ዜና

በፈቃድም ይሁን ያለፈቃድ በአዲስ አበባ እና በዙሪያው በሚገኙ ከተሞች የምትኖሩ የውጭ አገር ዜጎች የተላለፈ ጥብቅ መልዕክት

Views: 71

የኢፌዴሪ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየ መንገድ ገብተው የሚንቀሳቀሱ የውጭ አገር ዜጎችን የመመዝገብና የመቆጣጠር ስልጣን በአዋጅ ቁጥር 354/1995 እና ደንብ ቁጥር 114/1997 የተሰጠው ተቋም ነው።
ስለሆነም፣
• በተለያዩ የቪዛ ዓይነት ወደ ኢትዮጵያ የገባችሁና ቪዛችሁ የሚፀናበት ጊዜ ያለፈበት፤
• የመኖሪያ ፈቃዳችሁ የሚፀናበት ጊዜ ያለፈበት፤
• ምንም አይነት ቪዛም ሆነ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላችሁ፣
• በኢ.ፌ.ዴ. ሪ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት የስደተኝነት ወይም የጥገኝነት ጠያቂ ዕውቅና አግኝታችሁ በከተማ ስደተኝነት በፈቃድም ይሁን ያለፈቃድ በአዲስ አበባ እና በዙሪያው በሚገኙ ከተሞች የምትኖሩ የውጭ አገር ዜጎች በሙሉ፡-
አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ከሐምሌ 11 እስከ 25/2014 ዓ.ም ድረስ ምዝገባ የሚያካሂድ ስለሆነ፤ ዘውትር በስራ ሰዓት ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ በሁሉም ስራ ቀናት ማንነታችሁን የሚገልፅ ሕጋዊ ሠነድ /ፓስፖርት፣ የመኖሪያ ፈቃድ፣ የስደተኛ መታወቂያ ወይም የምዝገባ ማረጋገጫ ሰነድ ፣ የጉዞ እና/ወይም ሌሎች ተያያዥ ሠነዶችን/ ይዛችሁ በአካል በመቅረብ እንድትመዘገቡ አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ጥሪ ያቀርባል፡፡

የምዝገባ ቦታ፦
• በአዲስ አበባ ከተማ፡- በሁሉም የወረዳ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ጽ/ቤቶች እና ፒያሳ በሚገኘው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት፣
• በፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች፡- ገላን፣ ዱከም፣ ለገጣፎ፣ ሱሉልታ፣ ቡራዩ፣ ሆለታ እና ሰበታ
እንዲሁም ቢሾፍቱ ከተማ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ፅ/ቤቶች ናቸው፣
ከላይ በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ውስጥ ባልተመዘገቡ የውጭ አገር ዜጎች ላይ አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ በጥብቅ ያሳስባል፡፡
ማሳሰቢያ፡- የውጭ ዜጐችን በመቅጠር የምታሰሩ፣ በቤታችሁ ተከራይቶ ወይም በጥገኝነት የምታኖሩ ግለሰቦች በተሰጠው ጊዜ ገደብ መመዝገባቸውን እና የምዝገባ ማረጋገጫ መውስዳቸውን እንድታረጋግጡ እናሳስባለን።

ለበለጠ መረጃ ድረገፃችንን ይጎብኙ፡- www.invea.gov.et.
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *