ዜና

የኢትዮጵያ መንግሥት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በሥነ ምግባር ጥሰት እንዲጠየቁለት ማመልከቻ አስገባ

Views: 40

የኢትዮጵያ መንግሥት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር በሆኑት ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ላይ የሞራል፣ የሕግ እና የሙያዊ ሥነ ምግባር ጥያቄዎች እንዳሉት አመለከተ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዓለም ጤና ድርጅት የበላይ ጠባቂ ቦርድ በላከው የቅሬታ ማመልከቻ ላይ እንዳለው በዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የተነሳ የድርጅቱ የገለልተኝነት መርህ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል ብሏል።

ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን ግዙፉን የኣለም የጤና ድርጅት እንዲመሩ ያጨቻቸው ቢሆንም፤ ይህን ከፍተኛ ኃላፊነት ከወሰደ ግለሰብ የሚጠበቅ ሙያዊ ገለልተኝነት እንዳላሳዩ የኢትዮጵያ መንግሥት በቅሬታ ደብዳቤው አመልክቷል።

ሙያዊ ሥነ ምግባር ጥሰት ብሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በቅሬታ ከዘረዘራቸው ውስጥ ዶ/ር ቴድሮስ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ባላት ግንኙነት ላይ ጣልቃ መግባታቸው ያትታል።

ከዚህም ባሻገር ዶ/ር ቴድሮስ አሁንም በአሸባሪነት ለተፈረጀው ህወሓት፣ ድጋፍ መስጠት መቀጠላቸውንና አባልም መሆናቸውን አውስቶ ከስሷቸዋል።

በቅርቡ ዶ/ር ቴድሮስ በተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጵያ መንግሥት ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዳይደርስ ያደርጋል ሲሉ ከስሰዋል።

የድርጅታቸው እንቅስቃሴዎች የከፉ ጦርነቶች ባሉባቸው እንደነ ሶሪያና የመን እንኳ ባልተገታበት ሁኔታ በኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ባልታየ ሁኔታ እግድ እንደሚጣልባቸው አውስተዋል።

“በትግራይ የመድኃኒት እጦት ሰዎች በየቀኑ እንዲሞቱ እያደረገ ነው። የምግብ እጦትም በየቀኑ ሰው ይገድላል። ይህ ሁሉ ሳያንስ በየቀኑ የድሮን ጥቃት መፈጸምና ዜጎች በፍርሃት ተሰቅዘው እንዲቆዩ ማድረግ ትክክል አይደለም” ሲሉ ተደምጠዋል።

ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ከመመረጣቸው በፊት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ሚንስትር እና የጤና ሚንስትር ሆነው ለረዥም ዓመታት ማገልገላቸው ይታወሳል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዓለም ጤና ድርጅት የበላይ ጠባቂ ቦርድ በላከው የቅሬታ ደብዳቤ ላይ ዶ/ር ቴድሮስ የህወሓት ወታደራዊ ድሎችን ሲያስመዘግብ ደስታቸውን እንደሚገልጹ የጠቀሰ ሲሆን፤ ሰብአዊ ቀውሶች ሲፈጠሩም በተለየ ለአንድ ቦታ ብቻ እንደሚያደሉ ይከሳል።

በአጠቃላይ የዶ/ር ቴድሮስ ተግባር የድርጅቱን የገለልተኝነት መርህ የሚጥስና መልካም ስሙንም የሚያጎድፍ መሆኑን፣ እነዚህ የተጠቀሱት ክሶች በዶ/ር ቴድሮስ የፌስቡክ ገጽ የሚታዩ መሆናቸው አመላክቷል።

ከዚህም ባሻገር ዶ/ር ቴድሮስ የዓለም ጤና ድርጅትን በኢትዮጵያ እንዲወክል ለሰየሙት ግለሰብ ተልዕኮ በመስጠት አሻጥር እንዲሰራ ኃላፊነት ሰጥተውት እንደነበረና የአስቸኳይ እርዳታ ፈላጊ ሰዎችን ቁጥር ከ1.8 ሚሊዮን ወደ 3.8 ሚሊዮን አጋኖ እንዲያቀርብ በማድረግ ለተባበሩት መንግሥታትን የተሳሳተ መረጃ ያቀረብ ነበር ብሏል።

ይህም ማለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤትን ውሳኔዎች ማሳሳት ማለት ነው ሲል ይከሳል።

ዶ/ር ቴድሮስ የተባበሩት መንግሥታት ማኅበረሰብን ከኢትዮጵያ መንግሥት በተቃራኒ እንዲቆሙ የቴክኒክና የፋይናንስ እገዛን ሲሰጡ ነበር በሚልም ከሷቸዋል።

በእነዚህና ሌሎች ምክንያቶች የዓለም ጤና ድርጅት የቦርድ አመራሮች ዶ/ር ቴድሮስን የሚመረምር ኮሚሽን እንዲያቋቁምና እርምጃ እንዲወስድ የኢትዮጵያ መንግሥት ጠይቋል።

ዶ/ር ቴድሮስ በቅርቡ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት ላይ፣ ድርጅታቸው በትግራይና ሌሎች በጦርነቱ ለተጎዱ አካባቢዎች ያቀረቡት እርዳታ እንደነበረና ይህ እርዳታ ወደ አፋርና አማራ አካባቢዎች ማድረስ እንደተፈቀደላቸው ነገር ግን ወደ ትግራይ መላክ እንደተከለከሉ አውስተዋል።

ከሐምሌ ወር ጀምሮም በድርጅታቸው አንድም የመድኃኒት እርዳታ እንዳይደርስ ዝግ መደረጉን በመጥቀስ የኢትዮጵያ መንግሥትን ወቅሰዋል።

‘በዓለም ላይ በትግራይ እየደረሰ ያለውን ዓይነት መዓት የትም ዓለም ማየት አይቻልም። ትግራይ ገሀነም ሆናለች’ ሲሉም ተናግረዋል ዳይሬክተሩ።

ይህ ችግር በፖለቲካና ሰላማዊ መንገድ ነው መፈታት ያለበት፤ ጀግና ማለት ደግሞ ሰላምን የመረጠ ነው ሲሉ በዚሁ ቪዲዮ መልዕክት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ተናግረዋል።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት የሚቀርቡ ክሶችን በተመለከተ በሰጠው ምላሽ “መንግሥት ወደ ክልሉ እርዳታ እንዳይገባ እያደረገ ነው” በሚል በህወሓት በኩል የሚቀርበውን ክስ ተቀብለው የሚያስተጋቡ የዓለም ጤና ድርጅትን የመሳሰሉት ዓለም አቀፍ ተቋማት ወቀሳ “በመንግሥት ዘንድ ፍጹም ተቀባይነት የለውም” ሲል አጣጥሎታል።

ጨምሮም የኢትዮጵያ መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ እርዳታ ያለችግር እንዲቀርብ ለማስቻል እየሠራ መሆኑን ገልጿል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com