በከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ላይ የሚፈፀመው ድብደባ ቀጥሏል

Views: 437

-አንድ አሽከርካሪ በአማራ፤ ጨጨሆ አንገቱን ተቆርጦ ተገድሏል

በመንገድ ላይ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ግድያ፣ ድብደባ፣ ዘረፋ እና እገታ እየተፈፀመ ነው ሲል የኢትዮጵያ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማሕበር ገለጸ፡፡
የከባድ መኪና አሽከርካሪዎቹ ማዳበሪያ፣ ስንዴ እና ነዳጅን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶችን ከወደቦች ወደ መሐል አገር በማስገባት ሥራ ላይ የተሠማሩ ሲሆን፣ ‹‹የጦር መሳሪያ ታዘዋውራላችሁ ›› በሚል ጥርጣሬ የየአካባቢው ነዋሪዎች አግተው እንደሚያሰቃዩዋቸው ተነግሯል፡፡ አግተው በግዳጅ ገንዘብ እንደሚቀበሏቸውም አሽከርካሪዎች ገልፀዋል፡፡

አንድ አሽከርካሪ በአማራ ክልል፣ ጨጨሆ መድሃኒዓለም አካባቢ ከሁለት ወራት በፊት ታርዶ መገደሉን አቶ አለማየሁ ቤክሲሳ፤ የኢትዮጵያ ከባድ መኪያ አሽከርካሪዎች ማሕበር አባል በተለይ ለኢትዮ ኦን ላይን ገልፀዋል፡፡ ሟች ዐይኖቹ ተጎልጉለው እንዲወጡ የተደረገ ሲሆን፣ በከባድ ተሽከርካሪው ጭኖት የነበረው ነዳጅ ተዘርፏል ተብሏል፡፡ ይሁን እንጂ ገዳዮቹ እና ዘራፊዎቹ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በሕግ አልተጠየቁም፡፡

በቅርቡ በመተማ፣ ሸኔ አካባቢ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ታፍነው ተገኝተዋል ተብሏል፡፡ በሀረርጌ እና በአፋር፤ ጋላፊ ተመሳሳይ እገታዎች እና አፈናዎች ተስተውለዋል፡፡ በሜንጫና በድንጋይ መደብደባቸውንም ኢትዮ ኦን ላይን በስልክ ያነጋገራቸው አሽከርካሪዎች ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል መንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን በአካባቢው ተገኝቶ ችግሩን መቃኘቱን የገለፁት አሽከርካሪዎቹ፣ በተደጋጋሚ ቅሬታዎቻቸውን ቢያቀርቡም መንግሥት ተገቢውን ምላሽ እንዳልሰጣቸው ገልፀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማሕበር የአመራር አባል በጉዳዩ ላይ ጠቅላይ ሚንስቴር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) አሽከርካሪዎችን ሊያነጋግሩ ይገባል ያሉት አቶ መኮንን ሽብሩ፣ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትም በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com