ዜና

ኢትዮጵያዊያን በአዲሱ ዓመት ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተው እንዲሠሩ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ

Views: 51

ኢትዮጵያዊያን በአዲሱ ዓመት ለሰላም፣ እርቅና ይቅርታ ቅድሚያ ሰጥተው እንዲሠሩ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የክርስትና ሃይማኖት ተቋማት አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የሃይማኖት አባቶቹ በመልዕክታቸው በአዲስ ዓመት ለራሳችን እንዲደረግብን የማንፈልገውን በሌሎች ላይ ባለማድረግ ለሰላምና እርቅ መሥራት ይገባል ነው ያሉት፡፡
አዲሱ ዓመት የአንድነት፣ የይቅርታና የምህረት ሰላም የሰፈነበት ዘመን እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
አዲሱን ዓመት ስናከብር የተቸገሩትን በመርዳት መሆን እንዳለበት መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅድስ አቡነ ማቲያስ፤ አዲሱ ዓመት የሰላምና የአንድነት እንዲሆን ተመኝተዋል።
በዚህም ኢትዮጵያዊያን ለሰላምና እርቅ ቅድሚያ ሰጥተው ችግሮችን በውይይትና ምክክር እንዲፈቱም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ በበኩላቸው አዲሱ ዓመት ለምስጋናና ለንስሃ የምንተጋበት፣ ከስሜታዊነት ይልቅ አዕምሯዊ ስክነትን የምንመርጥበት መሆን አለበት ብለዋል።
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ሁሉም ወገኖች ለዕርቅና ለውይይት ዝግጁ እንዲሆኑም ነው ጥሪ ያቀረቡት።
ምዕመናንም በፆምና በጸሎት እንዲተጉና የአዲስ ዓመት በዓልን በመተጋገዝና በመረዳዳት እንዲያሳልፉ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ጸሐፊ ቄስ ደረጀ ጀምበሩ፤ አዲሱ ዓመት ከእርስ በርስ መፈራረጅ በመራቅ በቅን ልቦና ለጋራ ዕድገትና ሰላም የምንተጋበት እንዲሆን ተናግረዋል።
በዚህም ከተዛቡ መረጃዎች መራቅ በአዲሱ ዓመት አዲስ አስተሳስብ ሰንቅን ልንራመድ ይገባል ብለዋል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት አብያተ ክርስትያናት ህብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ መጭው ዘመን ከግጭት አዙሪት ወጥተን ሰላም የሰፈነበትና አለመግባባቶች የረገቡበት እንዲሆን ተመኝተዋል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *