ዜና

የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር የኮሮናቫይረስ መመሪያን በመተላለፋቸው ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ተጠየቁ

Views: 33

የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ኮሮናቫይረስን ተከትሎ የተጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብ በመተላለፍ አንድ የመጠጥ ድግስ ላይ መታደማቸውን ካመኑ በኋላ በርካቶች ከኃላፊነታቸውን እንዲነሱ እየወተወቱ ነው።

ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአውሮፓውያኑ 2020 ላይ ላደረጉት ነገር ይቅርታ ቢጠይቁም ሰሚ አላገኙም።

”በዚህ ምክንያት በርካቶች ቢቆጡ አልፈርድባቸውም” ብለዋል ጠቅላዩ።

የካቢኔ አባል የሆኑት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን ቆመዋል።

ነገር ግን የስኮትላንድ ካቢኔ መሪው ዳግላስ ሮስ እና ሌሎቹ የእንደራሴ ምክር ቤት አባላት ዊሊያም ራግ፣ ካሮሊን ኖክስ እና ሮጀር ጌል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ጠይቀዋል።

ትናንት ረቡዕ ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ይቅርታ ከጠይቁ በኋላ የስኮትላንድ ካቢኔ መሪው ዳግላስ ሮስ ”አስቸጋሪ ውይይት” ነበር ብለዋል።

መሪው አክለውም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ያላቸው እምነት መሸርሸሩን የሚገልጽ ደብዳቤ መሰል ጉዳዮችን ወደሚከታተለው ምክር ቤት እንደሚጽፉ አስታውቀዋል።

”እሱኮ ጠቅላይ ሚኒስትር ነው፤ የእሱ መንግስት ነው እነኚህን መመሪያዎች ያስቀመጠው፤ ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሰራው ስህተት ተጠያቂ መሆን አለበት” ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

ወግ አጥባቂዎቹ 54 የህዝብ እንደራሴዎች በአውሮፓውያኑ 1922 ለተቋቋመው ኮሚቴ ግልጽ ደብዳቤ የሚጽፉ ከሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትልቅ ፈተና ሊገጥማቸው ይችላል።

በርካታ የዩኬ ሚኒስትሮች በበኩላቸው የህዝብ እንደራሴዎቹ በሲቪል አገልጋይ ሱ ግሬይ የሚመራው መርማሪ ቡድን መረጃ እስነከሚያጠናቅር ድረስ ትንሽ እንዲታገሱ የጠየቁ ሲሆን ግኝቱ በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

ነገር ግን የእንደራሴ ምክር ቤት አባሉ ዊሊያም ራግ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ እራሳቸውን መከላከል የማይችሉበት ሁኔታ ላይ ነው የሚገኙት ብለዋል።

” የጠቅላይ ሚኒስትሩ እጣ ፈንታ በመርማሪው ኮሚቴ ግኝት ላይ ብቻ የተንጠለጠለ መሆን የለበትም” በማለት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

ሌላኛዋ የህዝብ እንደራሴ ቶሪ ካሮላይን በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ መላውን ወግ አጥባቂ ቡድን እየጎዱ ስለሆነ በፍጥነት ከስልጣናቸው መልቀቅ አለባቸው ሲሉ ተደምጠዋል።

ከዚህ በፊትም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የሰላ ትችት ይሰነዝሩ የነበሩት የህዝብ እንደራሴዋ በአይቲቪ ላይ በቀረቡበት ወቅት ”በትክክል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደካማ ጎናችን ናቸው” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋ ይቅርታ መጠየቃቸው ከምህረት ይልቅ ትልቅ ቀውስ ነው ይዞባቸው የመጣው። ሌላው ቀርቶ ጥቂት የማይባሉ የእርሳቸው ደጋፊ የህዝብ እንደራሴዎች ጭምር ቦሪስ ጆንሰን ከኃላፊነታቸው ይነሱ እያሉ ይገኛሉ።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com