ዜና

ሩሲያ ወደ መካከለኛው አውሮፓ ሀገራት ጋዝ መላክ አቋረጠች

Views: 33

ሩሲያ 40 የአውሮፓ ሀገራትን የጋዝ ፍላጎት አቅራቢ ሀገር ናት አሁን ላይ ወደ ጀርመን የሚገባው ነዳጅ ሙሉ ለሙሉ ቆሟል

ሩሲያ ወደ አውሮፓ ጋዝ መላክ አቋረጠች።

የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ስድስት ወራት ያለፈው ሲሆን ጦርነቱ በዓለም ምግብ እና ነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ እንዲመዘገብ ምክንያት ሆኗል።

ይህ በዚህ እንዳለም ጦርነቱ በዓለም ዲፕሎማሲ ላይ የተለያዩ መፋለሶችን ያስከተለ ሲሆን ሀገራት ከትብብር ይልቅ ጎራ ለይተው እንዲሰለፉ እያደረገም ይገኛል።

አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ላይ በተለያየ መንገድ በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ በሩሲያ ላይ ከስድስት ሺህ በላይ ማዕቀቦችን ጥለዋል።

ሩሲያም የአጸፋ እርምጃ በመውሰድ ላይ ስትሆን ማዕቀቡ ለአውሮፓ ሀገራት የምታቀርበውን ጋዝ ሽያጭ እክል አስከትሏል።

ይሄንን ተከትሎም 40 በመቶ ለሚሆኑ የአውሮፓ ሀገራት ነዳጅ ስታቀርብ የነበረችው ሩሲያ በማዕቀቡ ምክንያት ለአውሮፓውያን ነዳጅ መላክ አለመቻሏን በተደጋጋሚ ገልጻለች።

በነዳጅ ዕጥረት እየተፈተነ ያለው የአውሮፓ ህብረትም በሩሲያ ላይ የጣለውን ማእቀብ እስከማላላት ቢደርስም ሞስኮ ነዳጇን በሚፈለገው ልክ አለመላኳን ሮይተርስ ዘግቧል።

የአውሮፓ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆኑት ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ብሪታንያ፣ ቤልጂየም እና ሌሎች ሀገራት በነዳጅ ዕጥረት እየተፈተኑ ናቸው ተብሏል።

እነዚህ ሀገራት ሩሲያ ነዳጇን እንደጦር መሳሪያ እየተጠቀመችበት ነው ሲሉም ሞስኮን ከሰዋል።

ሩሲያ ለጁርመን እና አካባቢው ነዳጅ ስታስተላልፍበት የነበረው ኖርድ ስትሪም የተሰኘው ነዳጅ ማስተላለፊያ ከዛሬ ጀምሮ ለቀጣዮቹ አራት ቀናት በጥገና ምክንያት ነዳጅ መላክ እንደማይችል አስታውቃለች።

ሩሲያ ለተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ነዳጅ መላኳን በተለያዩ ምክንያቶች እየቀነሰች ሲሆን የነዳጅ እጥረት ያጋጠማቸው የአውሮፓ ሀገራት ደግሞ ኢኮኖሚያቸው በዋጋ ግሽበት እየተጎዳ ይገኛል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *