ዜና

በቅርቡ ከወጣው ኮንዶሚኒየም ዕጣ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነገረ

Views: 72

አዲስ አበባ ውስጥ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለማግኘት ለተመዘገቡ ሰዎች በተካሄደው የዕጣ ሂደት ላይ ከታዩ ጉድለቶች ጋር በተያያዘ የከተማው አስተዳደር ኃላፊዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነገረ።

ባለፈው ሳምንት አርብ ሐምሌ 01/2014 ዓ.ም. 25ሺህ 491 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በ20/80 እና የ40/60 የቁጠባ መርሃ ግብር አማካይነት ለባለ ዕድሎች እንዲደርስ ዕጣ መውጣቱ አስታውቆ ነበር።

ይህንን ሂደት ተከትሎም የተለያዩ ወገኖች በዕጣ አወጣጡና በዕጣው ውስጥ በተካተቱ ሰዎች ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችን ሲያነሱ ቆይተው፣ የከተማው አስተዳደር አደረግኩት ባለው ማጣራት ችግሮች እንዳሉ አረጋግጧል።

በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ያሉ ምንጮች ለቢቢሲ እንደገለጹት ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ቢያንስ ሁለት ኃላፊዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።

ሰኞ ዕለት የከተማው አስተዳደር ባወጣው መግለጫ ላይም ቤቶቹን ለማስተላለፍ ከተከናወነው የዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት በኋላ የተለያዩ ጥቆማዎች መቅረባቸውን አመልክቷል።
ይህንንም ተከትሎ በዕጣው ውስጥ በተካተተው መረጃ ላይ በተደረገው ማጣራት “በባንክ የተላከውና ለዕጣ እንዲውል ወደ ኮምፒውተር የተጫነው ዳታ ላይ ልዩነቶች ተግኝተዋል” ሲል ተፈጠረ ያለውን ችግር አመልክቷል።

ጨምሮም ባለፈው አርብ በወጣው የቤቶች ማስተላለፍ የዕታ ሂደት ላይ በተደረገው ማጣራት “ላልቆጠቡ ሰዎች ዕጣ መውጣትን ጨምሮ የተለያዩ የተዓማኒነት ጉድለቶች ታይተዋል” ሲል ገልጿል።

የከተማው አስተዳደር የተዓማኒነት ጉድለቶች ያላቸውን ጉዳዮች ዝርዝር እንዲሁም ጉድለቱ የታየው ምን ያህል ቤቶች ላይ መሆኑን አላሳወቀም።

በዚህም ምክንያት የቤት ማስተላለፍ ሂደቱ ላይ ተከስተዋል የተባሉ “የተዓማኒነት ጉድለቶች” ገለልተኛ በሆኑ በሚመለከታቸው ተቋማት ተጨማሪ የማጣራት ሥራ በመከናወን ላይ ነው ብሏል የከተማው አስተዳደር ባወጣው መግለጫ።

https://bbc.in/3Iz2al3

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *