ዜና

የተከተቡ ሰዎች ለምን በድጋሚ ኮሮናቫይረስ ይይዛቸዋል?

Views: 32

ኮቪድ የሰው ልጅን የሙጥኝ እንዳለ አለ።

አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ አርጀንቲና፣ ብራዚል እና ሌሎም አገራት ውስጥ ኦሚክሮን ተመልሶ እያመሳቸው ነው።

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የሆስፒታል አልጋን እየያዙ ነው።

ከእነዚህ የሚበዙት የተከተቡ ናቸው።

ታዲያ መከተብ ከተህዋሲው ካልተከላከለ ምንድነው ፋይዳው?

እርግጥ ነው ተከተቡ በተባሉ ሰዎች የሚታይ የጎንዮሽ ጉዳት ዝቅተኛ ነው።

ብዙ ሰዎች በድኅረ ክትባት ጊዜ ከትኩሳት፣ ከራስ ምታት፣ ከክንድ መለስተኛ ሕመም፣ ከድካምና ከማቅለሽለሽ የከፋ ስሜት አይሰማቸውም።

በክትባቱ ታይተዋል የሚባሉት አናፊላክሲስ፣ ቶምቦሲስ፣ ሚዮካርዲቲስ (የልብ አካባቢ መለብለብ) ወዘተ እጅግ ቁጥሩ ባነሱ ተከታቢ ሰዎች ዘንድ ብቻ ነው የተስተዋሉት።

አሁን ድፍን ዓለም እየጠየቀ ያለው ጥያቄ ግን አንድ ነው። መከተብ ከተህዋሲው መያዝ ካላዳነ ምንድነው ፋይዳው? የሚል።

ቢቢሲ ከሕጻናት ሕክምና አዋቂና የተላላፊ በሽታዎች አጥኚ ሬናቶ ክፎሪ ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ቆይታ አድርጎ ነበር።

እሳቸው እንደሚሉት ከሆነ በመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ እነ ፋይዘር እና አስትራዜኒካ እንዲሁም ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባታቸውን ሲያበለጽጉ ግብ የነበረው ተህዋሲው ሰዎችን ለከፋ የጤና ችግር እንዳይዳርጋቸው፣ ሲከፋ ደግሞ ለሞት እንዳያበቃቸው እንጂ ተህዋሲው እንዳይዛቸው ለማድረግ አልነበረም።

ሐኪሙ ይህ ግባቸው ተሳክቷል ብለው ያምናሉ።

“ክትባቶቹ እጅግ ለከፋው የጤና ችግር አጋላጭ ሁኔታ በቂና አስተማማኝ ምላሽ ይሰጣሉ። ቀላልና መለስተኛ ለሆኑ የተህዋሲው ምልክቶች ደግሞ ክትባቶቹ እምብዛምም ናቸው።”

እንደ ሐኪሙ ማብራሪያ መጀመሪያውኑም እኮ ክትባቶቹ ሥሪታቸው ወረርሽኙን ማቆም ወይም ሰው በተህዋሲው መልሶ እንዳይያዝ ማድረግ አልነበረም ይላሉ።

“ዋናው የክትባቶቹ ተልዕኮ አንድ ነው። ተህዋሲው ሰውነትን ለከፋ አደጋ ብሎም ለሞት እንዳያበቃ ጉዳቱን መቀነስ ነበር፤ ይህም ስኬታማ ነው” ይላሉ።

እንደ ምሳሌ የሚያቀርቡት በተለምዶ የጉንፋን ማስታገሻ የምንለው ክትባትን ነው። ያ ክትባት ለዘመናት ሲሰጥ ነው የተኖረው። አንድም ጊዜ ግን ጉንፋኑን ለማጥፋት ተብሎ አግልግሎት ላይ አልዋለም። ሰዎች በጉንፋን የተነሳ ወደከፋ ደዌ እንዳይወደቁ ማገዝ ነው ተግባሩ።

ይህ ክትባት ኢንፍሌዌንዛን ለማጥፋት አልተመረተም። ነገር ግን ልጆች፣ ነፍሰጡሮች፣ ሽማግሌዎች እና ገመምተኞች ይህ የኢንፍሌውዛ ተህዋሲዊ ችግር ውስጥ እንዳይጥላቸው ያደርጋቸዋል።

የኮቪድ-19 ክትባትም ተመሳሳይ ነው። ወረርሽኝ የማቆም ተልዕኮ የለውም ይላሉ።

የኮቪድ-19 ክትባቶች ምን ያህል ሞትን ታድገዋል የሚለውን ብንመለከት ይህን የሐኪሙን ሙግት የሚደግፍ ሆኖ እናገኘዋለን።

የኮመንዌልዝ ፈንድ ባወጣው አንድ ሰነድ ላይ እንደተመላከተው ኮሮናቫይረስ ክትባቶች ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ብቻ አንድ ሚሊዮን ሞትን ተከላክሏል።

ነገር ግን 10 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ሆስፒታል እንዳይገቡና አልጋ እንዳይዙ የሆኑት ክትባት በመውሰዳቸው ነው። ይህ አሐዝ የአሜሪካንን ሕዝብ ብቻ ግምት ውስጥ ያስገባ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅትና የአውሮፓ የተላላፊ በሽታ ቁጥጥጥር ማዕከል እንደሚገምቱት ደግሞ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ፣ በ33 የአውሮፓ አገራት የሚኖሩ ዜጎች ክትባቱ ከሞት ታድጓቸዋል።

ይህ በሌላ አነጋገር ሲገለጽ እነዚህ ሰዎች ክትባቱን በወቅቱ ባይከተቡ ኖሮ የመሞት ዕድላቸው ሰፊ ነበር።

ከእነዚህ መካከል ምናልባትም በርካታ ሰዎች ተህዋሲው መልሶ አልያዛቸውም ባይባልም፣ ለከፋ ጉዳት እንዳያደርሳቸው የሆነው ግን በመከተባቸውና በመከተባቸው ብቻ ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተከተቡ ሰዎች ለምን በተህዋሲው በብዛት መያዝ ጀመሩ?

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሙሉ ክትባት የወሰዱ ሰዎች ሳይቀር በኦሚክሮን እየተያዙ እንደሆነ የሚስተባበል ጉዳይ አይደለም።

ይህ በሦስት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

በተለይ በምዕራቡ ዓለም ገና እና አዲስ ዓመት ክብረ በዓል ላይ በርካታ ሰዎች በጋራ ብዙ ተቀራርበዋል። ይህ መቀራረብ ተህዋሲው እንደልብ እንዲዛመት ሳያስችለው አልቀረም።

ሁለተኛው ምክንያት ክትባቱ ለተቀረው ዓለም ከተሰራጨ ከዓመት በኋላ ተመራማሪዎች የደረሱበት አንድ ፍንትው ያለ ሐቅ ቢኖር፣ ክትባቱ አንድ ጊዜ ተወስዶ በቃ ከዚህ ወዲያ እምብዛም አያስፈልግም የሚባል እንዳልሆነ ነው።

“በጊዜ ሂደት የክትባቱ የመከላከል አቅም እንደሚወርድ ደርሰንበታል። አቅሙ የመውረዱ ፍጥነት ደግሞ ከተከታቢው ዕድሜና የተፈጥሮ ሁኔታ ጋር የተያያዘ ነው” ይላሉ ሐኪም ክፎሪ።

ይህም ሐቅ ነው ሦስተኛ ዙር የማጠናከሪያ ክትባት ዘመቻ እንዲከፈት ምክንያት የሆነው። ይህ ዘመቻ በቅድሚያ ዕድሜያቸው ለገፋ ብቻ ታስቦ የነበረ ቢሆንም ሌሎች ሰዎችም ቢወስዱት ጥቅም እንጂ ጉዳት እንደሌለው ተደርሶበታል።

ያም ሆኖ አሁንም የተከተቡ ሰዎች በተህዋሲው እየተያዙ ነው ያሉት። በዚህ ጉዳይ ላይ ሐኪሙ የሚሉት ይህንን ነው።

“ነገሩ እንደ ኢንፍሌዎንዛ ክትባት ነው። ከዚህ ሁኔታ ጋር፣ ከሐቁ ጋር ተስማምተን መኖር መቀጠል ነው የሚኖርብን። ሌላ ነገር የለም።”

መልካሙ ነገር ተከትበው ሳለ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመጣው ልውጥ የኮሮናቫይረስ ምክንያት ወደ ሆስፒታል የሚመጡ ሰዎች ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑ ነው።

ይህም የሚያሳየው ክትባቱ ይነስም ይብዛ ሥራውን እየሠራ መሆኑን ነው።

ይህን ሐቅ ለማስረዳት ኒውዮርክ ከተማን እንደ ማሳያ መውሰድ ብቻ በቂ ነው።

በታኅሣሥ ወር ወደ ሆስፒታል የሚመጡ ሰዎች እና የሟቾች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ አሻቀበ። ከእነዚህ ውስጥ እጅግ የበዙት ክትባት ያልወሰዱ ናቸው። ክትባት የወሰዱ ሰዎች ግን በተህዋሲው ቢያዙም ለሆስፒታል የሚያበቃ ችግር ላይ አልወደቁም።

የዩናይትድ ኪንግደም ጤና ቢሮም ቢሆን ከዚህ የተለየ ድምዳሜ ላይ አልደረሰም።

የኬምብሪጅ ዩኒቨርስቲ ባወጣው አንድ የጥናት አሐዝ አንድ ሙሉ ጠብታ የተከተበ ሰው በኦሚክሮን ቢያዝ ወደ ሆስፒታል የማይመጣበት ዕድል 81 ከመቶ በላይ ነው።

ሐኪሙ የመጨረሻ መልዕክታቸው ይህ ነው።

“ብከተብም ባልከተብም ያው በቫይረሱ መያዜ አይቀርምና ቢቀርብኝስ የሚሉት ሰዎች ፍጹም የተሳሳቱ ናቸው። እውነት ነው፣ የተከተበም ያልተከተበም በተህዋሲው ሊያዝ ይችላል። ነገር ግን ውጤታቸው አንድ አይደለም። የተከተቡት በቤታቸው ያልፉታል፤ ያልተከተቡት ግን ይሞታሉ።”

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com