ዜና

ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን በቃለ ምልልስ ወቅት ጸያፍ ቃል ተጠቅመዋል በሚል ውግዘት ደረሰባቸው

Views: 40

ፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ያልተከተቡ ሰዎችን ሕይወት አስቸጋሪ ማድረግ እፈልጋለሁ በሚል ቃለ ምልልስ መስጠታቸውን እና ይህንን ለመግለጽ የተጠቀሙበት ዘዬ ከፋፋይ እና ጸያፍ አገላለጽ ነው በሚል የተለያየ ትችቶችን እያስተናገዱ ይገኛሉ።

“በእርግጥ እነሱን [መከተብ የማይፈልጉትን] ማናደድ እፈልጋለሁ፣ እናም ይህን ማድረጋችንን እንቀጥላለን – እስከ መጨረሻው” ሲሉ ፕሬዘዳንቱ ላ ፓሪስያን ለተሰኘው ጋዜጣ ተናግረዋል።

የፈረንሳይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሊካሄድ ሦስት ወራት በቀረበት በዚህ ግዜ የማክሮን ተቃዋሚዎች ቃላቶቹ ከፕሬዝደንት የማይጠበቁ ናቸው ብለዋል።

የፓርላማ አባላትም ክትባት ባልወሰዱ ሰዎች የማሕበራዊ ሕይወት እንቅስቃሴዎች ላይ እገዳ ይጥላል ተብሎ የታሰበው ሕግ ላይ ክርክር ማድረጋቸውን አቁመዋል።

የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች በፕሬዝዳንቱ ቋንቋ ላይ ቅሬታ ማቅረባቸውን ተከትሎ የብሔራዊ ምክር ቤቱ ስብሰባ ትላንት ማክሰኞ ለሁለተኛ ጊዜ እንዲቆም ተደርጓል። የማክሮንን የቃላት አጠቃቀም፤ “የማይገባ፣ ኃላፊነት የጎደለው እና የታሰበበት” ሲሉ አንድ የተቃዋሚ መሪ ገልጸውታል።

ክትባት ያልወሰዱ ሰዎችን ማኅበራዊ ተሳትፎ የሚገድበው ሕግ ሳምንቱ ሳይጠናቀቅ ይፀድቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የክትባት ተቃዋሚዎችን ክፉኛ አስቆጥቷል። በርካታ የፈረንሳይ የፓርላማ አባላት በጉዳዩ ላይ የግድያ ዛቻ እየደረሰባቸውም ይገኛል።

የኮሮና ቫይረስን ክትባት በግዴታ የመስጠት መርሃ ግብሮች በበርካታ የአውሮፓ አገራት ውስጥ በጅማሮ ላይ ነው። በዚህ ቀዳሚ የሆነችው ኦስትሪያ ስትሆን ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ከ14 ዓመት በላይ ከሆኑ ታዳጊዎች ጀምሮ ክትባቱን ይወስዳሉ።

ጀርመን ለአዋቂዎች ክትባቱን ለማድረስ ተመሳሳይ እቅድ ይዛለች።

የጣሊያን መንግሥት ረቡዕ ዕለት ከየካቲት 5 ጀምሮ የኮቪድ-19 ክትባቱ ከ50 ዓመት በላይ ለሆናቸው ሁሉ ግዴታ እንደሚሆን አስታውቋል።

ማክሮን ማክሰኞ ዕለት ታትሞ በሚወጣው ሌ ፓሪዚያን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ አንድ ዙር ክትባት እንኳን ያልወሰዱትን አምስት ሚሊዮን የፈረንሳይ ነዋሪዎች “በኃይል አይከተቡም” ያሉ ሲሆን፤ ነገር ግን ሰዎች በተቻለ መጠን በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በመገደብ ክትባቱን እንዲወስዱ ለማበረታታት ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

“ወደ እስር ቤት አልካቸውም (ያልተከተቡትን)። ከጥር 15 ጀምሮ ግን ወደ ምግብ ቤት መሄድ እንደማይችሉ እንነግራቸዋለን። ቡና ለመጠጣት መሄድ አትችሉም፣ ወደ ቲያትር ቤቶች መግባት አትችሉም። ወደ ሲኒማ ቤቶች መሄድ አትችሉም ብለን መናገር አለብን” ሲሉ ፕሬዝደንት ማክሮን ተደምጠዋል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com