ዜና

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ያገረሸው ግጭት በእጅጉ እንዳሳሰበው ገለጸ

Views: 39

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትግራይ ኃይሎች እና በመንግሥት መካከል የተቀሰቀሰው ወታደራዊ ግጭት በእጅጉ እንዳሳሰበው ገለጸ።

ኮሚሽኑ የግጭቱን ማገርሸት በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው ሁሉም ተሳታፊ ኃይሎች ግጭት አቁመው ሰላማዊ መፍትሔ እንዲገኝ ውይይት እንዲጀምሩ ጥሪ አቅርቧል።

ቀደም ባለው ጦርነት በአፋር፣ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች ውስጥ ያሉ ሰላማዊ ሰዎች በቀጥታ ተጠቂ የሆኑባቸው መጠነ ሰፊ የመብት እና የሕግ ጥሰቶች መፈጸማቸውን አስታውሷል።

ስለዚህም በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች በጦርነቱ ተጠቂ የሆኑ የሁሉንም ሰላማዊ ሰዎች ሕይወት፣ አካላዊ እና የሞራል ደኅንነት እንዲሁም ክብራቸውን የመጠበቅ ግዴታቸውን እንዲወጡም ጠይቋል።

ኢሰመኮ እንዳለው በግጭቱ አካባቢዎች ያሉ ሰዎች በጦርነቱ ምክንያት በቅርቡ ካጧቸው ቤተሰቦቻቸው ሐዘን፣ ሰቆቃ  እና የንብረት ውድመት ጉዳት ሳይወጡ፤ እንዲሁም መሠረታዊ አገልግሎቶች ሳያገኙ እና ፍትህና መጽናናትን እየጠበቁ ባሉበት ጊዜ  ለወራት ከቆየ የተኩስ አቁም በኋላ ግጭት መቀስቀሱ በእጅጉ አሳስቦኛል ብሏል።

ኮሚሽኑ በቅርቡ ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በአፋርና በአማራ ክልሎች መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ካጋጠማቸው ሰዎች ጋር ባደረገው ምክክር እንዲሁም፣ በትግራይ ውስጥ ስላለው ሁኔታ በርቀት አደረኩት ባላቸው ክትትሎች ሕዝቡ ባልተቋረጠ የጦርነት ስጋት ውስጥ እንዳለ መረዳቱን ገልጿል።

ነዋሪዎች ጨምረውም በቀዳሚነት ሰላምና ደኅንነት ቀዳሚ ፍላጎታቸው መሆኑን እንዳመለከቱ ኮሚሽኑ ጠቅሷል። “ግጭት ውስጥ ያሉት ወገኖች እንዲሁም ባህላዊ መሪዎች እና ሴቶች በሐቅ ወደ ውይይት እንዲገቡ ከተደረገ” ሰላምና እርቅ ማምጣት ይቻላል ብለው ያምናሉ ብሏል ኢሰመኮ።

ኮሚሽኑ አክሎም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ባህላዊ እና የሃይማኖት መሪዎች፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪካ ኅብረት እና ቀጠናዊ ድርጅቶች ግጭት እንዲቆም የሚያደርጉትን ጥረት የበለጠ እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርቧል።

ለወራት ከዘለቀ ውጥረት በኋላ የሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በእርስ ጦርነት ዳግም መቀስቀሱ የተሰማው የትግራይ ኃይሎች በፌደራል መንግሥት እና በክልል ኃይሎች ጥምር ጥቃት ተከፍቶብኛል ካለ በኋላ ነው።

በዚህም ረቡዕ፣ ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. ንጋት 11 ሰዓት ላይ የፌደራል መንግሥቱ ከአማራ ኃይሎች ጋር በመሆን መጠነ ሰፊ ጥቃት ከፍተውብኛል ብሎ ነበር።

በተመሳሳይ የፌደራሉ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ደግሞ ህወሓት የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ገፍቶ ጦርነቱን ጀምሯል በማለት የትግራይ ኃይሎችን ተጠያቂ አድርጓል።

ሁለቱ ኃይሎች ወደ ጦርነት ተመልሰው መግባታቸውን ተከትሎ ተፋላሚ ወገኖች ከግጭት እንዲታቀቡ የተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ሌሎች ተቋማት እና አገራት ጥሪ አቅርበዋል።

ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበው ጦርነት መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ሲባል የተኩስ አቁም አድርገው በሰሜን ኢትዮጵያ ይካሄድ የነበረው ጦርነት ለአምስት ወራት ያህል ጋብ ብሎ ነበር።

በዚህ ወቅትም በአፍሪካ ኅብረት እና በተለያዩ አገራት አማካይነት ሁለቱም ወገኖች ጦርነቱን በውይይት እንዲቋጩ ጥረት ሲደረግ ቆይቶ ምንም አይነት ተጨባጭ ውጤት ሳያስገኝ ባለፈው ሳምንት ዳግም ጦርነቱ አገርሽቷል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *