ዜና

ጆ ባይደን ለካፒቶል ሂል አመጽ ትራምፕን ተጠያቂ ሊያደርጉ ነው

Views: 41
  1. ጆ ባይደን ለካፒቶል ሂል አመጽ ትራምፕን ተጠያቂ ሊያደርጉ ነው

በካፒቶል ሒል 1ኛ ዓመት ዝክር ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ለአመጹ ዶናልድ ትራምፕን ሊያብጠለጥሉ ነው።

ጆ ባይደን የካፒቶል ሒል ግርግር 1ኛ ዓመት ታስቦ በሚውልበት በነገው ዕለት ዶናልድ ትራምፕን በይፋ እንደሚወቅሱ ይጠበቃል።

ባይደን ንግግራቸውን የሚያደርጉት በአሜሪካ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ነውጡ በተስተዋለበት የሕንጻው ክፍል ነው።

ጆ ባይደን በንግግራቸው ለካፒቶል ሒል ግርግር ብቸኛውና አውራው ተጠያቂ ዶናልድ ትራምፕ እንደሆኑ በማያሻማ ሁኔታ ይናገራሉ ተብሏል።

ይህ እንደሚሆን የተናገሩት ደግሞ ቀደም ብለው መግለጫ የሰጡት የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ ናቸው።

ባለፈው ዓመት ጥር 6 ነበር ነውጠኛ የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች በአሜሪካ ይሆናል ተብሎ በማይጠበቅ ሁኔታ ካፒቶል ሒልን ሰብረው በመግባት ብጥብጥ የፈጠሩት።

ይህም በታሪክ የካፒቶል ሒል ግርግር ተብሎ እየታሰበ ነው።

መርማሪዎች እስከዛሬ 725 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውለው ምርመራ እያደረጉባቸው ነው።

ነውጠኛ የትራምፕ ደጋፊዎች ካፒቶል ሒልን ሰብረው ሲገቡ በወቅቱ የአሜሪካ እንደራሴዎች ሸንጎ ይዘው ነበር።

ይነጋገሩ የነበረውም የጆ ባይደንን መመረጥ ለማጽደቅ ነበር።

ከዚህ የካፒቶል ሒል ግርግር ትንሽ ቀደም ብሎ በምርጫ ተሸንፈው የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ ነውጠኛ ደጋፊዎቻቸውን እስከመጨረሻው እንዲፋለሙ ቀስቅሰው ነበር።

ዶናልድ ትራምፕ ያን ወቅት ምርጫው መጭበርበሩን ደጋግመው ይናገሩ የነበረበት ጊዜ ነው።

ጆ ባይደን ብዙም ስለ ቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስም ማንሳት የሚወዱ ባይሆንም ነገ ሳተርዴይ ሆል በሚሰኘው የካፒቶል ሒል አዳራሽ በሚያደርጉት ንግግር ግን ትራምፕን በስም እያነሱ እንደሚወቅሱ ይጠበቃል።

የታችኛው ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፒሎሲ በበኩላቸው በዕለቱ ያን ነውጥ በማሰብ የሕሊና ጸሎትን ይመራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በካፒቶል ሒል ግርግር ጥቂት ሰዎች ሞተዋል፤ 140 የሚሆኑ የጸጥታ አካላት ላይ ጉዳት ደርሷል።

ከካፒቶል ሒል ግርግር በኋላ ተሰናባች የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ ነውጥ በመቀስቀስ በሚል ክስ ተመስርቶባቸው የነበረ ሲሆን ያን ጊዜ በሪፐብሊካኖች ተሞልቶ የነበረው ሴኔት ግን ክሱን ውድቅ አድርጎት እንደነበረ ይታወሳል።

የካፒቶል ሒል ግርግር የአሜሪካ ሕዝብ በፖለቲካ ምን ያህል እየተከፋፈለ እንደመጣ ሁነኛ ማሳያ ተደርጎ በብዙ ተንታኞች ዘንድ ይወሳል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com