ዜና

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ህወሓት ጦርነቱን እንዲያቆም ግፊት እንዲያደርግ በብራሰልስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጠየቀ

Views: 44
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ህወሓት ጦርነቱን እንዲያቆም ግፊት እንዲያደርግ በአውሮፓ ሕብረት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ጽሕፈት ቤትና የኢትዮጵያ ኤምባሲ በቤልጂየም ጠየቀ፡፡
ኤምባሲው በትዊተር ገጹ ባሰፈረው መልዕክት ፥ የኢትዮጵያ መንግስት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ለሰላም ስምምነት ያለማቋረጥ ጥሪ ማቅረቡን አንስቷል፡፡
ሆኖም አሸባሪው ህወሓት ግን ወደ ሌላ የግጭት አዙሪት ውስጥ መግባትን መርጧልም ነው ያለው፡፡
በዚህም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሽብር ቡድኑ ህወሓት የጀመረውን ጦርነት እንዲያቆም ግፊት እንዲያደርግ ኤምባሲው ጠይቋል፡፡
አክሎም የአፍሪካ ህብረት ወደ ሚመራው የሰላም ውይይት እንዲመጣ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አስተዋጽዖ እንዲያደርግም ነው የጠየቀው፡፡
በተጨማሪም በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ፥ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሦስተኛ ዙር ወረራ መፈፀሙን እና እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ሕጻናትን ጨምሮ የትግራይን ሕዝብ በማስገደድ ለጦርነት አሠልፎ በሰው ማዕበል በመዋጋት ሕዝብን ለዕልቂት እየዳረገ እንደሆነ በሱዳን ተቀማጭ ለሆኑ መገናኛ ብዙኃን አስረድተዋል፡፡
ከዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ በተጨማሪ ጐረቤት ሀገራት በኢትየጵያ የሚፈጠሩ ችግሮች ገፈት ቀማሽ እንደመሆናቸው መጠን የአሸባሪ ቡድኑን ድርጊት በማውገዝ ረገድ ግንባር ቀደም ሚና ሊኖራቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።
አምባሳደሩ የኢትዮጵያ መንግስት ፍላጐት ችግሩን በሠላም ውይይት ለመፍታት ቢሆንም፥ ወንጀለኛው ቡድን ከአጥፊ ድርጊቱ የማይቆጠብ ከሆነ ግን የዜጎችን ደኅንነት የማረጋገጥ እንዲሁም የሀገሪቱን ሠላምና አንድነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንደሚወጣም ገልጸዋል።
Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *