ዜና

ዐቃቤ ህግ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ምትኩ ካሳ ላይ ክስ መሰረተ

Views: 44
የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ምትኩ ካሳ እና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ግብራበሮቹ ላይ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ህግ በዛሬው እለት ክስ መስርቷል፡፡
ተከሳሾች 1ኛ አቶ ምትኩ ካሳ ጉትሌ (የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩ) ፣2ኛአቶ አራጋው ለማ (የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የፋይናንስ ዳይሬክተር)፣ 3ኛ አቶ የማነ ወ/ማሪያም (የኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንደ ዴቭሎፕመንት አሶሴሸን ዋና ዳይሬክተር የነበሩ)፣ 4ኛ ዶ/ር ዮናስ ወ/ትንሳይ (የኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንደ ዴቭሎፕመንት አሶሴሸን የኦፕሬሽን ዘርፍ ም/ስራ አስኪያጅ)፣ 5ኛ አቶ ደመውዝ ኃይሉ (ኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንደ ዴቭሎፕመንት አሶሴሸን የፋይናንስ ዘርፍ ም/ስራ አስኪያጅ) ፣6ኛ ወ/ሮ ሶፊያ ጀማል ሰላሙ (የ1ኛ ተከሳሽ የትዳር አጋር) 7ኛ ወ/ሮ ሚልካ ምትኩ ካሳ (የምትኩ ካሳ ልጅ)፣ 8ኛ አቶ ኢያሱ ምትኩ ካሳ (የምትኩ ካሳ ልጅ)፣ 9ኛ አቶ መብራቱ አሰፋ (የኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንደዴቭሎፕመንት አሶሴሸን የመጋዘን ንብረት መዝጋቢ/ሰቶር ኦፊሰር) ፣ 10ኛአቶ ገ/ሚካኤል አብረሓ (የኤልሻዳይ አሶሴሽን ሰቶር ኦፊሰርና የንብረት ክፍል ሰራተኛ) ፣ 11ኛ አቶ ዮሃንስ በላይ ተድላ፣ 12ኛ አቶ ጌቱ አስራት እና 13ኛ ወ/ሮ ሕይወት ከበደ ሲሆኑ የዐቃቤ ህግ የክስ ዝርዝር እንደሚያሳየው 1ኛ ተከሳሽ በቀድሞው የግብርና ሚኒሰቴር የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት እና ምግብ ዋስትና ዘርፍ ሚኒስቴር ድኤታ በአሁኑ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር፤ 3ኛ፣ 4ኛ፣ 5ኛ፣ 9ኛ እና 10ኛ ተከሳሾች ኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንደ ዴቭሎፕመንት አሶሴሸን የተባለ ሀገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆነ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር፣የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ፣ የፋይናንስ ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ፣ የመጋዘን ንብረት መዝጋቢ/ስቶር ኦፊሰር፣ እና የንብረት ክፍል ሰራተኛ፤ 11ኛ ተከሳሽ የኤልሻዳይ ሰራተኛ ሳይሆን ከኮሚሽኑ የሚሰጥ እርዳታ ለመቀበል የኤልሻዳይ ወኪል ሆኖ ሲሰራ፤የማይገባ ጥቅም ለራሳቸው ለማግኘት እንዲሁም ለሌሎች ለማስገኘት በማሰብ በቀድሞ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ግንቦት 11 ቀን 2006 ዓ.ም፣ መጋቢት 22 ቀን 2007 ዓ.ም እና ሐምሌ 01 ቀን 2008 ዓ.ም ለኮሚሽኑ በተፃፉ ደብዳቤዎች ኤልሻዳይ ለሚያቋቁማቸው ዜጎች ድጋፍ እንዲደረግ በተሰጠ መመሪያ እና ከሚኒስቴሮች ምክር ቤት መጋቢት 19 ቀን 2008 ዓ.ም በአፋር ክልል አዋሽ አርባ አከባቢ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን እና በኤልሻዳይ በ3ኛ ዙር ሥልጠና ወስደው በመንግሥት መዋቀር ውስጥ ያልተመደቡ ሠልጣኞች የእርሻ ልማት፣ የእንሰሳት እርባታና ማደለቢያ የስራ ፕሮጅክትን በተመለከተ በቅርብ እንዲከታተሉ በማለት የተሰጠ መመሪያን አላግባብ በመተርጎምና ሽፋን በማድረግ፡- ከ3ኛ እስከ 5ኛ ያሉት ተከሳሾች ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር በመመሳጠር በተለያዩ ጊዜያት በአፋር ክልል ሰርዶ የተቀናጀ የግብርና ማዕከል ፣ በአማራ ክልል ቁጭት ለልማት ማዕከል ፣የደ/ብ/ብ/ሕ/ክልል እና ኤልሻዳይ የጋራ ማሰልጠኛ ማዕከል ፣በጋምቤላ ማሰልጠኛ ማዕከል እና በትግራይ ክልል ቀላሚኖ ማዕከል ተረጂዎች በሌሉበት፣ ካሉም ቁጥሩን እያጋነኑ 1ኛ ተከሳሽ ለሚመራው ኮሚሽን የእርዳታ ጥያቄ እያቀረቡ 1ኛ ተከሳሽም ከላይ በተጠቀሱት ማእከላት ዉስጥ የተረጂዎች ቁጥር በትክክል ስለመኖራቸው የዕርዳታ ጥያቄውን ከመፍቀዱ በፊትም ሆነ ድጋፉ ከተደረገ በኋላ ማረጋገጥ እየተገባው ይህን ሳያደርግ፣ በተጠየቀው መሰረት እንዲሰጥ ከመፍቀዱ በሻገር በራሱ የእጅ ጽሑፍ ሳይቀር “ከኃላፊነት ልነሳ እችላለሁ” በሚል የሚጠይቁትን የእርዳታ አይነትና መጠን አጋኖ በመጻፍ እርዳታውን እንዲሰጥ እየፈቀደ፤ በድምሩ የዋጋ ግምታቸው 799 ሚልየን 542 ሺ 436 ብር ከ84 ሳንቲም የሆነ 601 ሺ 668 ኩንታል ስንዴ፣ 41 ሺ 789 ኩንታል በቆሎ፣ እና 3 ሺ 399 ኩንታል ሩዝ፣ የዋጋ ግምቱ 2 ሚልየን 184 ሺ 344 ብር ከ80 ሳንቲም የሆነ 78 ሺ 320 ሊትር የምግብ ዘይት፣ አማካይ ዋጋቸው ያልታወቀ የተለያየ ዓይነት ለምግብ አገልግሎት የሚውሉ ግብአቶች ማካሮኒ 175 ኩንታል፣ ስኳር 9 ሺ 635 ኩንታል፤ ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች በቁጥር 530 ሺ 488፣ በካሬ 17 ሺ 386፣ በካርቶን 40፣ በጣሳ 404 እና በፓኬት 1 ሺ 800 አላግባብ እንዲወሰድ በማድረግ፤ 3ኛ፣ 9ኛ ፣10ኛ እና 11ኛ ተከሳሾችም ከላይ በተገለጸው አግባብ ከተረከቧቸው የእርዳታ ስንዴ መካከል ለተለያዩ የዱቄት ፋብሪካዎች በሕገ ወጥ መንገድ ግምቱ 107 ሚልየን 830 ሺ 696 ብር ከ32 ሳንቲም በመሸጥ 1ኛ ተከሳሽ በራሱ ስም በብር 8 ሚልየን 300 ሺ ብር በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08፣ ሕጋዊ ባለቤቱ በሆነችው በ6ኛ ተከሳሽ ስም በብር 9 ሚልየን 500 ሺ ብር ከእንይ ሪል ስቴት ኃ/የተ/የግ/ማ እና በሃዋሳ ከተማ በብር 9 ሚልየን 800 ሺ ብር መኖሪያ ቤት በመግዛት ከዚሁም ውስጥ ግለሰቧ ሀዋሳ ከተማ ውስጥ ለገዛችው ቤት 6 ሚልየን 400 ሺ ብር ክፍያ ስንዴውን ከሸጡለት ከኪያ ዱቄት ፋብሪካ ክፍያ የተፈፀመላት በመሆኑ፣ እንዲሁም ሁለት አይቬኮ ትራከር የደረቅ ጭነት ተሸከርካሪዎች ከእነተሳቢዎቻቸው በብር 8 ሚልየን 200 ሺ፣ እና ከፍሬንድሺፕ ቢዝነስ ግሩፕ ኃ/የተ/የግ/ማህበር (ፍሬንድሺፕ ሱፐርማርኬት) የዋጋ ግምታቸው ብር 66 ሺ 740 ብር ከ14 ሳንቲም የሆኑ የቤት እቃዎች እንዲገዛላት በማድረግ በባለቤቱ ስም ሕገ ወጥ ጥቅም ያገኘ በመሆኑ፤ ልጁ የሆነችው 7ኛ ተከሳሽ ብር 1 ሚልየን 300 ሺ በኤልሻዳይ ጥቅም እንዲሰጣት ወይም ደመውዝና ሌሎች ክፍያዎች እንዲከፈላት በማድረግ እና 8ኛ ተከሳሽ ለሆነው ለሌላኛው ልጁም ለቤት ኪራይ ክፍያ የሚዉል 806 ሺ ብር ጥቅም እንዲያገኝ በማድረግ በአጠቃላይ 1ኛ ተከሳሽ የተሰጠውን ሥልጣን በመጣስ በራሱና በቤተሰቦቹ አማካይነት ከኤልሻዳይ ድርጅት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሕገ ወጥ ጥቅም በማግኘቱ ፤እንዲሁም 3ኛ ተከሳሽ የዋጋ ግምታቸው ብር 7 ሚልየን 427 ሺ 500 ብር የሆኑ አራት ተሽከርካሪዎች በ6 ሺ 450 ኩንታል ስንዴ የለወጠ እና በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክ/ከተማ በልጁ በቦኤዝ የማነ ወልደማርያም ስም በ8 ሚልየን 306 ሺ 737 ብር ከ75 ሳንቲም መኖሪያ ቤት በመግዛት የማይገባው ጥቅም ያገኘ በመሆኑ፤ ተከሳሾቹ ሕገ ወጥ ጥቅም ያገኙ ወይም ያስገኙ እና በዚሁም ልክ በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ በመሆኑ፤ ተከሳሾች በዋና እና በልዩ ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት ሥልጣንን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡
በተጨማሪም በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል በ1ኛ ፣ 3ኛ፣ 6ኛ ፣ 7ኛ ፣ 8ኛ ፣ 11ኛ፣ 12ኛ፣ እና 13ኛ ተከሳሾች ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን በብሔራዊ ባንክ ከተወሰነው ወይም ከተፈቀደው መጠን በላይ የውጭ ምንዛሬ ይዞ መገኘት ወንጀልን ጨምሮ 1ኛ ተከሳሽ ላይ 4 ተደራራቢ ክስ በከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ተመስርቶበታል፡፡
ዛሬ /23/12/2014 ዓ.ም / በነበረው ችሎት 1ኛ ፣ 8ኛ ተከሳሾች (አቶ ምትኩ ካሳ እና ልጃቸው) ከሁለት ጠበቆቻቸው ጋር እና 11 ኛ ተከሳሽ ችሎት ቀርበው ማንነታቸው ከተረጋገጠ በኋላ ክሱ ተነቦላቸው 8ኛ ተከሳሽ የተከሰሱበት አንቀፅ ዋስትና የማይከለክላቸው በመሆኑ ጉዳያቸውን ከዉጪ ሆነው እንዲከታተሉ በጠበቆቻቸው የተጠየቀ ሲሆን ዐቃቤ ህግም ተቃዉሞ ባለማቅረቡ ፍ/ቤቱ 8ኛ ተከሳሽ (ኢያሱ ምትኩ ካሳ) በ50 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ ፈቅዶላቸዋል፡፡
1ኛ እና 11 ኛ ተከሳሾች የክስ መቃወሚያቸውን እስከ መስከረም 10 ዐቃቤ ህግ በመቃወሚያው ላይ እስከ መስከረም 20 አስተያየት እንዲሰጥበት በማለት በዚህም ላይ ብይን ለመስጠት እና ሌሎች ተከሳሾች ሲቀርቡ ለማየት ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት ተከሳሾቹ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ እና የፌደራል ፖሊስ ሌሎች ተከሳሾችን አፈላልጎ እንዲያቀርብ ታዟል፡፡(ፍትሕ ሚ/ር)
Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *