ዜና

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሰላምን በማረጋገጥ ረገድ የመሪነት ሚናዋን መወጣት እንደምትቀጥል ሙሉ እምነት አለኝ – የደቡብ ሱዳን መከላከያ ሚኒስትር

Views: 42
ኢትዮጵያ በቀጣናው ብሎም በአፍሪካ ሠላምን በማረጋገጥ ረገድ የመሪነት ሚናዋን መወጣት እንደምትቀጥል ሙሉ እምነት አለኝ አሉ የደቡብ ሱዳን መከላከያ ሚኒስትር አንጀሊና ቴኒ።
በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማህዲ ከደቡብ ሱዳን መከላከያ ሚኒስቴር አንጀሊና ቴኒ ጋር በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳዮች እና ቀጣናዊ ሁኔታዎች ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡
አምባሳደር ነቢል ÷ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራ እና በአፋር ክልሎች የፈጸመውን ወረራ እና ግፍ አስመልክቶ ለደቡብ ሱዳን መከላከያ ሚኒስትሯ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በጥምረት በመቆም የሽብር ቡድኑን ወረራ እና የሽብር ተግባር ቀልብሰዋል ብለዋል አምባሳደሩ በውይይታቸው፡፡
አሸባሪ ቡድኑ ያደረሰውን ጥፋት እና የንብረት ውድመትም በተቻለ መጠን ለመመለስ በተደረገው ጥረት በሀገር ውስጥ እና በውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያን ትብብር ከፍተኛ እንደነበርም አንስተዋል፡፡
የሱዳን መከላከያ ሚኒስትር አንጀሊና ቴኒ በበኩላቸው÷ የኢትጵያ መንግስት የውስጥ ጉዳዮቹን በራሱ የመፍታት ሙሉ አቅም እንዳለው አሳይቷል ብለዋል፡፡
አንጀሊና ቴኒ አያይዘውም፥ የኢትጵያ ሠላም መሆን ለቀጣናው ብሎም ለአፍሪካ ሠላም መሆን ዓይነተኛ ሚና እንዳለው አውስተው፥ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት( ኢጋድ ) ሚናም ለቀጣናው ሰላም ዋስትና መስጠት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
አንጀሊና ቴኒ ÷ ኢትዮጵያ በቀጣናው ብሎም በአፍሪካ ሠላምን በማረጋገጥ ረገድ ያላትን የመሪነት ሚና መወጣቷን እንደምትቀጥል ሙሉ እምነት እንዳላቸውም ነው የገለጹት፡፡
በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማህዲ እና የደቡብ ሱዳን መከላከያ ሚኒስትር አንጀሊና ቴኒ፥ ሁለቱን ሀገራት በሚመለከቱ ሌሎች ጉዳዮች ላይ መምከራቸውንም የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡
Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com