ዜና

ምርጫ ቦርድ ‘ኢሠፓ’ በሚል ስም የቀረበውን የፓርቲ ምዝገባ ጥያቄ ውድቅ አደረገ

Views: 50
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “የኢትዮጵያ ሠርቶ አደሮች ፓርቲ (ኢሠፓ)” በሚል ስያሜ የቀረበውን የአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ምዝገባ ጥያቄን ውድቅ አደረገ።
ከ30 ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ብቸኛው ገዢ ፓርቲ የነበረው ኢሠፓ፣ ሕገወጥ ተብሎ ከአገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ከተገለለ በኋላ በስሙ ለመደራጀት ጥያቄ የቀረበው ባለፈው ግንቦት ወር ነበር።
ቦርዱ የኢ.ሕ.ድ.ሪ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ከመሠረቱ ፓርቲ ጋር በተመሳሳይ ስም ለመመዝገብ የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ ያደረገባቸውን ሕጋዊ ምክንያቶች ዘርዝሯል።
ቦርዱ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ መሠረት ለምዝባ ጥያቄ የቀረበበት የፓርቲ ስያሜ ቀድሞ ሕጋዊ ሰውነት ከነበረው ፓርቲ ስያሜ ጋር በመመሳሰል፣ በመራጮች ዘንድ ግርታን የሚፈጥር ሆኖ ከተገኘ ቦርዱ ሊቀበለው አይገባም ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪ ከደርግ ከሥልጣን መወገድ በኋላ የወጣው እና ያልተሻረው ‘ሰላማዊ ሰልፍ እና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ሥነ ሥርዓት አዋጅ’ ኢሠፓ የተባለው ድርጅት ፀረ-ዲሞክራሲ እና ወንጀለኛ ደርጅት ነው በሚል በሕግ አፍርሶታል ብሏል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምዝገባ ጥያቄ የቀረበበት የፓርቲ ስያሜ በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተጽእኖ ፈጣሪ ከነበረ ፓርቲ ጋር ብቻ ሳይሆን የተመሳሰለው፣ “አሁንም ጸንቶ ባለ ሕግ ወንጀለኛ ተብሎ ከተፈረጀ እና ከፈረሰ ድርጅት ጋር ጭምር ነው” ብሏል ቦርዱ በደብዳቤው።
ቦርዱ በዚህ ስያሜ የቀረበለትን የፓርቲ ምዝገባ ጥያቄ ቢቀበል ያልተሻረ ሕግን እንደተሻረ፤ እንዲሁም የፈረሰ ድርጅት ገደቡ ተላልፎ እንደገና እንደተቋቋመ የሚመስል ግንዛቤን የሚፈጥር በመሆኑ እንዳልተቀበለው ገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም የስሙ መመሳሰል በምርጫ ወቅት ምራጮችን ሊያምታት ስለሚችል ቦርዱ በመቋቋሚያ በአዋጁ ቁጥር መሠረት “የኢትዮጵያ ሠርቶ አደሮች ፓርቲ (ኢሠፓ)” በሚል ስያሜ የቀረበለትን የፓርቲ ምዝገባ ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን አስታውቋል።
በቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ተፈርሞ የቦርዱን ውሳኔ በተላለፈበት ደብዳቤ ላይ፤ አስተባባሪዎቹ በሌላ ስያሜ ፓርቲ አቋቋመው የመደራጀት እና የፖለቲካ እንቅስቃሴ የማድረግ መብታቸው የተጠበቀ መሆኑን አስታውሰዋል።
የቀደሞው የኢትዮጵያሠራተኞች ፓርቲ
ከንጉሣዊው ሥርዓት መውደቅ በኋላ በወታደሮች ቁጥጥር ስር የገባው የኢትዮጵያ መንግሥት በእርስ በርስ ጦርነት፣ በድረቅና በከባድ የረሃብ አደጋ ስትናጥ የቆየችውን አገር ለ17 ዓመታት የመራው አስተዳደር በተለያዩ ቅርጾች መቆየቱ ይታወቃል።
ንጉሡ ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ ከተለያዩ የአገሪቱ የጦር ክፍሎች የተዋቀረው ወታደራዊ ኮሚቴ ደርግ፣ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር መስርቶ ከቆየ በኋላ፣ ርዕዮት ዓለሙን ሶሻሊዝም በማድረግ ወደ መደበኛ መዋቅር ለመሸጋገር ዓመታት ወስዶበታል።
በዚህም የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን (ኢሠፓአኮ) በማቋቋም ዝግጅት ሲያደርግ ከቆ በኋላ፣ ከ10ኛው የአብዮት በዓል ጋር በተያያዘ በመስከረም 1977 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲን (ኢሠፓ) የአገሪቱ ብቸኛው ገዢ ፓርቲ ሆኖ ተመስርቶ ነበር።
ፓርቲው አሁን በስደት ላይ በሚገኙት በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም የሚመራ የነበረ ሲሆን፣ በመላው አገሪቱ ሰፊ መዋቅር ዘርግቶ አገሪቱን ሲመራ ቆይቷል።
ነገር ግን ይህ ፓርቲ ከተመሰረተ ከአምስት ዓመት በላይ በሥልጣን ላይ ሳይቆይ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ለዓመታት የዘለቀውን የትጥቅ እንቅስቃሴ ሲያካሄዱ የነበሩት የኤርትራ ነጻነት ግንባር እና ህወሓት በጦር ሜዳው የበላይነት አግኝተው ፓርቲውን ከሥልጣን አስወግደውታል።
ይህንንም ተከትሎ በ17 ዓመቱ የደርግ የሥልጣን ዘመን በተፈጸሙት የመብት ጥሰቶች ምክንያት ኢሠፓ ሕገ-ወጥ ፓርቲ ተብሎ፣ አባላት እና አመራሮቹ ለዓመታት በእስር ቆይተዋል።
አብዛኞቹ የፓርቲው አመራሮችም በእድሜ እና በተለያዩ ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት የተለያዩ ሲሆን፣ ጥቂት የማይባሉት ደግሞ ከ20 ዓመታት እስር በኋላ ነጻ ወጥተው በኢትዮጵያና በተለያዩ አገራት ይገኛሉ።
ከጥቂት ወራት በፊትም አስካሁን ማንነታቸው ይፋ ያልወጣ ግለሰቦች ተሰባስበው ከሦስት አስርት ዓመት በኋላ፣ በኢሠፓ ስም አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ለማቋቋም ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ ማቅረባቸው በአውንታዊ እንዲሁም በአሉታዊ መልኩ መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።
እስካሁም ድረስ ይህንን ጥያቄ ያቀረቡት ግለሰቦች የቀድሞ የፓርቲው አባላት እና አመራሮች መሆን አለመሆናቸው በይፋ የታወቀ ነገር የለም።
Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *