ዜና

ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ እንደ ዐባይ ግዝፈቱን ያሳየበት የምረቃ በዓል፡፡ ስለ ክብር ዶክትሬቱ ተደስተናል።

Views: 44

ዛሬ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስድስት አሥርት ዓመታት ዕድሜን ያስቆጠረ ተቋም ነው፡፡ ዛሬ ተማሪዎቹን በድምቀትም አስመርቋል፡፡ አንጋፋ ከሚባሉት የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የኾነው ባህር ዳር ራሱን ከዐባይ ያቆራኘ፤ እንደ ወንዙ ሀገር አቋርጦ ማለፍን የሚሻ፣ እንደ ግዮን ስሙን ዓለም ዘንድ ለማስከበር መትጋትን መርህ ያደረገ ነው፡፡
ከምንም በላይ ግን ዛሬ ደስ አሰኝቶኛል፡፡ በኢትዮጵያ አንድ ሰሞን ምርቃት በመጣ ቁጥር ከ”እንኳን ደስ ያላችሁ” ይልቅ በተሰጠ የክብር ዶክትሬት መጨቃጨቁ በርትቶ ነበር፡፡ እዚያ ሰፈር እከሌ ካገኘ እዚህ ሰፈርስ በሚሉ ፉክክሮች ዩኒቨርሲቲዎች ቅርቤ ላሉት ሲሰጡም አይተናል፡፡
የፖለቲካው መንፈስ ስማቸውን በዓለም አቀፋዊነት የሚጠሩትን ተቋማት ሰፈር ሰፍቶአቸው ሲያሸማቅቁን ታዝበናል፡፡ በአስገራሚ ሁኔታ ከፍ ማለትንና ዓለም አቀፋዊነትን ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰጡ እስኪመስል እነሱ በአካባቢያቸው ታጥረዋል፡፡
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የዚህ ዓመት የክብር ዶክትሬት ከዚህ ቀደም ዜግነት ያልገደበው ዕይታን አሁን ዳግም አስረግጦ ቀጥሏል፡፡ ለአቡነ ኤርሚያስ የተሰጠው ክብር ለደግነት፣ ለወል አባትነትና ለርህራዌ የተለገሰ ነው፡፡ እሳቸውን መሳይ ደጋጎች ሁሉ ዛሬ ከባህር ዳር የክብር ዶክትሬታቸውን የተቀበሉ እንዲመስለኝ አድርጓል፡፡ ደግነት የተደረገላቸውን ሁሉ ያስደሰተው ክብር አስደስቶኛል፡፡
በሌላ በኩል ኮማንደር ደራርቱ የሀገር ምስል ኾና ተቀምጣለች፡፡ ደራርቱ ድል አድርጎ በምንወዳት ሀገር ደስ እንዲለን ማድረግ የቻለች ሰው ብቻ አይደለችም፡፡ ሀገር እንደምንወድ ሁሉ ሀገር መውደድን ጭምር ያሳየች ናት፡፡
በዚህ ጨለማ ወቅት ደራርቱን ምክንያት ዳር አላቆማትም፡፡ በሳቅ ጥላቻን ገፋ፣ በአርቆ አስተዋይነትን ስለ አነባችላት ሀገር ቃትታለች፡፡ ዛሬ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ደራርቱን ብቻ አይደለም ያከበረው፤ የምትወዳትን ሀገር፣ ብዝሃነትን፣ ድል አድራጊነትንና የባንዲራ ፍቅርንም ጭምር ክቡር ዶክተር አድርጓል፡፡
ብዙ ጊዜ የክብር ዶክተርነትን ክብር ለማጎናጸፍ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ውስን የሙያ ዘርፎችን ብቻ ዓይናቸውን ሲተክሉበት አይተናል፡፡ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ያልተገመቱ ሰዎችን ግን ግምታቸው የላቀ፣ ፋይዳቸው የበዛ፣ የሀገር ልጅነታቸው የሚያኮራ ሰዎችን አክብሯል፡፡
ጋምቤላ አይርቅበትም፤ አበርክቶ ይቀርብበታልና፡፡ ጅግጅጋ መሆን ባህር ዳር የመሆን ያህል መቅረቡን በአቶ ሙስጠፌ አይተነዋል፡፡ ቅርብ ስለኾነ መግፋትን አልተካነም አበበ መለሰ ምስክር ነውና፤ ደግሞ ደግነትን ያከብራል ቢኒያም መቄዶንያ ምስክርም ነው፡፡
ማድረግ እንጂ የት መጤነት ቦታ እንደሌለው በተመራማሪው ጃፓናዊ በፕሮፌሰር አሱሺ ሱኔካዋ አሳይቶናል፡፡ በኢትዮጵያ የሳይንስ ትምህርት ለማሳደግ ላበረከቱትስ ለፕሮፌሰር ማርክ ጌንፉንድ የሰጠው ክብር፤ ዛሬም እንደ ወትሮው ከክብሩ ሳይጎድል አክብሯል፡፡ እንደ ዐባይ ስሙን ከፍ ያደረገ የዐባይ ዳር ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ከሰፈሩ የሚነሳ ግን ሰፈሩ ላይ የማይቀር ተብሎ ይኖር ዘንድ ከከፍታው እንዳይወርድ እመኛለሁ፡፡ ለታላላቆቹ ሁለት ሰዎች በዚህ ዓመት የሰጠው ክብርም ከፍታውንም ዐባይነቱንም የዐባይነቱም ያሳየበት ነው፡፡
በዚህ ዓመት ከዩኒቨርሲቲው ለተመረቃችሁ ሁሉ እንኳን ደስ ያላችሁ እያልኩ፤ ፍሬያም ዘመንን እመኛለሁ፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *