ፀጉርን እንዲህ ተንከባከቡ
መግቢያ፡-
ፀጉር እንደ ሌላው የሰውነት ክፍላችን በቂ እንክብካቤ ልናደርግለት ይገባል፡፡ የፀጉር መሳሳት፣ ወዝ ማጣት፣ መሰባበር እና መነቃቀል፣ እንዲሁም የራስ ቆዳ በፎረፎር፣ በተለያዩ የፈንገስ ዓይነት እና በቆረቆር መጎዳት እንዲሁም የራስ ቆዳ መድረቅ ዋና ዋና ችግሮች ናቸው፡፡
ችግሩን ከሚያባብሱት ውስጥ ዋናዎቹ፡- ንፁህ ባልሆነ ውሃ መታጠብ፣ በቧንቧ ውሃ መታጠብ፣ ተስማሚ ባልሆነ ሳሙና መታጠብ፣ ተስማሚ ያልሆነ ቅባት እና ተስማሚ ያልሆነ የፀጉር ቀለም መጠቀም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በተለይ በትልልቅ ከተሞች ውስጥ የቧንቧ ውሃ ፀጉርን እንዴት እንደሚጎዳ ያልተነቃበት ጉዳይ ነው፡፡
ጥቂቶቹ ደግሞ፡- በቂ ንጥረ ምግብ በተለይም በቂ ፕሮቲን፣ ቫይታሚን እና ማዕድናት አለማግኘት እና ፀጉር በፀሐይ ሙቀት በከፍተኛ ሁኔታ ሲጎዳ ነው፡፡
በዚህ ጽሑፍ ላይ ዋናዎቹ የችግሩ አባባሽ ለተባሉት እና ለሌሎችም ይረዳ ዘንድ የሚከተለውን ምክሮች ተመልከቱ፡፡ ከተጠቀሱት ውስጥ የቻሉትን እንደ ችግሩ ስፋት በሳምንት ሁለት ጊዜ፣ በየሳምንቱ ወይም በየሁለት ሳምንቱ ማድገረግ ነው፡፡ የተነገረውን መጠን በማስተዋል ለራስ እንደሚስማማ አድርጎ ማዘጋጀት ነው፡፡
ከመታጠብ በፊት፡- ለሚያስፈልጉ ዝግጅቶች ከተጠቀሱት ውስጥ የቻሉትን ቀድመው ያዘጋጃሉ፤ በሚታጠቡበት፡- ጊዜ ከተነገሩት የቻሉትን ይጠቀማሉ፣ ከታጠቡ በኋላም- ማግኘት የሚችሉትን ያዘጋጃሉ፡፡ ይህን የፀጉር ክብካቤ ዘዴ ለጥቂት ጊዜ ልምምድ ካደረጉ በኋላ ሌሎችን መምከር ይጀምራሉ፡፡
አስተውሉ፡- እዚህ ላይ የተገለፁ አማራጭ ለፀጉር ክብካቤ የሚውሉ ነገሮች ተፈጥሯዊ ስለሆኑ ኬሚካል የላቸውም፡፡ ይህም ሆኖ ሁሉም ነገር ለሁሉም ሰው ላይስማማ ይችላል፡፡ እንዲሁም የሰውነት መቆጣት (አለርጂ) የሚሆኑባችሁን ለዩ፡፡ አብዛኛው እዚህ ላይ የተነገሩት ምክሮች የካበተ የሕዝብ እውቀትን መሠረት ያረጉ ናቸው፡፡
- 1. ከመታጠብ በፊት የሚያስፈልግ ዝግጅት፡-
ፀጉርን ከመታጠብ በፊት ፀጉርን በሚረዱ፣ ከቆዳ ላይ ቅባት፣ ፎረፎር እና ቆሻሻን ሙልጭ አድርገው የሚያነሱ ነገሮች መጠቀም ነው፡፡ ለምሳሌ የተመረጠውን ተፈጥሮአዊ ከተክሎች የሚዘጋጅ መታጠቢያ ወይም ተስማሚ ቅባት ወይም ተስማሚ የፀጉር ዘይት መቀባት፣ የራስ ቅል እና ፀጉርን በደንብ ማሸት፣ መሸፈን እና ለሰዓታት ወይም ለአንድ ለሊት ማሳደር፡፡
ለምሳሌ የራስ ቆዳ እና ፀጉርን ለማፅዳት የሚሆኑ ነገሮችን እንደዚህ ማሰናዳት፣
- 1. 1. የአብሽ ዱቄት፡-
እንደ ፀጉሩ መጠን፣ አንድ የሻይ ማንኪያ ወይም አንድ የሾርባ ማንኪያ የአብሽ ዱቄት፣ አንድ ወይም ሁለት ኩባያ ውሃ ላይ ቀስ በቀስ መነስነስ፣ ዱቄቱ ወደታች ወረዶ ሲወፍር በእጅ ወይም በትንሽ መምቻ (ብሌንደር) መምታት፣ በጣም እንዳይወፍር ንፁህ ውሃ እየጨመሩ መምታት እና እንደ ሊጥ ማዘጋጀት፣
ይህን የራስ ቆዳ እና ፀጉርን አሽቶ መለቅለቅ፡፡ በላስቲክ መሸፍን እና ከላይ በፎጣ መጠቅለል፡፡ ከ 1 እስከ 2 ሰዓት ማቆየት እና መታጠብ፡፡ ተስማሚ ሳሙና ወይም ሻምፖ በጥቂቱ ማድረግ፡፡ ይህ ሲሆን ያልተለመደ ስለሆነ ለሰዉ የሚለቅ አይመስለውም፣ ሽታ ያለው ይመስል ይሆናል፡፡ ፈጽሞ አብሹ ዝልግልዝ እና የሳሙና ዓይነት ፀባይ ስላለው ሙልጭ ብሎ ይለቃል፡፡ ያለውን ቆሻሻ በሙሉ ያስለቅቃል፡፡ ከታጠቡ በኋላ እንኳን የአብሽ ሽታ ምንም የለም፡፡
ለአንድ ቀን ብቻ ጨክነው ይሞክሩት፡፡ ከዚያ እስከዛሬ ባለማወቅዎ ይቆጭዎታል፡፡
ምስል አንድ ለመቀባት የተዘጋጀ የአብሽ ሊጥ
ጥቅሙ፡-
- አብሽ ፀረ ፈንገስ ነው፣ በራስ ቆዳ እና ፀጉር ላይ የሚገኝን ቆሻሻ ያስለቅቃል፡፡
- ለፀጉር ውበት እና ጥንኮሬን ይጨምራል፣
- ተፈጥሯዊ በመሆኑ ለጤና አስተማማኝ ነው፣
- ዋጋው በጣም ቀላል ነው፡፡ (ይችን ታህል የአብሽ ዱቄት ዋጋ ሁለት ብር ቢሆን ነው)፣
- የአገር ምርት ነው፡፡ በውድ ዋጋ ከውጪ የገባ አይደለም፡፡
- 1. 2. የአብሽ ዱቄት እና የረጋ ወተት
ከአንድ ኩባያ የረጋ ወተት ከላይ ያለውን ወፍራሙን እርጎ አንስቶ፣ በላዩ አንድ የሾርባ ማንኪያ የአብሽ ዱቄት መነስነስ እና አብሮ መምታት፣ ያን ደህና አድርጎ የራስ ቆዳ እና ፀጉርን መቀባት፡ እስከ 2 ሰዓት ማቆየት፤ ቀጥሎም መታጠብ፡፡
ጥቅሙ፡-
ወተት የበለጠ ብዙ ንጥረ ምግብ ስላለው፣ ከላይ ለአብሽ ብቻ ከተነገረው የበለጠ ለፀጉር እና ለራስ ቆዳ ጤና እና ውበት ይለግሳል፡፡
1. 3. ቅቤ እና የቀሲል ዱቄት
ቅቤ በብዙ የአገራችን ህዝብ ዘንድ የተለመደ የፀጉር ቅባት ነው፡፡ ለራስ ቆዳ እና ለፀጉር ጤንነት እና ውበት ሲባል ይቀቡታል፡፡ አንድ ትንሽ ወይም ትልቅ ስኒ ለጋ ቅቤ (ከ 5ዐ እስከ 1ዐዐ ግራም የሚደርስ) እራስን ቀብቶ በላስቲክ ሸፍኖ ማሳደር፣ ወይም በአንድ ሾርባ ማንኪያ የቀሲል ዱቄት መለወስ እና የራስ ቆዳ እና ፀጉርን በደንብ መቀባት፡፡ በላስቲክ መሸፈን፤ አንድ ሌት ወይም ለተወሰነ ሰዓታት አቆይቶ መታጠብ ነው፡፡ ቅቤ ብቻውን መቀባት የፈለገ፣ በሚታጠብበት ጊዜ የቀሲል ዱቄቱን በውሃ ለውሶ መቀባት ይችላል፡፡
ጥቅሙ፡-
- ቅቤም ሆነ ቀሲል ለቆዳ እና ለፀጉር ዘመናትን ያስቆጠሩ መድኃኒት ናቸው፤
- ቅቤው የሚፈለገውን ግልጋሎት ከሰጠ በኋላ ቀሲሉ ያስለቅቀዋል፣ የቅቤው ሽታ ይለቃል፤
ቀሲል ምንድነው?
ቀሲል (በሱማሊኛ) በገበያ ላይ ያለው የዱቄት ምርቱ ስም ሲሆን፤ ዋናው የምርቱ መገኛ ዛፍ ቁርቁራ ነው፡፡ ይህ ዛፍ በሰሜን ጎንደር እና በትግራይ ገባ ይባላል፡፡ ትልቅ የቆላ ዛፍ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቆላ ምድር ሁሉ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ጥቅሙን እጅግ የተረዱት የጅግጅጋ ሰዎች ናቸው፡፡ የቅጠሉ ለጋ እና ጠንካራው ለየብቻ ተሰብስቦ ይደርቃል፡፡ እዚያው ጅግጅጋ በተዘጋጀለት ልዩ ወፍጮ ይፈጫል፡፡ በኩንታል እየተሞላ ለአገር ውስጥ ገበያ ተጭኖ ይጓጓዛል፡፡ እነሆ የቀሲል ዱቄት በሚል ስያሜ ለመላ ኢትዮጵያ የሚዳረሰው ከዚህ ነው፡፡ ስንት የሚገርም ነገር አለ፡፡ አዳማ ከተማ ፖስታ ቤት ፊት ለፊት ትልቅ የቁርቁራ ዛፍ አለ፡፡ ከዛፉ ጥላ ሥር ሆነው ዱቄቱን የሚሸጡ ሴቶች ነበሩ፡፡ አጥብቀው ሲጠይቋቸው ቀሲል “ቁርቁራ” ነው ብለው አይናገሩም፡፡ ለነሱ ቀሲል ከጅግጅጋ ብቻ የሚመጣ የተለየ ዱቄት ነው፤ እንጂ ጥላ ሆኗቸው ከአጠገባቸው ያለው ዛፍ አይደለም፡፡
- 1. 4. የቁልቋል በለስ ተክል
የቁልቋል በለስ ተክል የተለየ ቅጠል የለውም፡፡ በተለያየ አካባቢ መብቀል ይችላል፡፡ ጠፍጣፋ ብቃዩ በእሾህ የተሞላ ነው፡፡ ይኸው ጠፍጣፋ ብቃዩን በመትከል ማልማት ይቻላል፡፡
እራስ ላይ ለመቀባት ማዘጋጀት
- አንድ ጠፍጣፋ ቅጠሉን በጥንቃቄ ከላዩ መቁረጥ እና ወደ ቤት መውሰድ፤
- ይህን በእሳት ረመጥ ወይም በጋለ ብረት ምጣድ ላይ እሾኹን መለብለም (ማቃጠል)፤
- ማጠብ እና መሰንጠቅ፣ ከዚያም መከታተፍ፣
- በንፁህ ውሃ ዘፍዝፎ ማሸት፣ ወፈር ያለ ዝልግልግ ውሃ ይወጣዋል፤
- ዝልግልጉን ውሃ ከልጣጩ ለይቶ ማጥለል፣
- በዚህ ውሃ የራስ ቆዳ እና ፀጉርን አሽቶ መቀባ፣ በላስቲክ ሸፍኖ ማቆየት፣
ከሁለት ሰዓት በኋላ መታጠብ፡፡
ምስል ሁለት ቁልቋል በለስ እሾሃሙ ዓይነት
የቁልቋል በለስ ጥቅሙ
- ቆረቆር እና ፈንገስ ያጠፋል፣ ቆሻሻን ከራስ ላይ ያስለቅቃል፡፡
- ለፀጉር ውበት እና ጥንኮሬን ይጨምራል፣
- ተፈጥሯዊ በመሆኑ ለጤና መልካም ነው፤
- ዋጋ አያስወጣም፣ ከጫካ ማምጣት ነው፣ ሲሆን ዘንድሮን በጓሮው የተከለው ሰው ለከርሞ ለጎረቤቱ ሁሉ ይተርፋል፣
- የተፈጥሮ ውጤት ነው፡፡
- 1. 5. የእሬት ተክል
የእሬት ተክል በሌላ የዓለም አገራት ብዙ ክብካቤ ይደረግለታል እና ብዙ ጥቅም ይገኝበታል፡፡ የእኛው ግን በዱር ውስጥ በበጋ ወራት ይደርቃል፣ ክረምት ያለመልማል፣ እንዲሁ ዘመናት አለፉ፡፡ መቸም ወደፊት ሰው ሁሉ ሁለት ተክል ከቤቱ ጊቢ መትክል ያስፈልገዋል፡፡ አንድ የእሬት ተክል እስከ 2ዐዐ ብር ችግኙን መግዛት ይቻላል፡፡ በነፃ ግን ከዱር መሰብሰብ ነው፡፡
እራስ ላይ ለመቀባት ማዘጋጀት
- አንድ ወይም ሁለት የእሬት ጆሮ ( እንደ ቅጠል መሆኑ ነው) ከሥር ያለውን መቁረጥ፣
- በሁለቱም ጎኑ ላይ ጠንካራ እሾህ መሳዩን ቆርጦ ማንሳት፣
- የቀረውን ማጠብ እና መሰንጠቅ፣ ከዚያም መቆራረጥ፣
- በንፁህ ውሃ ዘፍዝፎ ማሸት፣ (አንድ ቀን ወይም ለሊት ማቆየት ይቻላል)
- ሲታሽ እንደ ቁልቋል ወፈር ያለ ዝልግልግ ውሃ ይወጣዋል፤
- ዝልግልጉን ውሃ ከልጣጩ ለይቶ ማጥለል፣
- በዚህ መራራ የሬት ዝልግልግ የራስ ቆዳ እና ፀጉርን አሽቶ መቀባት እና ሸፍኖ ማቆየት፣
ከሁለት ሰዓት በኋላ መታጠብ፡፡
ምስል ሶስት የእሬት ተክል
የእሬት ጥቅሙ
- እሬት ፀረ ቆረቆር እና ፀረ ፈንገስ ነው፡፡ እንዲሁም ቆሻሻን ከራስ ላይ ያስለቅቃል፡፡
- ለፀጉር ውበት እና ጥንኮሬን ይጨምራል፣
- ተፈጥሯዊ በመሆኑ ለጤና መልካም ነው፤
- ዋጋ አያስወጣም፣ ከመስክ ለቅሞ ማምጣት ነው፣
- ሁለት የእሬት ተክል ከጓሮ ያለው ሰው ብዙ ጥቅም ያገኝበታል፣
- የተፈጥሮ ውጤት ነው፡፡
- 1. 6. የተቀቀለ የተልባ ዝልግልግ
ተበጥሮ የተለቀመ የተልባ ዘር፣ አንድ ስኒ በአንድ ሊትር ንፁህ ውሃ መቀቀል፣ በረድ ሲል ማጥለል፡ ሲቀዘቅዝ የራስ ቆዳ እና ፀጉርን በደንብ መለቅለቅ፡፡ በፕላስቲክ ሸፍኖ በፎጣ ጠቅልሎ ማቆየት፡፡ እስከ ሁለት ሰዓት አቆይቶ መታጠብ፡፡
- 1. 7. የተለያዩ የፀጉር ቅባት
- ከ 3- 4 የነጭ ሽንኩረት ፍሬ ወቅጠው ከአንድ ስኒ የኮኮናት ዘይት ጋር ይደባልቁና፣ ያሳድሩት፣ ከዚያም በፀጉር ቆዳ እና ፀጉርን መቀባት፣ ለግማሽ ሰዓት ማቆየት፣ ማጣቀሻ 1
- የጉሎ ዘይት 2ዐ ሚሊ ሊትር (ግማሸ ማለኪያ ያህል) ቀብቶ አንድ ሰዓት ያህል በላስቲክ ሸፍኖ ማቆየት፡
- የወይራ ዘይት እና ጥቁር አዝሙድ ዘይት አንድነት ቀይጦ 2ዐ ሚሊ ሊትር ቀብቶ በላስቲክ ሸፍኖ ሁለት ሰዓት ያህል አቆይቶ መታጠብ፡፡
- የሰሊጥ ዘይት 2ዐ ሚሊ ያህል ቀብቶ በላስቲክ ሸፍኖ፣ ሁለት ሰዓት ያህል አቆይቶ መታጠብ፡፡
- ሌሎችንም ለፀጉር የተመረጡ ቅባትን በእንዲህ ዓይነት መጠቀም፡፡
- 1. 9. ሌሎች አማራጮች
ከእነዚህም ሌላ ያልተጠቀሱ ብዙ ተፈጥሯዊ የሆኑ አማራጮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ልት የሚባለው ተክል ሥሩን ወቅጠው ሲቀቅሉት ልክ እንደ ተልባ ዝልግልግ ውሃ ይወጣዋል፡፡ የአደስ ቅጠል የቅቤን ሽታ ያጠፋል፡፡ የእንቁላል አስኳል እና አቡካዶ ለፀጉር ልስላሴን ይሰጣሉ ወዘተርፈ፡፡ ዋናው ጉዳይ በዚህ ዓይነት በማንበብ፣ በመጠየቅ እና በመጠቀም እራስ እና ፀጉርን መንከባከብ ነው፡፡
- 2. እራስን መታጠብ
ውሃ ማዘጋጀት (ወይም ቀድሞውኑ ማጠራቀም)
በሚታጠቡበት ጊዜ አስቀድመው ፀጉር ለመታጠብ የሚሻለውን ውሃ ማዘጋጀት ነው፡፡
በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ፀጉር ለመታጠብ፣ እራስ እና ፀጉር ለመቀባት የሚዘጋጁ ነገሮችን ለመለወስ፣ እና በመጨረሻም ፀጉርን ለማለቃለቅ ንፁህ ውሃ ተብሎ የተገለፀው፣ ፀጉርን የማይጎዳ ለዚሁ ሲባል የሚዘጋጅ ውሃ ማለት ነው፡፡
- 2. 1. በጣም ተመራጩ ለፀጉር የሚሆነው የተጣራ የዝናብ ውሃ ነው፡፡ ዘወትር በዝናብ ወቅት ቀድቶ ማስቀመጥ እና በአግባብ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ (ያስቀመጡት የዝናብ ውሃ ካለቀ ወይም ከሌለ)
- 2. 2. በማጣሪያ በተጣራ የቧንቧ ውሃ፣ የወንዝ ውሃ፣ የምንጭ ውሃ ወይም የኩሬ ውሃ መታጠብ ነው፡፡ (ይህ ካልሆነ እና አቅሙ ካለ የታሸገ ውሃ መጠቀም ነው) ለፀጉር የሚሆነው ውሃ ሁሌም ቀዝቃዛ ነው፡፡ ማሞቅ አያስፈልግም፡፡
እራስን ወይም ፀጉርን ለመታጠብ የሚሻሉትን የሳሙና፣ ሻምፖ ወይም ኮንዲሽነር ዓይነት እንደተስማሚነቱ መምረጥ ያስፈልጋል፡፡
- 3. ከታጠቡ በኋላ በታከመ ውሃ መለቃለቅ
ታጥበው ሲያበቁ ለዚሁ ከተመረጡት ውስጥ ማዘጋጀት የቻሉትን፤ ለምሳሌ በሳማ ሻይ ውሃ፣ በሮዝመሪ ሻይ ውሃ፣ በሴጅ ሻይ ውሃ፣ በጦስኝ የሻይ ውሃ መለቃለቅ እና ለ 3ዐ ደቂቃ በላስቲክ መሸፈን፤ ከዚያም ማበጠር ነው፡፡ ይህ በመጨረሻ ላይ ለመለቃለቂያ የሚዘጋጀውም ውሃ ከቧንቧ ውሃ የተቀዳ መሆን የለበትም፡፡ የታጠቡበት ውሃ የቧንቧ ውሃ ቢሆን እንኳን ይህ በማጠናቀቂያ ላይ የሚጠቀሙት የዕፀዋት ሻይ የሚዘጋጅበት የተጣራ የዝናብ ውሃ ቢሆን የተሻለ ነው፡፡ የዝናብ ውሃው ከእነዚህ ተክሎች ጋር የተዘጋጀ ሲሆን እጅግ ጥሩ ነው፡፡
ከእነኚህ የተገኙትን አንዱን ለብዙ ጊዜ ወይም እንደተገኙ መጠቀም ይቻላል፡፡ እንዲሁም ሁለቱን ቀይጦ መቀቀልና መጠቀም ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ሳማ እና ጦስኝ፣ ሳማ እና ሮዝመሪ ወይም ሴጅ እና ሮዝመሪን፡፡
የእነዚህ ዕፀዋት ሻይ፣ ለቆዳ ወዝ ይሰጣሉ፣ ለፀጉር ሥሮች እና ለፀጉር ጤናማ እንዲሆኑ ይረዳሉ፡፡ ፈንገስ እና መሰል ነገሮችን በደንብ ያስወግዳሉ፡፡ ለፀጉር ጥንካሬ ይረዳሉ፡፡ ፋርማሲስት እና ባዮኬሚስት የሆኑት የህንዱ ኩንታል ዳስ የሚከተሉትን ምክሮች ይለግሳሉ፡፡ ማጣቀሻ 2
3.1 የሳማ ሻይ ውሃ
እርጥብ የሳማ ቅጠል (5ዐ ግራም ያህል) ወይም ደረቅ ቅጠል (15 ግራም ያህል) በአንድ ሊትር ውሃ ለ 5 ደቂቃ ያህል ማፍላት፡፡ ሲቀዘቅዝ ተጣርቶ በመጨረሻ ላይ ለመለቃለቂያ ይሆናል፡፡
3.2 የጦስኝ ሻይ ውሃ
ደረቅ የጦስኝ ቅጠል (15 ግራም ያህል) በአንድ ሊትር ውሃ ለ 1ዐ ደቂቃ ማፍላት፡፡ ሲቀዘቅዝ ተጣርቶ በመጨረሻ ላይ ለመለቃለቂያ ይሆናል፡፡
3.3 ጥሬ አብሽ ውሃ
ግማሽ ስኒ ጥሬ አብሽ አጥቦ በአንድ ሊትር ንፁህ ውሃ ዘፍዝፎ ማሳደር፣ ከተዘፈዘፈበት ውሃ ጋር ተጨማሪ አንድ ሊትር ውሃ ጨምሮ ለ1ዐ ደቂቃ መቀቀል፡፡ ሲቀዘቅዝ ማጥለል፡፡ በዚህ መራር ውሃ የራስ ቆዳ እና ፀጉርን ማሸት፡፡ በላስቲክ ሸፍኖ ለ3ዐ ደቂቃ ማቆየት፡፡ ከዚያም ማበጠር፤
3.4 የሎሚ ውሃ
እስከ ሁለት የሚደርሱ ሎሚዎችን መጭመቅ፣ የተጨመቀውን ውሃ በሌላ ንፁህ አንድ ሊትር ውሃ ላይ መቀየጥ፡፡ ታጥበው ሲያበቁ በዚህ ውሃ ማሸት እና ለ 3ዐ ደቂቃ በላስቲክ መሸፈን፡፡
3.5 የሮዝመሪ ሻይ ውሃ
እርጥብ የሮዝመሪ ቅጠል (3ዐ ግራም ያህል) ወይም ደረቅ ቅጠል (1ዐ ግራም ያህል) በአንድ ሊትር ውሃ ለ 1ዐ ደቂቃ ማፍላት፡፡ ሲቀዘቅዝ ተጣርቶ በመጨረሻ ላይ ለመለቃለቂያ ይሆናል፡፡
3.6 የሴጅ ሻይ ውሃ
እርጥብ የሴጅ ቅጠል (2ዐ ግራም ያህል) ወይም ደረቅ ቅጠል (1ዐ ግራም ያህል) በአንድ ሊትር ንፁህ ውሃ ለ 1ዐ ደቂቃ ማፍላት፡፡ ሲቀዘቅዝ ተጣርቶ በመጨረሻ ላይ ለመለቃለቂያ ይሆናል፡፡
ሴጅ በገበያ ላይ ብዙም አይገኝም፡፡ ከችግኝ አምራቾች ዘንድ ሊገኝ ይችላል፡፡ በቀላሉ በግንጣዩ የሚለማ ተክል ነው፡፡ ብዙ የጓዳ እና የጤና ጥቅሞች ያሉት ውድ ተክል ነው፡፡ ብዙ ሰው ይህን ተክል ቢያለማ ዋጋ ያገኝበታል፡፡ ስለ ሴጅ ተክል ወደፊት በሰፊው እንመለስበታለን፡፡
- 4. . ተስማሚ ቅባት መምረጥ
ሁልጊዜም ተስማሚ ቅባት መቀባት ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም ዓይነት የፀጉር ቅባት ለሁሉም ሰው ላይስማማ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ብዙ የፀጉር ቅባቶች አሉ፡፡ ከውጪ አገራትም የሚገቡ አሉ፡፡ ከእነዚህ እንደየሰዉ፤ የሚስማማውን መርጦ በአግባቡ ቆዳን እና ፀጉርን መቀባት ነው፡፡
ቸር ሰንብቱ፡፡
- 5. የመረጃ ምንጭ፣
ማጣቀሻ 1 ኩምሳ ከበደ፣ 2ዐዐ9 ዓ.ም; ነጭ ሽንኩርት (አስገራሚው የተፈጥሮ መድኃኒት);ማንኩሳ; አሳታሚ፣ መላ ማተሚያ ድርጅት; አዲስ አበባ፡
ማጣቀሻ 2 Kuntal Das, 2014, Herbal Plants and their Applications in Cosmeceuticals, CBS Publishers & Distributors Pvt Ltd, Indian Binding House Nolda UP, New Delhi, India
I am glad that one of EPRP Pioners (Kflu Tadese) owned thismedia.I hope it will be a great instrument for EPRP and for for it’s members at home and abroad.
1 do you publish English articles?
.2 Where is your email address?
Girma