ዜና

በድጋሚ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ የአሜሪካ ዲፕሎማት ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው አሜሪካ ግጭቱ ወታደራዊ መፍትሄ አይኖረውም ብላለች

Views: 49

በፌደራል መንግስት እና ህወሓት መካከል ያለው ጦርነት ለወራት ጋብ ካለ በኋላ በድጋሚ ተቀስቅሷል

በኢትዮጵያ፤ በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል በድጋሚ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የአሜሪካ ፕሬዝደንት አማካሪ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ኋይት ኃወስ አስታውቋል፡፡

ኋይት ኃውስ በትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ የፕሬዝደንት ባይደን አማካሪ ማይክ ሀመር በዚህ ሳምንት መጨረሻ ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ ብሏል፡፡

ማይክ ሀመር ሁሉም አካላት ሰላም እንዲያወርዱ ጥረት ያደርጋሉ ብሏል መግለጫው፡፡

የአሜሪካ መንግስት የኤርትራን ወደ ግጭት መግባት፣ የህወሐትን ከትግራይ ውጭ ጥቃት መክፈት እና የመንግስትን የአየር ድብደባ እንደምታወግዝ ኋይት ኃውስ  የፕሬስ ሴክሬታሪ ካሪን ዣን ፒየር ገለጹ፡፡

ዣን ፒየር ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ከአምስት ወራት ቆይታ በኋላ ዳግም ላገረሸው ግጭት ምንም አይነት ወታደራዊ መፍትሄ እንደሌለውም ተናግረዋል፡፡

ግጭቱ እንደገና ከመጀመሩ በፊት፣ ለአምስት ወራት የሰብዓዊነት ተብሎ የተደረሰው ስምምነት ተስፋ ሰጭ ነበር ያሉት የዋይት ሀውስ የፕሬስ ሴክሬታሯ ካሪን ዣን ፒየር፤ አሁን በተፈጠረው ወታደራዊ ውጥረት ስበዓዊ እርዳታ መቆሙ ያሳስበናል ብለዋል፡፡

አክለውም “ሁሉም አካላት ራሳቸውን መቆጣጠር አለባቸው ፤ በተለይም ሁሉም ተዋናዮች ለተቸገሩ ወገኖች የደርሰው ሰብዓዊ እርዳታ እና መሰረታዊ አገልግሎት እንደገና እንዲጀመር ውጥረቱን ረገብ እንዲያደርጉት እናሳስባለን” ሲሉ ተደምጠዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ በሰሜን ኢትዮጵያ ዳገም ያገረሸው ግጭት ለመቅረፍ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሀመር በዛሬው እለት ኢትዮጵያ እንደሚገቡ ዣን ፒየር አስታውቀዋል፡፡

ልዩ መልዕክተኛው ሀመር በኢትዮጵያ ቆይታቸው፤ ሁሉም ወገኖች ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን አቁመው ወደ ሰላም ድርድር ዳግም እንዲመጡ ጫና ለመፍጠርና መልዕክት ለማስተላለፍ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ፤ በኢትዮጵያ ዳግም ግጭት መጀመሩ አሜሪካን እንደሚያሳሰባቸው ከሳምንት በፊት መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡

ብሊንከን ፤ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ እንዲሁም በመጨረሻም ግጭቱን በዘላቂነት ለማስቆም ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ በቅርብ ጊዜ የተቀሰቀው ጦርነት፣ ትንኮሳ የተሞላባቸው ትርክቶችና እንዲሁም ዘላቂ የተኩስ አቁም እጦት እየታዬ የነበረውን መሻሻል አደጋ ውስጥ የሚከት መሆኑም ተናግረዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *