ዜና

የጆሎንጌ ጤና ዳቦ

Views: 1684

በኢትዮጵያ ከተሞች ዳቦ እንዴት የተወደደ ምግብ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ይህ ገበያውን የሞላው ነጭ የስንዴ ዳቦ ግን ለሁሉም ሰው ይስማማል ወይ ቢባል የሚስማማቸው ብዙዎች ቢሆኑ እንኳን ጥቂቶች አይስማማቸውም፡፡ ነጭ ዳቦ የማይስማማቸው ምን ዓይነት ዳቦ እንመገብ  የሚል ጥያቄ  ይኖራቸዋል፡፡

ነጭ የስንዴ ዳቦ ሲመገቡ የማይስማማቸው ሰዎች (ሌላው ችግር ለጊዜው ይቆይና) ስንዴ ውስጥ የሚገኘው ግሉተን የተባለ ንጥረ ነገር፣ የጤና መታወክ ስለሚያደርስባቸው ነው፡፡ በተለይም ግሉተንን መቋቋም የማይችሉ   (Gluten intolerance)  ሰዎች  ችግሩ ይብስባቸዋል፡፡ ስለሆነም  “ስንዴ አይስማማንም፣ ያቅረናል፣ ያቃጥለናል፣ አንበላም” የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ እንዲያውም ችግሩ ከፍተኛ ደረጃ የሲደርስ ሴኤሊያክስ (Coeliacs)  በሽታ ታማሚ ይሆናሉ፡፡ በዚህ በሴኤሊያክስ በሚባል በሽታ የተያዘ ሰው እስከመጨረሻው  ከግሉተን የፀዳ ምግብ ብቻ መመገብ ግድ ይለዋል፡፡  ግሉተንን የማይቋቋሙ ሰዎችም በሽታው ሴኤሊያክስ ደረጃ እንዳይደርስባቸው ስንዴን መተው ወይ መቀነስ ግድ ይላቸዋል፡፡ ማጣቀሻ አንድ

በዚህ በሽታ እጅግ የሚጎዱት አውሮፓውያን ናቸው፡፡ እነሱ በሴኤሊያክስ በሽታ በመጎዳታቸው የተነሳ፣ ጤፍ ከግሉተን ነፃ በመሆኑ እና ሌላም ብዙ ጠቀሜታ ስለአገኙበት ነው ጤፍ ላይ “የሙጥኝ” ያሉበት፡፡

ይህ ስለሆነ የጤና ዳቦው ገበያ በተለይም በከተሞች ውስጥ ተፈላጊ ነው፡፡ አንድም ጥቂቶች ይህ የተለመደው ነጭ ዳቦ ስለማይስማማቸው፣ ሁለትም የግሉተን ችግር ያለባቸው የውጭ አገር ሰዎች በከተሞች ውስጥ በመኖራቸው ነው፡፡

እነዚህ በከተሞች ዳቦ ጋገራ የተራቀቁ ዳቦ ቤቶች እና ዳቦ ጋጋሪ ባለሙያተኞች የቀረበላቸውን እህል አሽሞንምነው ይጋግሩታል፡፡ ያልቀረበላቸውን እህል ከየት አምጥተው ይጋግሩት ታዲያ? አቅራቢዎችስ ያልታረሰውን ምርት ከወዴት ያመጡታል?

ጤና ዳቦ ለመጋገር ከሚያስችሉ የእህል ዓይነት አንዱ ረይ  (Ray/ (Secale cereal) የተባለ እህል ነው፡፡ ረይ የጥንት እህል ነው፡፡ በደጋ ምድር የአፈር ለምነቱ ባነሰበት፣ ውርጭና ድርቅን በመቋቋምም ይለማል፡፡ ረይ አበቃቀሉ ረዥም ሲሆን የእህሉ ቅርጽ አጃን ይመስላል፡፡ መሬቱ ሲመቸው ወፈር ያለና ረዘም ያለ የአጃ ፍሬ ይመስላል፡፡ በጣም ካልተመቸው ደግሞ ቀጠን አጠር ያለ አጀ ይመስላል፡፡ የእህሉ ቀለም ደብዛዛ ሰማያዊ ነው፡፡ ዳቦውም ለጤና ተስማሚ ቀለሙ ጠይም ያለ ወይም ጥቁር ነው፡፡

ለመሆኑ ሬይ  ምን ዓይነት እህል ነው? የተባለ እንደሆን፣

“በዚህ ዘመን የሬይ  ብዙ ዓይነቴ ያለው በአፍጋኒስታን፣ ኢራን እና መካከለኛ ምስራቅ በተራራማ ምድር ላይ  ነው፡፡ ምናልባትም ሬይ  ከእነዚህ አካባቢ ይሆናል ወደ ኤሽያ፣ ሰሜን አፍሪካ፣ ራሽያ፣ መካከለኛ እና ምዕራብ አውሮፓ የተስፋፋው፡፡ ማላመድ የተጀመረውም ከ3ዐዐዐ እስከ 4ዐዐዐ ዓ.ዓ በፊት ይሆናል፡፡”    ማጣቀሻ 2

 ዊኪፒዲያ የመረጃ መረብ ላይ ስለ ሬይ  እንዲህ ተገልጿል፡፡  “በአገረ አውሮፓ በሰፊው ጥቅም እየሰጠ ያለውን ሬይ  በዓለም ላይ በከፍተኛ መጠን የሚያመርቱትን 7 አገራት እንጥራ የተባለ እንደሆን ራሽያ፣ ፖላንድ፣ ጀርመን፣ ቤላሩስ፣ ዩክሬን፣ ቻይና እና ካናዳ ናቸው፡፡ የሬይ  ዋና የምርት መስመር የሚዘረጋው ከሰሜን ጀርመን ጀምሮ፣ በፖላንድ፣ዩክሬን፣ቤላሩስ፣ ሉቲኒያ እና ላቲቪያን አቋርጦ እስከ መሐከለኛ እና ሰሜን ራሽያ ይደርሳል፡፡  ጠቀሜታውም ለዱቄት ምርት፣ ሬይ  ዳቦ፣ ሬይ  ቢራ፣ ሬይ  ውስኪ፣ ሬይ  ቮድካ፣ እና ለእንስሳት መኖ ይጠቀሙታል፡፡” ማጣቀሻ 3

 ምስል ሁለት ሬይ  (ጆሎንጌ) እህሉ ይህንን ይመስላል

ለመሆኑ ሬይ  እኛ አገር አለ ወይ?

በኢትዮጵያ፣ አርሲ ውስጥ በጭላሎ ተራራ እና ጋለማ ሠንሠለታማ ተራሮች በምዕራቡ ግርጌ በሚገኙ ወረዳዎች (አካባቢዎች)   ከ 5ዐ አመታት በፊት በስዊድኖች ፕሮጀክት መጥቶ የማልማት ሙከራ ተደርጎ ነበር፡፡ ስዊድኖች አምጥተው ለአገሬው አርሶአደር ሲሰጡት የአካባቢው ሰዎች ብዙ የጉዲፈቻ ስም አውጥተውለታል፡፡   እናም በአካባቢው ስመ ብዙ ነው፡፡ ጆሎንጌ፣ ዴራ፣ አጃ ጉራቻ፣አጃ ፋራንጂ፣ ፣ የከብት አጃ፣ ወዘተ ይባላል፡፡ በሁሉም ስሙ ጠርተን ስለማንዘልቅ እንዲያግባባን ጆሎንጌ ወይም ሬይ  እያልን ወጋችንን  እንቀጥል፡፡

ጆሎንጌ እርጥብ ደጋ አካባቢ ይመቸዋል፡፡ ለዘር ለአንድ ሄክታር ከ8ዐ እስከ 1ዐዐ ኪሎ ግራም እህል ይበቃል፡፡  ተዘርቶ እስኪ ሰበሰብ በእርሻ ማሣ ላይ እስከ 5 ወር  ወይም 6 ወር ይቆያል፡፡ አበቃቀሉ ስንዴን ቢመስልም የእህሉ ቁመና ረዥም፡ ከሰው ቁመት በላይ ነው፡፡ ቁመቱ ከ 1፣7ዐ ሳ.ሜትር እስከ 2፣ዐዐ ሜትር ይደርሳል፡፡  አጨዳው በደረሰ ጊዜ ማንም ሰው ቀጥ ብሎ ቆሞ ያጭደዋል፡፡ ገለባውም ብዙ ነው፣ ለመኖ ወይም ለሣር ቤት መሥሪያ ያገለግላል፡፡ ውቅያው በብልሃት ካልሆነ በቀር በቀላሉ ከምርቁ ዓይለይም፡፡ ስለዚህ በጣም እስኪደርቅ በክምር ማቆየት ያስፈልጋል፡፡

ይህ ሬይ  (ጆሎንጌ) የተባለ እህል በዘመኑ በነበረው የስዊድን ፕሮጀክት ለምን እንዳልተስፋፋ አሁን መውቀስ ባይቻልም፣ ለነገሩ

 • አርሶ አደሩ ሬይ ን ትቶ ስንዴን አስፋፍቶ ይሆናል፣
 • ሬይ  ጠየም ያለ ሲሆን ሰንዴ ነጣ ያለ በመሆኑም ገበያው አልፈለገው ይሆናል፣
 • ከስንዴ ወደ ኋላ እስከ 2 ወር ስለሚዘገይና የእርሻ ማሳ ላይ ስለሚቆይ አልፈለጉት ይሆናል፤
 • በቅርቡ ደግሞ ኢርጎት በተባለ በሽታ ተጎድቷል የሚባል  ሐተታ ስለነበር፣

ሆኖም እስከዚህ ዘመን ድረስ በመጠኑ በትንንሽ እርሻዎች ላይ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በገበያም ላይ ተፈላጊ ነበር፡፡ በቆጂ፣ ቀርሣ፣ ሣጉሬ  እና አሰላ ከተሞች የእህል ገበያ ላይ ይሸጣል፡፡

ምስል ሶስት  ከበቆጂ ጨፋ የተገኘ 2ዐዐ8 ዓ.ም

በአካባቢው ያለው ጠቀሜታ

በጣም ተፈላጊነቱ ለጠላ ሲሆን ጠላው እንዴት ነው? የተባለ እንደሆን፤ በጣም ጥሩ ጠላ ይሆናል፡፡ ጠላው ውሃ ያነሣል፣ ይጣፍጣል፡፡ ገብስና ጆሎንጌ ከጥቁር ገብስ ጋር ተቀይጦ ሲጠመቅ እጅግ ጥሩ ነው፡፡  ለካቲካላ አረቄም ይቀጠሙታል፡፡ እንዲሁም በትንሽ መጠን የእንጀራ እህል ላይ ደባልቀው በማስፈጨት ይጠቀሙበት ነበር፡፡

ይህ ከታች ምስሉ የሚታየው አልኮል አልባ ጠላ በተለምዶ “ኬኔቶ” የሚባለው ነው፡፡ የተሰራው ጥቁር ገብስ እና ሬይ ለየብቻ ተቆልቶ፡  በእኩል መጠን ተቀይጦ፣  በውሃ ተቀቀለ፣ ውሃው ተጣርቶ ሲቀዘቅዝ እርሾ፣ ስኳር (ሩብ ኪሎ) እና ማር (1ዐዐ ግራም) ተደርጎበት በ ሁለት ቀን ፈልቶ ለመጠጣት ደረሰ፡፡ የተቆላው በአንድነት አንድ ኪሎ እህል አስር ሊትር መጠጥ ተገኘበት፡፡

ምስል አራት  አልኮል አልባው “የቤት ኬነቶ” የጠላ ዓይነት

ለእንስሳት መኖ

ለእንሰሳት በእርጥብነቱ ሣሩ እየታጨደ ለመኖነት ማብላት ይቻላል፡፡ ሬይ በሳር ደረጃ ሳለ ለመኖ የሚደርሰው ከተዘራ ከ2 እስከ 3 ወር ባለው ጊዜ ነው፡፡ በቂ ርጥበት ካገኘና ከተከለለ (ከተጠበቀ) መልሶም ለሁለተኛ ዙር ይበቅላል፡፡ በክረምት ወይም በበልግ ዝናብ እና በመስኖ መዝራት ይቻላል፡፡

እህሉ ወቅቱን ጠብቆ ከታጨደ በኋላ የሚቀረው ገለባ እና ከተወቃ በኋላ የሚለየው ገለባ ለከብት መኖ ጥሩ ነው፡፡

እራሱ ጥሬው እህል ለእንስሳት መኖ በብረት ምጣድ ላይ በመጠን ታምሶ፣ በወፍጮ ተሸርክቶ፣ ከገለባ ጋር በፈላ ውሃ ተለውሶ ይሰጣል፡፡ ለሚወፍሩ ከብቶች፣ለወተት ላሞች፣ ለተጎዱ ከብቶች  ምርጥ መኖ ነው፡፡

ጆሎንጌን (ሬይ ) ከስንዴ ጋር አነፃፅረን ያየን እንደሆነ፣  

ማወዳደሪያ

ስንዴ

ጆሎንጌ (ሬይ )

የአናቱ ዘለላ እና ፍሬ ብዛት የስንዴ ዘላላ ያጥራል፣ ፍሬው ሲያንስ ከ15 እስከ 25፤ ዘሩ በጣም ሲያፈራ ከ3ዐ እስከ 4ዐ ይሆናል፡፡ ዘለላው ከስንዴ ይበልጣል፣ ማስረጃው የአናቱ ዘለላ ረዥም  እስከ 2ዐ ሣ.ሜ ነው፣፣  አንዱን ዘለላ አሽተን ፍሬውን የቆጠርነው እንደሆነ ከ 7ዐ እስከ 1ዐዐ ዘር ይሆናል፡፡
ግቻው ግቻው ከጆሎንጌ ያንሳል ግቻው ብዙ ነው፣አንዱ ሥር እስከ 15 አገዳ ይይዛል፡፡
ምርታማነት ከ25 እስከ 4ዐ ኩንታል በሄክታር ከ4ዐ እስከ 6ዐ ኩንታል  በሄክታር
ለጤና ተስማሚነተ ግሉተኑ የማይመቻቸውን ይረብሻል ከስንዴ የበለጠ ለጤና ተስማሚ ነው፡፡

ስንዴን በግሉተን ምክንያት የማይመገቡ ይወዱታል፣

ገለባው ለመኖ ገለባው አነስተኛ ነው ከስንዴ ከሚገኘው ሁለት እጥፍ ይሆናል፡፡
ኬሚካል ማዳበሪያ፣ በሄክታር እስከ 2 ኩንታል ያስፈልጋል  ኬሚካል ማዳበሪያ አያሰፈልገውም፣ በጣም የደከመ አፈር ላይ 2ዐ ኪሎ/በሄከታር
ብርዳማ አካባቢ ለስንዴ ምቹ ያልሆኑ ለጆሎንጌ ምርት ማፈሻ ቦታዎች ናቸው
ውርጭን ስንዴ አይቋቋምም ሬይ  ውርጭን ይቋቋማል
ድርቅን ስንዴ አይቋቋምም ሬይ  ድርቅን ይቋቋማል
መሬትን ያክራል መሬትን አያክርም ሬይ  መሬትን ያክራል

ምስል አምስት ሬይ  (ጆሎንጌ የዘለላውን ርዝመት ለማሣየት )

 እህሉ ታርሶ ተመርቶ የመጣ ዘመን ዳቦ ቤቶች እንዴት ይጋግሩታል

በሀገረ ኢንግሊዝ አንድሪው ዋሂትሌይ የተባለ ዳቦ ጋጋሪ አለ፡፡ አንድሪው ዋሂትሌይ “ብሬድ ማተርስ”፣ ብሎ የሰየመውን የዓለም ድንቅ የዳቦ መጽሐፉን ያሣተመው በ2ዐዐ6 እ.ኤ.አ ነበር፡፡ ይህ መጽሐፍ ባለ 372 ገጽ ሲሆን፣ የታተመው ለንደን ነው፡፡ መጽሐፉ በታተመበት ዓመት ዊነር አፍ ቤስት ፉድ ቡክ /Winner of Best Food Book/ ተብሎ በአንድሬ ሲሞን ቡክ አዋርድስ ተሸልሟል፡፡  ዋሂትሌይ  በአገሩ፣ አገር አቀፍ የእውነተኛ ዳቦ ንቅናቄ የሚባል ህዝባዊ ህብረት ከሌሎች ጋር ሆኖ መሥርቷል፡፡ ሬይ  /Rye/  የተባለ እህል  በአውሮፓ እና በራሽያ የታወቀ ምርት፣ የታወቀ ዳቦ ነው ይላል  ዋሂትሌይ ፡፡ ማጣቀሻ 4

አንድሪው ዋሂትሌይ   የሬይ  ዳቦው እንዴት እንደሚጋገር እንደሚከተለው ይነግረናል፡፡

 • እርሾው ከ 3ቀን በፊት ይዘጋጃል፣ ከዚያም በየቀኑ መጠኑ እየጨመረ ቆይቶ፣
 • በ4ኛው ቀን የከረመው እርሾ ጋር የሚፈለገው የሬይ  ዱቄት ይቦካል፣
 • ሊጡን በጣም ላላ አድርጉት፣ ብዙ ውሃ ያነሳልና፣
 • ብዙ ማሸት አያስፈልጋችሁም፣
 • ተቦክቶ ብዙ ሰዓት ቢቆይም ችግር የለውም፣ እንዲያውም ለብዙ ሰዓት በቦካ መጠን

ጥሩ ቃና ይመጣል፤

 •  ሬይ  ብቻውን ሲጋገር ዳቦው የስንዴን ያህል ይነፋል ብላችሁ አትጠብቁ፣
 • ሬይ  ብዙ ውሃ ስለሚወስድ በሚጋገርበት ጊዜ ከስንዴ ይበልጥ ጥቂት ጊዜ  /ለምሳሌ ከ1ዐ እስከ 15 ደቂቃዎች/ መጨመር ያስፈልጋል፡፡

እንግዲህ አንድሪው ዋሂትሌይ  ከነገረን ባልትና በተጨማሪ እኛ እንደባሕላችን ድፎ ዳቦ፣ ሙልሙል የውሃ ዳቦ፣ አንባሻ፣ ኩፍታ፣ ድር.ቦሽ፣ሰተቶ እና የመሣሰሉትን ለመጋገር አንድ  እጅ የተፈተገ ጆሎንጌ እና  አንድ እጅ ስንዴ ቀይጠን፣ ከቅመማ ቅመም ደግሞ ድንብላል፣ ቀረፋ፣ ነጭአዝሙድ፣ጨው ጨምረን ማስፈጨት፡፡ በቤት እርሾ ሊጡ ከተቦካ በኋላ የተለቀመ ጥሬ ጥቁር አዝሙድ ጨምረን መጋገር፡፡ በቃ! ዳቦው የሚታይ ብቻ ሣይሆን የሚበላና የሚስማማ ይሆናል፡፡

ማጠቃለያ

ስለ ሬይ (ጆሎንጌ) እርሻ ልማት እና ምግብ ጉዳይ፣  ሚዛን የሚያነሱ ነገሮች እነዚህ ናቸው፡

 • በአነስተኛ እርሻ መሬት ላይ በቀላሉ ሊለመድ ይችላል፣
 • ሬይ ያለኬሚካል ማዳበሪያ፣ የአፈር ልምላሜ በደከመበት መሬት ላይ መዝራት ይቻላል፣
 • ስንዴ እና ገብስ በውርጭ በሚጠቁበት ቀዝቃዛ ደጋማ አካባቢ ይመረታል፤
 • የዋግ በሽታ፣ ፈንገስ እና ሌሎች ስንዴን በሚያጠቁ በሽታዎች አይጎዳም፣
 • ምግብነቱ ለጤና ተስማሚ ነው፡፡ በተለይም ግሉተን ለማይቋቋሙት፣
 • ለጤና ዳቦ፣ ለባሕላዊ ካቲካላ፣ ለጠላ እና ለእንስሰት መኖ በአገር ጥሩ ጠቀሜታ አለው፤
 • በምርምር ቢደገፍ እና በቂ ምርት ቢገኝ፣ ለቢራ፣ ለቮድካ እና ለመሳሰሉት ሊሆን ይችላል፡፡

የእርሻ ባለሙያዎች እና ተጠቃሚዎች ሊያውቁት የሚገባ

በቅርብ 1ዐ አመታት ወዲህ ጆሎንጌ በፊት ይዘራበት ከነበረበት አካባቢ እርሻው በጣም ተመናምኗል፡፡ አሁን የሚዘራው በጥቂት ቦታዎች ለምሳሌ ጢዮ ወረዳ እና ዲገሉና ጢጆ ወረዳ ከወደ ጭላሎ እና ጋለማ ጥግ ላይ ነው፡፡ እንዲህ የተመናመነበት እና ከገበያ የወጣበት ምክንያት ምንድነው የተባለ እንደሆን ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ጆሉንጌ የተለያየ ሰብብ ደርሶበት ነው፡፡

አንደኛው ሰበብ፣ ኢርጎት የተባለ ፈንገስ ያጠቃዋል፡፡ ይህም በሰው ላይ ኢርጎቲዝም  የተባለ በሽታ ያስከትላል፡፡ ይህ ፈንገስ ጆሎንጌን ሲያጠቃው የእህሉ ዘለላ ወይም ፍሬ ያብጣል፣ ይጠቁራል፣ ረዘም ያለ የአይጥ አር ይመስላል፡፡ በላዩም  ቅባት መሠል ነገር አለው፡፡ አይጣል ነው!  ኢርጎት የተባለ ፈንገስ ገብስን፣ ስንዴን እና ማሽላንም ሊያጠቃ ይችላል፡፡

ሁለተኛው ሰበብ፣ በእርሻ ማሣ ላይ ከ 5 ወራት በላይ መቆየቱ ነው፡፡ ሌላው አዝመራ ተሰብስቦ ጆሎንጌ ይቆያል፡፡ ይህም ከብቶች ያጠፉታል፡፡ ከጎረቤት ጋር ንትርክ ውስጥ መግባት ይመጣል፡፡

ሶስተኛው ሰበብ፣ በቀላሉ አይወቃም፡፡ ወይም እንደ ስንዴ እንደታጨደ ወዲያው አይወቃም፡፡ ለመውቃት ጊዜ ይፈልጋል፡፡

አራተኛው ሰበብ፣ ይኸው እንደዛሬ በዓለም ገበያ ላይ ውድ መሆኑን አልሰማንም፡፡ አውሮፓውያን እንደሚፈልጉት አላወቅንም ነበር፡፡ ምርጥ ቮድካ፣ ምርጥ ውስኪ፣ ምርጥ ቢራ፣ መሆኑን መረጃ አልነበረንም፡፡

ለተነሱት ችግሮች የመፍትሔ ሐሣብ እንጠቁማችሁ፡፡

በደጋ አካባቢ ያሉ ስንዴን ውርጭ የሚጎዳባቸው የአነስተኛ እርሻ ባለቤቶች ጆሎንጌን (ሬይን) በትንሹ ለምሳሌ ግማሽ ጥማድ  መሬት ላይ ቢያርሱ ከ 5 እስከ 7 ኩንታል ያገኙበታል፡፡ (ለዚህ ከ 8 እስከ 1ዐ ኪሎ ግራም ዘር ይበቃል)

ኢርጎት ፈንገስ ለተባለው መፍትሔው፤ በበሽታ የተያዘውን ማንኛውንም እህል ቢሆን ከመታጨዱ በፊት መልቀም ነው፡፡ ከታጨደም በኋላ ለምግብ ወይም ለዘር ሲፈለግ ሙልጭ አድርጎ ማጠብ ነው፡፡ ጆሎንጌ ብቻ ሣይሆን ለሌላውም እህል ተመሣሣይ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡

የእርሻ ማሣ ላይ የመዘግየቱን ችግር ለመቅረፍ ጎረቤታሞች በአንድ አቅራቢያ ዘርተው መጠበቅ እና መረዳዳት ይችላሉ፡፡ ቀጥሎም አጭደው፣ ከምረው ማቆየት እና ሌላውን አዝመራ ከሰበሰቡ በኋላ መውቃት፤ ወይም በየጊዜው የሚቀርቡትን የመውቅያ ማሽን ቴክኖሎጂ በግብርና ጽ/ቤት እና በማህበራት በኩል ማፈላለግ ይችላሉ፡፡  እንዲያውም በቅርብ ዘመን የእህል ክምር እየተበተነ የሚወቁ ቀላል ማሽኖች  እየተሰሩ ናቸው፡፡ ከምሮ አቆይቶ በነዚህ መውቃት ይቻላል፡፡

ለምግብነት አጥቦ፣ ፈትጎ፣ ብቻውን፣ ከስንዴ ጋር፣ ከሌሎች የእህል፣ የጥራጥሬ ወይም የሥራሥር ምርቶች ጋር አመጣጥኖ አስፈጭቶ መመገብ ይቻላል፡፡

 

 

ማጣቀሻ

ማጣቀሻ 1   በቀለች ቶላ. 2ዐዐ8 ዓ.ም ጤፍ የኛ በረካ ከአጃቢዎቹ ጋር፣ አርትስቲክ ማ.ድ አዲስ አበባ

ማጣቀሻ 2     Brink, M., 2006. Secale cereale L. In: Brink, M. & Belay, G. (Editors). PROTA

(Plant Resources   of Tropical Africa / Ressources végétales de l’Afrique tropicale),

Wageningen, Netherlands.

ማጣቀሻ 3   Wiki pedia the free Encyclopaedia

 ማጣቀሻ 4    Andrew Whitley,2006, BREAD  MATTERS , Why and how to make your own, Fourth

Estate, Great Britain,

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com