረምግብ ይዘት ቁልፍ ነገሮች ናቸው፡፡

ማይኮቶክሲንስ ሙቀትን ይቋቋማሉ እናም አንዴ በርበሬ ምርት ሂደት ውስጥ ከተፈጠሩ በኋላ ለማስወገድ አስቸጋሪ ናቸው፡፡

ትልቁ ስጋት ማይኮቶክሲንስ ለብዙ አጣዳፊ እና ሥር የሠደዱ በሽታዎች መነሻ ምክንያት እየሆነ መምጣት ነው፡፡ ማጣቀሻ 1

ምግብን ከበሽታ ስለመጠበቅ ጉዳይ ላይ የሚዘጋጅ መጽሔት በ ግንቦት 2ዐ11 እ.ኤ.አ እትሙ ላይ በርበሬ ላይ የተደረገ አንድ ጥናት አካቶ ነበር፡፡ የጥናቱ ርዕስ በመጋዘን ተከማችቶ በሚቀመጥ ጊዜ የበርበሬ አፍላቶክሲን እና የሻገታ ቶሎ ቶሎ መራባት የዳሰሳ ጥናት የሚል ነው፡፡

ይኸኛው ጥናት ከሚጠቅሰው ላይ ይህንን እናስተውል፤

 • ምንም እርጥበት በማያስገባ ፕላስቲክ ከረጢጥ እና ከጁቴ በተሰሩ ጆንያ ውስጥ በተቀመጡት  ደረቅ በርበሬ ላይ ከመጀመሪያ ቀን አንስቶ፣ በ 5ዐኛው፣ በ1ዐዐኛው እና በ15ዐኛው ቀን ላይ የንጽጽር ጥናት ተደረገ፡፡  በጁቴ ጆንያ ውስጥ የተቀመጠው በርበሬ ለአፍላቶሲን ብክለት በጣም የተጋለጠ ሆነ፡፡
 • የተከማቸበት የሙቀት ደረጃ ከ 25 እስከ 3ዐ ድግሪ ሴንቲግሬድ በሆነበት ብክለቱ ብሶ ተገኘ፣ የሙቀት ደረጃው  2ዐ ድግሪ ሴንቲግሬድ  በሆነበት የተቀመጠው የተሻለ ሆነ፤ ረዥም ጊዜ ማስቀመጥ እና ሙቀቱ እየበዛ ሲሄደ ብክለቱም የበዛ ይሆናል ሲል ያሳስሳል ጥናቱ፡፡ ማጣቀሻ 2 

የእኛ አገር የበርበሬ አያያዝ  

አርሶ አደሩ የበርበሬ አዝመራ ወራት ሲደርስ ይለቅመው እና ይሰበስበዋል፡፡  በወቅቱ  ከእርሻ ማሳ ውስጥ ከበርበሬ እንጨቱ ላይ ለቅመው ወድያው በመሬት ላይ ይዘረጉታል- እንዲደርቅ ብለው፡፡ እስኪደርቅም ከ4 እስከ 7 ቀናት እዚያው መሬቱ ላይ እያገለበጡት ያደርቁታል፡፡ በርበሬው በመሬቱ ላይ ተዘርሮ በመድረቅ ሄደት ላይ እያለ፤ በርበሬውን ከመሬቱ አፈር ውስጥ  የሚገኙ ሻጋታ (ፈንገስ) አስፐርጊሉስ ወይም ፐኒሲሉም በተባሉት ወይም በሌላ ዓይነት የሻገታ ዝርያዎች  ይለክፉታል፡፡ እነዚህ ልክፍቶች እርጥበት እና ሙቀት ባገኙ ቁጥር ይመረቅናሉ፣ ይባዘሉ፣ ሺ ምንተሺ ይሆናሉ፡፡  ልክፍቶቹ የሰው የጤና ጠንቅ መሆናቸው ደግሞ የተረጋገጠ ነው፡፡

በኛ አገር የተለመደው አምራቹ በርበሬውን ባደረቀበት ቦታ ላይ እንዳለ በጅምላ ሊሸጠው ይችላል፡፡ ወይም ወደ ጎተራው ከቶ ያስቀምጣል፡፡  በጅምላ የገዛው ሰው መልሶ ያከፋፍላል ወይም ይቸረችራል፡፡ በብዛት ገዝተው በትልልቅ መጋዘን የሚያስቀምጡም አሉ፡፡  እንደዚሁ ሲል ከአምራች፣ ከጅምላ ገዢ፣ ከአከፋፋይ፣ ከችርቻሮ ሻጭ እያለ በርበሬ ቀማሚ ዘንድ (ባልትና ቤት)፣ ወይም በየቤታችን ይደርሳል፡፡ እኛም ሸክሽከን፣ ደልዘን፣ አድርቀን፣ ዱቄት አድርገን እንቀምማለን፤ ከዚያም ለምግብነት እናውለዋለን፡፡

ከዚያስ ምን ሆነ?

በርበሬውን ሻጮች (አብዛኖቹ) በዚህ ሁሉ ሂደት ዋጋ እንዳይቀንስ ወይም የበለጠ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ በየጊዜው ውሃ ያርከፈክፉበታል፡፡  በርበሬው ዛሬ ውሃ ሲያርከፈክፉበት ውሃውን ይመጠዋል፣ ቅላቱ ይጨምራል፣ ያምራል፣ ክብደቱም ይጨምራል፡፡ ሻጩ ከበርበሬ ብቻ ሳይሆን ከውሃ ክብደትም የበርበሬ ዋጋ ይቀበላል ማለት ነው፡፡ ይህ አሳሳቢው የውሃ ማርከፍከፍ ተግባር በሚያሳዝን ሁኔታ አምራቹ ዘንድ፣ ጅምላ ገዢ፣ አከፋፋይ፣ ወይም ቸርቻሪው ዘንድ  ከእነዚህ ከአራት አካላት አንዱ፣ ሁለቱ፣ ሶስቱ ወይም አራቱም ዘንድ ሊተገበር ይችላል፡፡

ለምሳሌ የመጨረሻ ቸርቻሪው 1ዐ ኪሉ በርበሬ ላይ ግማሽ ሊትር ውሃ ቢያርከፈክፍ ነገ ሲሸጠው ከ1ዐ ኪሎ በላይ ነው ዋጋ የሚቀበልበት፡፡ በፊትም በርበሬው ሲመጣ ሂደቱ እንደዚሁ እያለ፤ በርበሬው በየቦታው ውሃ እየጠጣ ቸርቻሪው ዘንድ ደርሶ ይሆናል፡፡

በርበሬው በየቦታው ውሃ እየተቀበለ እየወዛ፣ እያማረ ከእርሻ እስከጓዳችን ከዚያም እስከ ሆዳችን ቢመጣ ምንድነው ችግሩ፣ ውሃ አይደለም እንዴ ምን አለበት?  ወጥ ራሱ ሲሰራ በውሃ አይደለም እንዴ?  ሊባል ነው፡፡

እምህ! የችግሩ ቁልፍ እዚህ ጋ ነው፡፡ እነዚያ በርበሬው ከማሳ ሲለቀም እና መሬት ላይ ሲዘረጋ በርበሬውን የለከፉት የሻገታ ልክፍቶች በየጊዜው ውሃ ሲያገኙ እየተባዙ ይመጣሉ፡፡ በርበሬው ከላይ ሲታይ የሚያምር ቀይ ወዛም ነው፤ ልክፍቶቹ ያሉት ከውስጥ ነው፡፡ የሚራቡት ውስጥ-ለውስጥ ነው፡፡ በነዚህ ልክፍቶች  የተለከፈ በርበሬ በዐይን ሲታይ መገለጫው ይህ ነው፡፡

ምስል ሁለት:-

(ከላይ ያለው ምስል በጣም ወዛም የሚያምር ቀለም ያለው ነው፡፡ እራሱ ተሰንጥቆ ሲታይ ውስጡ እንደዚህ በሻገታ ልክፍቶች የተበላሸ ነው፡፡)

እነዚህ ልክፍቶች በርበሬው እቤት ከደረሰ በኋላ ቢደርቅ፣ ቢቀመም፣ ቢደለዝ፣ ቢታመስ፣ ቢፈጭ፣ ዱቄቱ ቢቁላላ፣ በውሃ ቢፈላ፣ አይጠፉም፣ አይሞቱም፡፡  

በርበሬው በመጨረሻ ሊሰናዳ ተመዝኖ፣ ተቀንጥሶ፣ ውስጡን ሲከፍቱት ከላይ በምስሉ ላይ እንሚታየው ያለ የተበላሸ በርበሬ ይገለፃል፡፡ ይህን በዐይን የሚታየውን ለቅመን እንለየው እንበል፡፡ ነገሩ የጉድ ነው፡፡ ይህ ሲለቀም የሚቀረው ወይም በዐይን ሲታይ ንፁህ የሚመስለው ከተገዛው መጠን  እስከ ግማሽ ያንሳል፡፡ ለምሳሌ 2ዐ ኪሎ የገዛ ሰው እርጥበቱ ሲደርቅ 1 ኪሎ ይቀንሳል፤ ቆሻሻ ሲለቀም 1 ኪሎ ይቀንሳል፣ እግሩ ሲቀነጠስ 2 ኪሎ ይቀንሳል፣ በመጨረሻም ይህ በልክፍቶቹ የተበላሸው ሲለቀም ከ 4 እስከ 8 ኪሎ ይቀንሳል፡፡

አልፎ አልፎ “በጣም ንፁህ ነው ልክፍት የለውም”  የተባለው እንኳን እስከ 1 ኪሎ የተለከፈ ከውስጡ ነጭ ሊለቀምለት ይችላል፡፡ ይህ ንፁህ የሚባለው መሬት ላይ ከደረቀ በኋላ የትም ቦታ ውሃ ያልተርከፈከፈበት ማለት ነው፡፡ ውሃ ሳያስነኩት ሸማች ዘንድ የደረሰ፡፡  ሆኖም ቀድሞ መሬት ላይ ሲዘረጋ በበሽታው ሊለከፍ ይችላል፡፡  ነገር ግን ውሃ ባለመጨመሩ ምክንያት ልክፍቱ አልተባዛም ማለት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ገበያ ውስጥ ማግኘት ግን ቀላል አይደለም፡፡ እንዲህ ዓይነት በርበሬ ከተዘጋጀ በኋላ እንኳን  በሌላ አገር በላብራቶሪ ሲፈተሽ ብቻ ነው ብክለቱ የሚታየው፡፡ በአውሮፓ ሕብረት እና በእንግሊዝ የሆነው እንዲህ ነው፡፡

የሚያሳዝነው አብዛኞቹ በቤት ሳይቀር ሲያሰናዱት እንጨቱን (የበርበሬ እግር) እና ቆሻሻውን ብቻ ይለቅሙና ይህን ከላይ ቀይ ከውስጥ ነጭ የሆነውን አብረው ያሰናዳሉ፡፡ እነሱ  “ያው የበርበሬ ዓመል ነው ችግር የለውም”  ይላሉ፡፡ ደግሞ “በርበሬ በውድ ዋጋ ገዝተን እንዴት እንጥላለን” ይላሉ፡፡

በእነ ሐብታሙ ፉፋ እና ቀልቤሳ ኡርጋ ከ 12 አመት በፊት በአዲስ አበባ ውስጥ በሽሮ እና በርበሬ ዱቄት ላይ የተደረገው ጥናት አለ፡፡ ሽሮ የተባለው ከበርበሬ ጋር ተመጥኖ የተዘጋጀው ማለት ነው፡፡ በጥቅል ሐሳብ መግለጫው ላይ በመንግስት ባለቤትነት ባሉ መጋዘኖች፣ በችርቻሮ ሱቆች እና ከገበያ ላይ ተወስዶ በተጠናው ናሙናዎች ውስጥ በርበሬ ላይ 13 ከመቶ እና ሽሮ ላይ 8 ከመቶ በዚሁ በአፍላቶክሲን የተበከለ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ እናም በከፍተኛ ሥጋት ውስጥ ያለ ሸቀጥ ስለሆነ ይበልጥ ጥናት ያስፈልገዋል”  ብለው ነበር፡፡ ማጣቀሻ 3

የዚህ ጥናት አቅራቢዎች ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ የሙያቸውን አበርክተው ነበር፡፡ በወቅቱ የሚመለከታቸው አካላት ይህን ጥናት መሠረት አድርገው ሥራ ቢጀምሩ ኖሮ፤

 1. ዛሬ ከአፍላቶክሲንስ የፀዳ በርበሬ እንመገብ ነበር፤
 2. አገሪቱ በርበሬ ወደ ውጪ ገበያ ልካ ገቢ ታገኝበት ነበር፤
 3. የበርበሬ እርሻ በጣም የተስፋፋ ይሆን ነበር፡፡

በርበሬ እና የውጪ ገበያ

በብዙ ድካም እና በብዙ የሙያ ጥራት በርበሬ አዘጋጅተው  ለውጪ ገበያ ለማቅረብ የሞከሩ የባልት ድርጅቶች ነበሩ፡፡ እዚህ ሆነው ምንም ነጭ የሆነ የለውም ብለው በርበሬውን ከገበያ መርጠው፤ ወይም ከራሱ ከገበሬው ማሳ ድረስ ሄደው በውድ ዋጋ ገዝተው፣ በጽዳት አዘጋጅተው ለአውሮፓ ገበያ አቀረቡት፡፡ በእኛ አገር ላብራቶር ሲያስፈትሹት ችግር የለበትም፤ በአውሮፓ ላብራቶሪ ሲፈተሽ “ በአፍላቶክሲን የተበከለ ነው” የሚል ማስረጃ ይጠቀስበታል፡፡ ያ እንዲያ የተደከመበት፣ ስንት ዋጋ የወጣበት በርበሬ እዚያ አውሮፓ አይሸጥም፤ አይለወጥም፡፡  የሚጠብቀው ዕጣ እዚያው አውሮፓ ይደፋል ወይም ወደ አገሩ ይመለሳል፡፡

በካፒታል ጋዜጣ ላይ እንደተዘገበው የዛሬ ሁለት ዓመት ግንቦት ላይ የአውሮፓ ሕብረት የኢትዮጵያን በርበሬ     (1ዐ ሚሊየን ዶላር ዋጋ የነበረውን) አልቀበልም ብሉ መልሶታል፡፡

እንግሊዝ፣ የኢትዮጵያ በርበሬ ተመርምሮ የጥራቱን ደረጃ ጠብቆ እስኪገኝ ድረስ  ወደ አገሯ  እንዳይገባ እገዳ ጥላለች፡፡ ማጣቀሻ 4

ይህ ሁሉ መከራ በርበሬ አምራች ላይ ሲወርድበት ኢትዮጵያ ውስጥ ጠበቅ ያለ መመሪያ አለመውጣቱም የሚገርም ነው፡፡

በርበሬን በሻንጣ ወደ ውጪ መውሰድ

በርበሬን በሕጋዊ ገበያ ወደ ውጪ መሸጥ ብዙ ተግዳሮት ደረሰበት፤ እስከ እገዳ ድረስ፡፡ የአበሻ ሰው ደግሞ ያለ በርበሬ ምግብ አይበላለትም፡፡ አቋራጩ ዘዴ ከነ ድርቆሽ፣ ከነ ቅንጬ ጋር አብሮ በሻንጣ ይዞ መሄደ ሆነ፡፡ ለነገሩ ለበርበሬ በኮንቴነር ተከቶ፣ በመርከብ ውሃ ላይ ከሚጓዝ እንዲህ በሻንጣ ተሽሞንምኖ  በአይሮፕላን ቢሄድ ሳይሻለው አይቀርም፡፡  ይህ በሻንጣ የሚሄደው በርበሬ ከብክለት የፀዳ ነው ማለት አይቻልም፡፡ የተረጋገጠው ጉዳይ ግን በየትም ላብራቶር አይፈተሽም፡፡

ምክር ቢሆን

የበርበሬ ጉዳይ ውስብስብ ሆነ፡፡ ወደ ውጪ ገበያ ሄዶ ዋጋ ማምጣት አልቻለም፡፡ እኛም የትም ያልተመረመረ ግን መበከሉ እየታወቀ እንመገበዋለን፡፡ በዓለም ላይ የተሠሩትን ጥናት ስታነቡ፤ በሥርዓት ደርቆ የተቀመጠ ነገር ግን በጊዜ ሂደት ትንሽ ብክለት የደረሰበት ነው፤ በተራቀቀ ላብራቶሪ ሲመረመር መበከሉን የሚያዩት፡፡  ከቶም የእኛ አገር በርበሬ ደርቆ የተቀመጠ ብቻ ሳይሆን በየደረጃው ውሃ እየተርከፈከፈበት ውሃ ሲጠጣ ከርሞ የሚመጣው ምን ያህል ስጋት እንደሆነ ትገነዘባላችሁ፡፡

(በዚህ ጽሑፌ መጨረሻው ላይ  ከእርጥብ ቃሪያ የተቀመመ ዱቄት እንዴት እንደሚዘጋጅ የፃፍኩት ወድጄ አይደለም/ መላ ያገኘሁ መስልሎኝ ነው፡፡)

አፋጣኙ ምክር፡-

 • በብዙ ጥናት እንደተረጋገጠው በዚህ ጊዜ እና ዘመን በገበያ ላይ ያለው አብዛኛው የእኛ አገር በርበሬ የተለከፈ ነው፡፡ እባካችሁ ተመጋቢዎች በተቻለ መጠን የበርበሬ ፍጆታችሁን ቀንሱ፡፡ ለምሳሌ በቃሪያ ተክታችሁ ሥሩ፡፡ አረንጓዴ ቃሪያን ልክ እንደበርበሬ ቀምሞ ማሰናዳት ይቻላል፡፡ እስቲ ልክ እንደ በርበሬ በቅመም ደልዙት እና አሰናዱት፡፡ አልጫ ቅመም ይሆናል፡፡ ቃሪያ እራሱ የበርበሬ እናት እና አባት አልነበረም እንዴ! ከቃሪያ ጉያ ወጥቶ ሲደርቅ አይደለም እንዴ አፈር ሲነካው በርበሬ የተለከፈው! ከቅላት በቀር ያነሰው ነገር እኮ የለም፡፡ ዋናው ነገር ቃሪያ በዚያ ልክፍት አልተነካም፡፡ እናሳ ምንድነው ችግሩ? ለፋሲካ ዶሮም ቢሆን መሥሪያ ይሆናል፡፡ ዋናው ነገር ጤና ነውና!
 • ለቤት ለማሰናዳት ስትገዙ በጣም ምረጡት፡፡ የተለከፈ የበዛበትን አትግዙ፡፡
 • እቤት ከደረሰ በኋላ በርበሬውን፣ እያንዳንዱን ሰንጥቁ እና እዩት፡፡ አንዳች ነጭ ነገር ያለውን ጣሉት፡፡ ከላይ ለምን የፈለገ ቀይ አይሆንም፣ ለጤናችሁ ባጠቃለይ፣ ለጉበት ደግሞ በተለይ ጠንቅ ስለሆነ አስወግዱት፡፡
 • በቤት የተሰናዳው እንኳ እንዲህ ያለ ሥጋት አለበት፡፡ በሌላ ቦታ የሚሰናዳው ደግሞ ችግሩ የፀና ነው፡፡
 • ምግብ አዘጋጆች እባካችሁ የበርበሬን ፍጆታ ቀንሱ፣ በሌላ ቅመም ተኩት፡፡ ይኸው ነገሩ፡፡

ዋናው ምክር፡-

1ኛ፣ በርበሬ አምራቾች ሲለቅሙት ከቶውንም በርበሬ ልክ እንደ ቡና ትኩረት ተሰጥቶት ከእርሻ ማሳ ገና እንደተለቀመ አፈር ሳይነካው፣ ቆጥ ነገር ተሰርቶለት፣ እዚያ ላይ ተዘርሮ መድረቅ ነው ያለበት፡፡ ከዚያም ምንም እርጥበት ሳይነካው ደረቁን ወደ ንፁህ ማከማቻ ቦታ መድረስ አለበት፡፡ እንደዚህ ሲሆን በበሽታው አይለከፍም፡፡ ለብዙ ወራት (እስከ አንድ አመት ) ምንም ሳይሆን መቆየት ይችላል፡፡

2ኛ፣ አምራቾች፣ አከፋፋዮች፣ ቸርቻሪ ነጋዴዎች እባካችሁ ስለ ህዝብ ጤና ስትሉ ምንም ውሃ አትጨምሩበት፡፡ ውሃ ሳትጨምሩ የሚገባችሁን ክፍያ ጠይቁ፡፡ ለምሳሌ ከእርሻ ማሳ ተነስቶ ስንቱን ገበያ አቋርጦ  ለተጠቃሚ እስኪሸጥ ድረስ ምንም ውሃ ያልነካውን ከፍ ያለ ዋጋ ጠይቁበት፡፡

3ኛ፣ ሸማቾች ጥሬውን በርበሬ በብዛትም ሆነ በአነስተኛ መጠን ስትገዙ የተበላሸውን ለይታችሁ ተመልከቱ፡፡ የተለከፈ ብስባሽ ያለውን አትግዙ፡፡ (የተለከፈውን ተመጋቢ ገዢ ሲያጡ እለት ከፈለጉ ለአገር ውስጥ ወይም ለውጪ ለቀለም ፋብሪካ  ይሽጡት፡፡)

4ኛ፣ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ለአምራቾች፣ ለአከፋፋዮች፣ እና ለሌሎችም በቂ ስልጠና እና ምክር መስጠት አለባቸው፡፡ እንዴት መሰብሰብ እንዳለባቸው፣ እንዴት እንደሚያደርቁት፣ አያያዙን በሙሉ፡ ቀጥሎም ወደ ክትትል እና ቁጥጥር መግባት  አለባቸው፡፡

5ኛ፣ እጅግ ጥናት ቢደረግበት ማድረቂያው እራሱ የተሻሻለ መሆን አለበት፡፡ ከሌላው አገር ቴክኖሎጂውን ማምጣት ያስፈልግ ይሆናል፡፡  መንግስት የጥናቱን ሥራ ቢያግዝ እራሳቸው የገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበራት አስፈላጊውን ማሽን ገዝተው ማቅረብ ይችላሉ፡፡ የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ውስጥ ያለው የቅመማት ባለጉዳይ መሥሪያ ቤት ይህ መልዕክት ይድረሳችሁ፡፡

6ኛ፣ በውጪ አገራት ያላችሁ ባለሐብቶች የተሻሻለውን ዘዴ እና መሳሪያ ወደ አገር በማምጣት አርሶ አደሩን ብትረዱ፤ እራሳችሁም ተጠቃሚ መሆን ትችላላችሁ፡፡

በርበሬን በቤታችሁ እንደዚህ እናሰናዱ፡-

ሀ) የበርበሬ ዱቄት፡-

ይህ እንደ ምሳሌ ነው እንጂ በብዙ ቦታ የተለያየ የቅመማ ዘዴዎች አሉ፡፡

ሀ) የተገዛው በርበሬ ተመርጦ ምንም ነጭ ነገር የሌለው፤ ውሃ ያልነካው ደረቅ በርበሬ ነው እንበል፡፡ አሁን መጥነን እናሰናዳው፡፡ ተለቅሞ፣ እግሩ ተቀንጥሶ፣ ተሰንጥቆ ከውስጥ ነጭ ያለው ካለ ተወግዶ፣ ንፁህ በርበሬ ከደረቀ በኋላ 2 ኪሎ ተሸክሽኮ ቀርቦ ቢሆን፤ ለዚህ የሚበቃው እርጥብና ደረቅ ቅመም ቀጥሎ ይዘጋጃል፡፡

ምስል ሶስት፡-

የተሸከሸከ ደረቅ በርበሬ

ለ) ከእርጥቡ ቅመም ከያንዳንዱ 3ዐዐ ግራም ያህል የተላጠ ነጭ ሽንኩርት፣ ቀይ ሽንኩርት እና ዝንጅብል፣ ከያንዳንዱ 2ዐዐ ግራም ያህል የተሸመጠጠ ሮዝመሪ ቅጠል እና በሶብላ ቅጠል፣ እነዚህ እርጥብ ቅመማት መጀመሪያ ለየብቻ ይወቀጣሉ፡፡ ከዚያም ከተሸከሸው በርበሬ ጋር ይደለዛሉ፡፡ አስተውሉ የእነዚህ እርጥብ ቅመም የደረቅ ክብደት መጠን እስከ 2ዐ በመቶ       ቢሆን ነው፤ ስለዚህ ይህ እርጥብ ቅመም በደረቅ መጠኑ ሲተመን ጠቅላላው ክብደት ሩብ ኪሎ ያህል ይሆናል ማለት ነው፡፡ (25ዐ ግራም)

(ዛሬ ዛሬ መልካሙ ዜና፡- በከተሞች ውስጥ መደለዣ ማሽን አለ፡፡ እቤት በአግባብ ተለቅሞ የተሰናዳውን ደረቅ በርበሬ እና እርጥብ ቅመማት ወስዶ ማስጨፍለቅ ይቀላል፡፡

 መጥፎ ዜና ደግሞ፡- የመደለዣው ዋጋ በርበሬው ይገዛል ነጩ ሳይለቀምለት፣ እግሩ ብቻ ተቀንጥሶ፣ ወድያው ይደልዙታል፡፡ እነዚያ አስጊ የሆኑት  የሻገታ ልክፍቶች (የበሰበሰ በርበሬ ውስጥ ያሉት) አብረው ተጨመሩ፤የጤና ቀውስ መነሻ አብሮት መጣ ማለት ነው፡)

የተለደለዘው አንድ ለሊት ብቻ አድሮ ለፀሐይ ማስጣት እና ማድረቅ ነው፡፡ ምናልባት እነዚያ ልክፍቶች ቢኖሩበት የበለጠ ሳይባዙ ማስጣት ይሻላል፡፡  ተደልዞ በእርጥበቱ በቆየ መጠን እጅግ ይባዛሉ፡፡ በደንብ ደርቆ ሳይፈጭ ጥቂት ወራት ማቆየት ይቻላል፡፡ ተደልዞ ደርቶ የተቀመጠው የሚፈጭ ዕለት ለሰስ ባለ ሙቀት በሸክላ ምጣድ ላይ ይታመሳል፤ ደረቅ ቅመማት ይጨመራሉ፡፡

ሐ) ተበጥሮ የተለቀመ ከደረቁ ከያንዳንዱ 1ዐዐ ግራም ጦስኝ፣ ጥቁር አዝሙድ፣ ነጭ አዝሙድ ድንብላል እና አብሽ፣ እንዲሁም ከያንዳንድ 5ዐ ግራም የኮረሪማ የውስጡ ፍሬ፣ ቅርንፉድ፣ ቀረፋ፣ የጤናዳም ፍሬ፣ እና 3ዐዐ ግራም ጨው ታምሶ ይደባለቅበታል፡፡

መ) በርበሬ ብቻ በሚፈጭበት ወፍጮ ማስፈጨት ነው፡፡ በማግስቱ ዱቄቱ በወንፊት ተነፍቶ ክዳን ባለው በማይዝግ እቃ ይቀመጣል፡፡

የዚህ ዱቄቱ መጠን እስከ 3 ኪሎ ይሆናል፡፡ በርበሬ እና ቅመሙ ጨው ጭምር፤ ምጥኑ  (2፡1) ያህላል፡፡ ሁለት እጅ በርበሬ እና አንድ እጅ ቅመም ማለት ነው፡፡

ለ) ከእርጥብ ቃሪያ የተቀመመ ዱቄት

በዚህ ስሌት እና ጣዕም ከቀይ ቃሪያ ወይም ከአረንጓዴ ቃሪያ፤ ቀይ የበርበሬን ዱቄት ወይም አረንጓዴ የቃሪያ ዱቄት እናዘጋጅ እንበል፡፡ የቃሪያ 8ዐ በመቶ ውሃ ነው ቢባል፣ አንድ ኪሎ ደረቅ በርበሬ ከ5 ኪሎ ቃሪያ ጋር ይመጣጠናል፡፡ ስለዚህ ከላይ እንደተነገረው 3 ኪሎ የተቀመመ ቀይ ዱቄት ወይም አረንጓዴ ዱቄት ከቃሪያ አዘጋጅተን ለማግኘት፣ እስከ 1ዐ ኪሎ ቃሪያ ከተነገረው ቅመም ጋር ማሰናዳት  እና አድርቆ ማስፈጨት ነው፡፡

ይህ ሲሆን የሚገኘው ውጤት ምን ሊሆን ይችላል?

 • በዋናነት ከተባለው አፍላቶክሲን የበሽታ መዘዝ የፀዳ የቃሪያ ቅመም ይገኛል፤
 • ሲቀጥል በሚገርም ሁኔታ ዱቄቱ ከደረቀው በርበሬ የበለጠ ቃና ሊኖረው ይችል ይሆናል፡፡
 •  እስቲ ፈትሹት፡፡ እንዴ! ታድያ በርበሬ ወደን፣ በአፍላቶክሲን ታመን እንዴት ይሆናል!

 ሐ) ሌላው የቃሪያ ድቁስ

በወለጋ- ቆጭቆጫ፣ በወላይታ- ዳጣ የሚባል ከቀይ ወይም አረንጓዴ ቃሪያ ወይም ሚጥሚጣ ተቀምሞ የሚዘጋጅ ግሩም ድቁስ አለ፡፡ ይህ በጣም ጥሩ ቅመም ነው፡፡  በተዘጋጀበት ጊዜ በወቅቱ ከተጠቀሙት ጥሩ ነው፡፡ ለምግብም ጥሩ አባዪ (አፒታይዘር) ነው

መልካም ንባብ!

                                               

ማጣቀሻ 1   Overview of Fungi and Mycotoxin Contamination in Capsicum Pepper and in Its Derivatives    Toxins 2019, 11(1), 27; https://doi.org/10.3390/toxins11010027

ማጣቀሻ 2    Assessment of Hot Peppers for Aflatoxin and Mold Proliferation during Storage  Article (PDF Available)inJournal of food protection 74(5):830-5 · May 2011 with316 Reads  DOI: 10.4315/0362-028X.JFP-10-449 · Source: PubMed

ማጣቀሻ 3    Fufa H1, Urga K.  Fufa H, Urga K. Screening of aflatoxin in Shiro and ground red pepper in Addis Ababa. Ethiop

Med J. 1996 Oct;34(4):243-9. PubMed PMID: 9164040.

US National Library of Medicine     National Institutes of Health

https://www.nih.gov/ማጣቀሻ 4     Capital Newspaper :  EU rejects Ethiopian Red pepper for unsafe levels of toxins –May 8, 2017 | Filed under: News | Posted by: Admin
Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com