“ህወሓት ወረራውን እያስፋፋ መጮኹን ቀጥሎበታል” – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አሸባሪው ህወሓት ወረራውን እያስፋፋ መጮኹን እንደቀጠለበት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የሰጠው መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፦
“ህወሓት ወረራውን እያስፋፋ መጮኹን ቀጥሎበታል” – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
ህወሓት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችን ገፍቶ በየአቅጣጫው በለኮሰው እና ዛሬም እያስፋፋ ባለው እሳት ንጹሓን እየተገደሉ ፣ ሕዝብ እየተፈናቀለ፣ ንብረትም እየወደመ ነው።
አሁን እንደሚታየው አሸባሪውን ህወሓት ከሀገር አጥፊነት ተግባሩ የማስቆም ግዴታ በኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ላይ ወድቋል። ምክንያቱም:-
1. የሽብር ቡድኑ ሰላማችንን እንዳያደፈርስና ሀገራችንን እንዳያፈርስ መከላከል ስለሚገባ፤
2. ህወሓት ወደ ትግራይ የሚላከውን እርዳታ ለተቸገረው ሕዝብ እንዳይደርስ፣ በተቃራኒው እርዳታው ለጦርነት እንዲውል እያደረገ በመሆኑ መንግሥት እርዳታው ለተረጂው ሕዝብ እንዲደርስና ትግራይ ውስጥ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ሕዝቡን ከችግር የመከላከል ግዴታ ስላለበት፤
3. ሕወሓት በእኩይ ተግባሩ ሕዝብን በረሃብ ለመቅጣት አቅዶ ተደጋጋሚ ጦርነት የሚከፍተው በክረምት የግብርና ወቅት በመሆኑ መንግሥት ወረራውን እየተከላከለ ያለው ሕዝብን ከረሃብ የማዳን ግዴታ ስላለበት ጭምር ነው።
ይሁንና በህወሓት የሽብር ቡድን እየደረሱ የሚገኙ ጥፋቶችን ለማስቆም መንግሥት ለሰላማዊ አማራጭ ያደረጋቸው ጥረቶች ሁሉ እየመከኑ ባሉበት ሁኔታ፥ አሸባሪውን ህወሓት መጫን ሲገባቸው “ሁለቱም ወገኖች” በሚል የሚወጡ መግለጫዎች ከእውነታው ያፈነገጡ በመሆናቸው ተቀባይነት የላቸውም።
በመሆኑም ህወሓት ተደጋጋሚ የሰላም አማራጮችን በመግፋት የከፈተው ጥቃት ሀገራችንን እንዳይበትን፥ የመከላከያ ኃይላችን በሁሉም አቅጣጫ የተከፈተበትን ወረራ ከሰላም-ወዳዱ ደጀን ሕዝብ ጋር በመሆን በጽኑ ጀግንነት በመከላከል ላይ ይገኛል።
ነሐሴ 26 ቀን 2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት