ዜና

ተመድ፤ በኢትዮጵያ የህጻናት ግድያ ጉዳይን ሊመረምር ነው

Views: 86

ተመድ በዩክሬን እና ሞዛምቢክ ተመሳሳይ ምርመራዎችን እንደሚያካሂድ አስታውቋል፡፡

በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት 2021 ባጋጠሙ ግጭቶች 2515 ህጻናት ተገድለዋል ያሉት የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ 5 ሺ 555 ህጻናት መጎዳታቸውን ተናግረዋል፡፡

ህጻናት እና የትጥቅ ግጭቶችን በማስመልከት ዓመታዊ ጉባዔ ተካሂዷል፡፡ በጉባዔው ግጭቶችን አስመልክቶ የቀረበው ሪፖርት በ2021፤ 6310 ህጻናት ለውጊያ ተመልምለዋል ያለ ሲሆን ሌሎች የእገታ፣ ጾታዊ ጥቃትና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ጥሰቶች በህጻናት ላይ መድረሳቸውን አመልክቷል፡፡

ጥሰቶቹ በዋናነት በየመን፣ ሶሪያ፣ አፍጋኒስታን፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሶማሊያ፣ እስራኤል እና በፍልስጤም ህጻናት ላይ መድረሳቸውን ሪፖርቱ ጠቁሟልም፡፡

ጥሰቶቹን አስመልክተው የተናገሩት ጉቴሬዝ የቀጣዩ ዓመት (የ2022) በዩክሬን፣ በኢትዮጵያ እና በሞዛምቢክ ህጻናት ላይ እንደተፈጸሙ የተረጋገጡ የመብት ጥሰቶችን ይጨምራል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ተባብሰው በቀጠሉት ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ሴቶች፣ህጻናትና አረጋውያን በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ መሆናቸው ይነገራል፡፡

በፌዴራሉ መንግስትና በህወሓ መካከል የተካሄደውን ጦርነት ጨምሮ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጸሙት ጥቃቶች በርካታ ህጻናት መገደላቸው፤ ወላጅ አልባ መሆናቸውና ለተለያዩ ጉዳቶች መዳረጋቸውም ነው የሚነገረው፡፡

በቅርቡ በወለጋ የተለያዩ አካባቢዎች በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች በገለልተኛ አካላት እንዲመረመሩ ጥያቄዎች በምክር ቤት ጭምር ሳይቀር መነሳታቸው ይታወሳል፡፡

መንግስት በሽብርተኝነት የተፈረጀውን ኦነግ/ሸኔን ጨምሮ የንጹሃንን ደም ያፈሳሉ በተባሉ አካላት ላይ ዘመቻ መጀመሩን ማስታወቁ የሚዘነጋ አይደለም፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *