ዜና

አሸባሪው ህወሓት የወደሙ 14 ሆስፒታሎች እና ከ60 በላይ ጤና ጣቢያዎች አገልግሎት መስጠት ጀመሩ

Views: 49
በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ 14 ሆስፒታሎች እና ከ60 በላይ ጤና ጣቢያዎች አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ መደረጉን ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።
ሆስፒታሎቹ እና ጤና ጣቢያዎቹ በተደረገላቸው መልሶ ጥገና ወደ አገልግሎት መመለሳቸውን ነው የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ የገለጹት።
ሚኒስትሯ ዓለም አቀፍ ኢትዮጵያውያን የተባበረ ዳያስፖራ ጥምረት ባዘጋጀው የዙም ውይይት ላይ ተሳትፈው የጤና ዘርፍ የመልሶ ማቋቋም ስራዎች ላይ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፥ በአሸባሪው ህወሓት የተጎዱ ዜጎችንና የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም ሰፊ ሀብትና አፋጣኝ ምላሽ የሚያስፈልገው መሆኑን ጠቅሰዋል።
መንግስት አጠቃላይ የመልሶ ግንባታውን በእቅድ እያከናወነ ሲሆን፥ በተለይ የወደሙ የጤና ተቋማትን ከማቋቋም አንጻር በአዲስ አበባ እና በክልሎች የሚገኙ ሆስፒታሎች ሃላፊነት ወስደው የወደሙ የህክምና መሳሪያዎችን እንዲያሟሉ እየተደረገ ነው ብለዋል።
እስካሁን በተደረገው የመልሶ ጥገና ሥራ 14 ሆስፒታሎች እና ከ60 በላይ ጤና ጣቢያዎች ወደ ስራ እንዲመለሱ መደረጋቸውን ነው ሚኒስትሯ የገለጹት።
በዚህም ተቋማቱ ቢያንስ መሰረታዊ የሚባሉ የእናቶች ወሊድ፣ የህፃናት አጣዳፊ ህክምናዎች እና ድንገተኛ ህክምናዎች እንዲሰጡ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በመልሶ ማቋቋም ሂደቱ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እያደረጉ ያሉት ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን በመጥቀስ አመስግነዋል።
በማህበረሰቡ ላይ የደረሰውን የስነልቡና ጉዳት ለማከም ከተለያዩ የማህበራዊና የአዕምሯዊ ጤና ባለሙያዎች ጋር እየተሰራ ሲሆን÷ ዳያስፖራውም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com