ዜና

ሾልኮ የወጣው የብልጽግና የድኅረ ጦርነት ሰነድ በጥቂቱ

Views: 33

                                                                      “በሬ ሆይ በሬ ሆይ ሳሩን አየህና፣ ገደሉን ሳታይ እልም ካለው ገደል ወደቅክብን ወይ?ሀገራዊ ብሂል

መግቢያ

የፖለቲካ ቅራኔዎች ወደ ግጭት አድገው ለብዙኃን እልቂትና ለንብረት ውድመት ምክንያት በመሆን በጦርነት ድምዳሜ ሊያገኙ ይችላሉ። ሆኖም ጦርነቱን በድል ያጠናቀቀው ኃይል የድኅረ ጦርነት ሁኔታውን በአግባቡ መምራት ካልቻለ፣ የጦርነቱ ሂደት የሚፈጥረው የፖለቲካና ወታደራዊ፣ ማኅበራዊና ሥነ ልቡናዊ መናጋት የሚወልዳቸው ችግሮች ድሉን ወደ ኋላ የሚቀለብሱና አሸናፊው ወገን ወደ አዲስ ብጥብጥ እንዲገባ የሚያደርጉ የድኅረ ጦርነት ቀውሶች ሊከሰቱ ይችላሉ። ጠላትን በጦር ሜዳ በማሸነፍ ብቻ ዘላቂ ድል ማግኘት አይቻልም። የጦርነት ሜዳ ድል በዘላቂነት እንዲረጋገጥና ወደ ፖለቲካ ድል ከፍ እንዲል፣ ከድል ማግሥት የሚከሠተውን የድኅረ ጦርነት ሁኔታ በአግባቡ መምራትና የተገኘውን ድል ወደ ኋላ ሊመልሱት ከሚችሉ ተግዳሮቶች መጠበቅ ያስፈልጋል። በማያባራ ጦርነት አዙሪት ውስጥ የቆዩ ሀገራት ተሞክሮም ለዚህ እውነታ ጥሩ ማሳያ ይሆናል።

ከዘመናት ትግል በኋላ ነጻነቷን ያገኘችው ኢስት ቲሞር ከነጻነት ማግሥት የነበረውን የድኅረ ጦርነት ሁኔታ በአግባቡ መምራት ባለመቻሏ በመከላከያና በፖሊስ ውስጥ የታቀፉት የቀድሞ ታጋዮቿ ጎራ ለይተው ጦርነት እስከመግጠም የደረሱበት አለመረጋጋት ውስጥ እንድትቆይ አድርጓታል። በላይቤሪያም በእርስ በርሱ ጦርነት የተሳተፉ ታጣቂዎች ይፈጽሟቸው የነበረው ሕገ ወጥ ተግባራት ሀገሪቱ ለተራዘመ የድኅረ ጦርነት አለመረጋጋት እንድትጋለጥ ያደረገ ነበር።

ድኅረ ጦርነት ቀውስ ብዙ መነሻዎች ያሉት ክሥተት ነው። ለድኅረ ጦርነት ቀውስ መነሻ ተደርጎ የሚቀርበው አንዱ ጉዳይ ጦርነት በተከሠተበት ማኅበረሰብ ውስጥ ተለምዷዊ እሴቶች ላይ የሚፈጥረው መሸርሸር ነው። በግጭት ውስጥ ያለፉ ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው በጦርነት ውስጥ የሚፈጸሙ የኃይል እርምጃዎችና ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች፣ በድኅረ ጦርነት ማኅበረሰቡ የኃይል እርምጃና ሕገ ወጥ ተግባራት እንዲለማመድ በማድረግ ከጦርነቱ በኋላ ወንጀል የሚበራከትበትን ማኅበራዊ ዐውድ ይፈጥራሉ። ጦርነት ግድያና ዘረፋን በቀላሉ የሚያይ ማኅበረሰብ ሊፈጥር ይችላል። በዚህ የተነሣ የሕግ የበላይነትን ብቻ በማስፈን የድኅረ ጦርነት መረጋጋትን መፍጠር ፈታኝ ይሆናል።

በጦርነቱ የተሳተፉ ታጣቂዎች ጦርነቱ ተጠናቆ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ቢደረግም ትጥቅ የመፍታት ሂደት በቀላሉ የሚተገበር አይደለም። በመሆኑም፣ ታጥቆ የሚገኘው ኃይል ለሥርዓት አልበኝነት መበራከት ጉልህ ሚና ይጫወታል። ታጣቂው የተሰለፈበት የጦርነት ዓላማ፣ ከጦርነቱ ማለቅ ጋር ቢቋጭም የታጣቂው ፍላጎት ወደ ቁስ መሰብሰብ ሊሸጋገር ይችላል። ከዚህም በላይ ጦርነቱ የሚፈጥረው ውድመት የሚያስከትለው ሥራ አጥነት ሥርዓት አልበኝነቱን ያባብሰዋል።

“በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ በጦርነት የሚከሠተው የዕሴት መሸርሸርና ሥርዓት አልበኝነት ከቁጥጥር ውጭ እንዳይወጣ ለማድረግ የሚያስችሉ የመንግሥት የሕግ ማስከበር ተቋማት በጦርነቱ የመፈራረስ ዕጣ ያጋጥማቸዋል። የመንግሥት ተቋማት መዳከም ከሌሎች አስቻይ ሁኔታዎች ጋር ተደምሮ የድኅረ ጦርነት ሁኔታው ወዳልተረጋጋ ጫፍ እንዲደርስ ይገፋዋል። በተጨማሪም የድኅረ ጦርነት ሁኔታው የሚፈጥረው የጸጥታና የፖለቲካ ክፍተት፣ ጣልቃ በመግባት ጦርነቱን በራሳቸው መንገድ መቅረጽ ለሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

ሁኔታው ከወቅታዊ ሁኔታችን ጋር ተመሳሳይነት አለው። አሸባሪው ጁንታ የከፈተብንን ወረራና ጦርነት በተሳካ ሁኔታ በአጭር ጊዜ እየቀለበስን ነው። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት፣ ከወራሪው አሸባሪ ነጻ በወጡ ቀጣናዎች የአለመረጋጋት ችግር እየተስተዋለ ነው። ይህም እንደ ሀገር ወደ ድኅረ ጦርነት አለመረጋጋት እንዳንገባ ያሠጋል።

በተለይም ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶችን ለሕልውና ዘመቻው በስፋት እንዲሳተፉ ማድረጋችን ይታወቃል። በእነዚህ ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች የሚገኙ አንዳንድ ክፍሎች፣ በጦርነቱ ያስቀመጥናቸውን ፖለቲካዊ ግቦች ወደሚሸረሽሩ ተግባራት የመሠማራት አዝማሚያ እያሳዩ መጥተዋል። ሀገራዊ የክተት ዐዋጁን በመቀላቀል ውሱን የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማጉላት እየተጠቀሙበት ነው። የወገንን የተግባር አንድነት የሚበታትኑ ተግባራት ላይ የመሳተፍ አዝማሚያም እያሳዩ ነው።

“ሳይቃጠል በቅጠል” እንዲሉ የሥርዓት አልበኝነት ዝንባሌዎቹ ጠላቶቻችን በቅንጅት ከከፈቱብን ጦርነት ጋር ተዳብሎ ከጫፍ የደረሰ ድላችንን ወደ ኋላ እንዳይመልሰው የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል። የድኅረ ጦርነት ሁኔታውን በትኩረትና በዲሲፕሊን መምራት ካልቻልን ጦርነት ውስጥ ያስገቡን ጠላቶቻችን በጦር ሜዳ ያጡትን ድል፣ በድኅረ ጦርነት ቀውስን ለማግኘት እንዲሞክሩ ያደርጋቸዋል። በመሆኑም በወገን በኩል በሚፈጠሩ ግድፈቶችና መዛነፎች አማካይነት ወደ ድኅረ ጦርነት ቀውስ እንዳንገባ የጋራ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።

የሰነዱ አንኳር ጉዳይ በጁንታው ላይ የተቀዳጀናቸውንና በቀጣይም የምንቀዳጃቸውን ሁለንተናዊ ድሎችን ጠብቆ በማስፋት ወደ ዘላቂ ሰላም ለመሸጋገር የምናደርገውን ጥረት መዳሰስ ነው። ከዚህ አኳያ ሰነዱ የጦርነት ድሉን ተከትለው የሚመጡ የፖለቲካና የጸጥታ ችግሮችን በመቃኘት፣ ወደ ድኅረ ጦርነት አለመረጋጋት ሊከቱን የሚችሉ መዛነፎችን በመለየት፣ ለችግሮቹ መፍትሔ በማበጀት፤ አርመን ወደ ፊት መቀጠል የሚቻልባቸውን አቅጣጫዎች ይጠቁማል።

 

2 ሀገራዊ የድኅረ ጦርነት ፈተናዎችና አቅጣጫዎች

2.1 የአማራ ክልል ሁኔታ

/ የፖለቲካ ሁኔታ

በፖለቲካው መስክ ሊፈጠሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ጠቅለል አድርገን ስናያቸው በሦስት ፈርጆች ሊሠፍሩ ይችላሉ፤ የድል ሽሚያ ፖለቲካ፣ የይገባኛል ፖለቲካ እና የተከዳን ፖለቲካ ናቸው።

የድል ሽሚያ ፖለቲካ፡ ድሉን ማን አመጣው በሚል አጀንዳ ሕዝቡን የመከፋፈልና የፖለቲካ ተዋሥዖው ባለድሉ እኔ ብቻ ነኝ በሚል እሰጥ አገባ እንዲሞላ የሚያደርግ ነው። ይህ የድል ሽሚያ ፉክክር፣ በዋናነት በክልሉ የጸጥታ ኃይሎችና በፌዴራል ኃይሎች መካከል፣ እንዲሁም በክልሉ ልዩ ልዩ ኃይሎች መካከል፣ እንዲሁም በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች መካከል የሚፈጠር ሊሆን ይችላል። በተለይም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚደረግ ፉክክርና እርስ በርስ መካሰስ፣ በጦርነቱ ውስጥ የነበረን ሚና እየጠቀሱ መወቃቀስ፣ ወዘተ. የክልሉን ፖለቲካና አንድነት አደጋ ውስጥ ሊጥለው ይችላል።

 የይገባኛል ፖለቲካ፡ ከግለሰብ እስከ ቡድን በትግሉ ውስጥ የተሳተፉ ወይም የደገፉ አካላት ስለታገልኩ ልዩ ችሮታ ያስፈልገኛል/ይገባኛል የሚል አጀንዳ ይዘው የሚመጡበት ነው። ይህን ሁኔታ በሁለት መንገድ መመልከት እንችላለን፤ አንደኛ – በመንግሥት ውስጥ፣ ሁለተኛ ከመንግሥት ውጭ። በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የዘመተውና ያልዘመተው አመራር፣ በጉልህ የተሳተፈውና ያልተሳተፈው አመራር፣ ወዘተ. መካከል ውጥረት መከሠቱ አይቀርም። በዘመቻው ጉልህ ተሳትፎ ስላለኝ የተሻለ ቦታ ይገባኛል የሚሉ ድምፆች ቅሬታና የመጠላለፍ አዝማሚያ መፍጠራቸው አይቀርም። በሌላ በኩል ደግሞ ከመንግሥት ውጭ ያሉ አካላት ከዘመቻ መልስ ጥቅም ወይም ሥልጣን ፍለጋ በመንግሥት ላይ ጫና ማሳደራቸው አይቀርም። ጫናው በግለሰብ ወይም በተደራጀ አኳኋን በቡድን ደረጃ ሊከሠት ይችላል። በግለሰብ ደረጃ ከመንግሥት ልዩ ችሮታ የመፈለግና በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ቅድሚያ ለማግኘት መሞከር ሊኖር ይችላል። በቡድን ደረጃ ደግሞ የድል አጥቢያ አርበኝነት አዝማሚያ፣ እኔ ነኝ ባለድሉ ማን ይናገረኛል የሚል ዐመፀኝነት፣ እና የመንግሥትን ሥልጣን የመገዳደር ፍላጎት ሊስተዋል ይችላል።

ይህኛው አዝማሚያ በቀጣይ ለክልሉ ፖለቲካ ዋነኛ ሥጋት ሊሆን የሚችል ነው። በተለይም ይህ የድል አጥቢያ አርበኝነት አዝማሚያ ከአካባቢያዊነት ጋር ከተሰናኘና የአመራሩም በዚያ ተሳታፊ ከሆነ የክልሉን ፖለቲካ ከፍተኛ አደጋ ላይ ሊጥለው እንደሚችል መገመት ይቻላል።

የተከዳን ፖለቲካ፡ የትግራይን ክልል ሙሉ ለሙሉ በመቆጣጠር ድል ይገኛል ብሎ የሚያምን ልሂቅና አክቲቪስቱ፣ ጦርነቱ እነሱ በሚያስቡት መንገድ ባለመጠናቀቁ የፌዴራል መንግሥት ‘ከድቶናል’ የሚል ቅሬታ ሊቀርብ ይችላል። የፌዴራል መንግሥቱ ክህደት ፈጽሞብናል፣ መንግሥት ሌላ ዓላማ አለው፣ ዘመቻ ህብረብሔራዊ አንድነትን ቀደም ብሎ ማድረግ ይቻል ነበር፣ ወዘተ. የሚሉና ጦርነቱ የሚቋጭበትን መንገድ ያለመቀበል አዝማሚያዎች ይኖራሉ።

 

/ የጸጥታ ሁኔታ

በድኅረ ጦርነት ክልሉን ሊፈትኑት ከሚችሉት ዋና ዋና ጉዳዮች አንዱ የሕግ የበላይነት መሸርሸር ነው። ጦርነቱን ተከትሎ ሊፈጠሩ የሚችሉ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎችንና የጸጥታ ችግሮችን በሦስት ከፍለን መመልከት እንችላለን፡- የተለምዷዊ ወንጀሎች መበራከት፣ አጋጣሚውን ለግል ጥቅም የማዋል ፍላጎት፣ እና በትግራይ ክልል ውስጥ በቀል የመፈጸም ፍላጎት ናቸው።

/ ሰብአዊ ሁኔታ

አሸባሪው ሕወሐት ከአማራ ሕዝብ ጋር ሂሳብ አወራርዳለሁ ብሎ የመጣ በመሆኑ በአማራ ክልል አሰቃቂ ሰብአዊ ቀውስ እንዲከሠት አድርጓል። ጭፍጨፋዎች ተፈጽመዋል፤ ሴቶች ተደፍረዋል፤ ሕጻናት ተገድለዋል፤ ሕጻናት እናቶቻቸው ሲደፈሩና አባቶቻቸው ሲገደሉ አይተዋል፤ ሕዝብ ተፈናቅሏል፣ ሰቆቃዎች ተፈጽመዋል። አሁን የሚስተዋለው ሰብአዊ ቀውስም በጊዜ ሂደት የመንግሥትን ዐቅም እየተፈታተነና የችግር ተጋላጮች ቁጥርም እየጨመረ እንደሚመጣ መገመት ይቻላል።

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com