ዜና

ከዩክሬን ለኢትዮጵያ የተላከው ስንዴ ጂቡቲ ገባ

Views: 39

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካኝነት ለኢትዮጵያ ከዩክሬን የተገዛው እህል በዛሬው ዕለት ነሐሴ 24/ 2014 ዓ.ም. ጂቡቲ ገባ።

ይህ የስንዴ ምርት ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አፍሪካ የተላከ እህል መሆኑም ተገልጿል።

ጂቡቲ የደረሰችው መርከብ የሊባኖስ ባንዲራ ያላትና ብሬቭ ኮማንደር የምትሰኝ ሲሆን፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም አማካይነት የተገዛውን 23 ሺህ ቶን ስንዴ ጭነት መያዟ ተነግሯል።

የእህል ጭነቱን ከመርከቧ ላይ በማራገፍ ወደ ኢትዮጵያ ለማድረስ አራት ቀናት ያህል እንደሚወስድ ተነግሯል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ቃል አቀባይ ክሌር ኔቪል ከዚህ ቀም ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ስንዴው ተቋሙ በጦርነት እና በአስከፊ ድርቅ ምክንያት የተጎዱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ለመመገብ የሚያደርገውን ጥረት ይደግፋል።

ከ22 ወራት በፊት በተቀሰቀሰው ደም አፋሳሽ የርስ በርስ ጦርነት ችግር ላይ ያሉ 3.4 ሚሊዮን የሚሆኑ የትግራይ ክልል ነዋሪዎችን እንዲሁም በአፋር እና በአማራ ክልሎች ያሉ ሕዝቦችን ለመርዳት እንደሚውል ክሌር አክለው ገልጸዋል።

በተጨማሪም በሶማሌ ክልል በተከታታይ የዝናብ እጥረት ምክንያት በድርቅ ለተጠቁ 2.4 ሚሊዮን ነዋሪዎች አቅርቦት ይውላል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ ባለፉት አራት አስርት ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ድርቅ በመመታቷ እና በበርካታ ግጭቶች ሳቢያ 20 ሚሊዮን የሚሆነውን ሕዝቧን እርዳታ የሚሻ እንደሆነ የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ አመልክቷል።

በአሁኑ ወቅት ወደ ጂቡቲ የደረሰውም ስንዴ ከሚያስፈልገው ጋር ሲነፃጸር የውቅያኖስ ጠብታ ያህል ነው ተብሏል።

በዛሬው ዕለት ወደ ጂቡቲ የደረሰው የመጀመሪያው ጭነት ሲሆን፣ ከግማሽ ሚሊዮን ቶን በላይ ስንዴ እና ሌሎች የእህል ዓይነቶች በሃምሳ መርከቦች ከዩክሬን ወደቦች መጫናቸውን የተባበሩት መንግሥታት አስታውቋል።

ሐምሌ 15/2014 ዓ.ም. ሩሲያ በዩክሬን ወደቦች ላይ ጥላው የነበረውን እገዳ ያነሳች ሲሆን፣ ይህም መርከቦች በጥቁር ባሕር በኩል ባለው መተላላፊያ እንዲገቡ እና እንዲወጡ አስችሏቸዋል።

ሩሲያ እና ዩክሬን ከተባበሩት መንግሥታት እና ከቱርክ ጋር በጥቁር ባሕር ደኅንነቱ የተጠበቀ መተላለፊያ (ኮሪደር) ለመክፈት ስምምነት ተፈራርመዋል።

ደኅንነቱ የተጠበቀ የባሕር መተላለፊያ (ኮሪደር) ሰኔ 15/2014 ዓ.ም. ከተከፈተ ጀምሮ 560 ሺህ ቶን እህል እና ሌሎች የምግብ ዓይነቶች ከዩክሬን ወደቦች ተልከዋል።

ይህ ጭነት 451 ሺህ 481 ቶን በቆሎ፣ 41 ሺህ 622 ቶን ስንዴ፣ 6 ሺህ ቶን የሱፍ ዘይትን ይዟል።

70 በመቶው የሚሆነው እህልና ምግብ ወደ ቱርክ፣ ኢራን እና ደቡብ ኮሪያም አቅንቷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዩክሬን እህል ዋነኛ ገዢ ሲሆን፤ ይህንንም እህል በረሃብ አደጋ ውስጥ ወደሚገኙ አገሮችም ይልካል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስካሁን 60 ሺህ ቶን ስንዴ ከዩክሬን በመግዛት በችግር ላይ ላሉ አገራት ለመላክ ችያለሁ ብሏል።

የባሕር መተላለፊያውን የሚያስተዳድረው የጋራ ማስተባበሪያ ማዕከል (ጄሲሲ) እንዳስታወቀው 15 የጭነት መርከቦች በአሁኑ ወቅት በጥቁር ባሕር ወደ ዩክሬን ወደቦች በመጓዝ ላይ ናቸው።

የዩክሬን መንግሥት በበኩሉ በወደቦቻቸው 30 መርከቦች ምግብ ለመጫን ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግሯል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ከዩክሬን የሚመጣው እህል መቆም በአህጉሪቱ ለ30 ሚሊዮን ቶን የምግብ እጥረት እና 40 በመቶ የምግብ ዋጋ ንረት ለመፈጠሩ አስተዋፅኦ ማድረጉን ገልጿል።

በናይጄሪያ እንደ ፓስታ እና ዳቦ ያሉ የምግብ ዓይነቶች ዋጋ 50 በመቶ ከፍ እንዲል አድርጓል።

በዓመት ከአንድ ሚሊዮን ቶን በላይ ስንዴ ከዩክሬን በምታስገባው የመን፣ የዱቄት ዋጋ 42 በመቶ፣ ዳቦ 25 በመቶ ጭማሬ አሳይቷል።

ሌላዋ ከፍተኛ የዩክሬን ስንዴ አስመጪ በሆነችው ሶሪያ የዳቦ ዋጋ በእጥፍ ጨምሯል።

የባሕር መተላላፊያ መከፈቱን ተከትሎ የዓለም የምግብ ዋጋ መቀነስ አሳይቷል።

የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) መረጃ እንደሚያሳየው የሐምሌ ወር የዓለም አቀፉ የምግብ ዋጋ 9 በመቶ ቀንሷል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *