ዜና

በሰደድ እሳት የወደመ ደን ለመተካት የአንኮበር ወረዳ እና ዋሊያ ቢራ በጋራ እየሰሩ ነው!

Views: 37
– የወፍ ዋሻ ደን ብሔራዊ ፓርክ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ ነው!
– ድምፃዊ ካሥማሠ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ተሳታፊ ነበር!
በአማራ ክልል የአንኮበር ወረዳ አካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ጽ/ፈት ቤት አስተባባሪት እና በዋሊያ ቢራ አክሲዮን ማኅበር ድጋፍ አቅራቢነት በወረዳው በመጋቢት ወር በሰደድ እሳት የወደሙ የደን ሃብቶችን መልሶ ለመተካት በትብብር እየተሰራ ነው፡፡
በአንኮበር ወረዳ ዘጎ ቀበሌ የወፍ ዋሻ ደን በተሰኘ አካባቢ በሰደድ እሳት የወደሙ የደን ሃብቶችን መልሶ ለመተካት የችግኝ ተከላ ሥራ በዛሬው (ሰኞ ነሐሴ 24 ቀን 2013 ዓ.ም) እለትም በአካባቢው ነዋሪዎች እየተከናወነ ነው፡፡ ለችግኝ ተከላው የሚውሉ ከ2500 በላይ የአገር በቀል ዛፎችን ችግኝ ያቀረበው ዋሊያ ቢራ ሲሆን፣ ችግኙ በአግባቡ እንዲጸድቅ ለመንከባከብ የሚያስችልና የአካባቢውን ተራራማ መልክዓ ምድር ተደራሽ የሚያደርጉ (መኪና ስለማይገባ) ሁለት ሞተር ሳይክል ለወረዳው ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ጽ/ፈት ቤት አበርክቷል፡፡
ቅዳሜ ነሐሴ 22 እና እሁድ ነሐሴ 23 ቀን 2013 ዓ.ም በዋሊያ ቢራ ሠራተኞች፣ በአካባቢው ማኅበረሰብ፣ በወረዳው ኃላፊዎች እና በበጎ ፈቃደኞች በተከናወነ አካባቢውን የመንከባከብና የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ላይ በርካታ ለአካባቢው ተስማሚ የሆኑ ሀገር በቀል ዛፎች ተተክለዋል፡፡ የዋሊያ ቢራ የክብር አምባሳደር ድምፃዊ ካሥማሠ በአንኮበር ተገኝቶ ችግኞችን ተክሏል፡፡
የአንኮበር ወረዳ አካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ጽ/ቤት ተወካይ ኃላፊ አቶ ይሻው ታምሬ እንደገለጹት፣ የወፍ ዋሻ ተብሎ በሚታወቀው ሥፍራ ስምንት ሺህ ሄክታር መሬት በደን የተሸፈን ጥብቅ ሥፍራ ሲሆን፣ ባለፈው መጋቢት ወር በሰደድ እሳት የተቃጠለው 235 ሄክታር መሬት ነው፤ ከዚህ ውስጥ 90 ሄክታር መሬት መልሶ መልማት ያለበት ነው ያሉት ኃላፊው፣ እስከ አሁን 11 ሄክታር በክልሉ አካባቢ ነዋሪዎችና በተባባሪ አካላት መልሶ ማልማት ተችሏል፡፡ 79 ሄክታር የደን ሥፍራው ደግሞ በራሱ ጊዜ መልሶ ያገግማል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
የዋሊያ ቢራ አክሲዮን ማኅበር ሲኒየር ብራንድ ማኔጀር ወ/ሪት ፋይዳ ዘውዱ በችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ተሳትፎ ያደረጉ ሲሆን ‹‹ዋሊያ ቢራ ከተፈጥሮ መንከባከብ ጋር የተገናኙ እንቅስቃሴዎችን እንደ መርህ ይዞ ስለሚሳተፍ ነው ወደ አንኮበር የመጣነው ብለዋል፡፡
‹‹ይህን ድጋፍ ያደረግነው ምርቶቻችን ሁሉ የተፈጥሮ ጥገኞች በመሆናቸው ነው፤ አብረን በጋራ ስንሰራ የሕብረተሰቡን ልማት እናነቃቃለን፤ እኛም በውጤቱ እንጠቀማለን፡፡›› ያሉት ወ/ሪት ፋይዳ፣ ‹‹እንደሚታወቀው የዋሊያ ቢራ መሪ-ቃል ‹አንድ ላይ ወደ ላይ› የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉን ነገር የምናደርገው ከሕብረተሰቡ ጋር በአንድነት ነው፡፡ ስንተባበርና ስንተጋገዝ ኃይላችን ከፍ ይላል›› ብለዋል፡፡
የአንኮበር ወዳጆች ስብስብ አስተባባሪ አቶ ጌታ መኮንን በአማራ ክልል የአንኮበር ወረዳ አካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ጽ/ፈት እና በዋሊያ ቢራ አክሲዮን ማኅበር መካከል የደን ልማት ትብብርና ድጋፍ እንዲደረግ ያስተባበሩ ግለሰብ ናቸው፡፡
የወፍ ዋሻ ደን በአማራ ክልል አሉ ከሚባሉ ጥቂት ጥብቅ የደን ሃብት አንዱ ነው ያሉት አቶ ጌታ መኮንን፣ በሰደድ እሳት የወደመውን ደን ለመከላከል የአካባቢውን ማኅበረሰብ፣ የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት እና የበጎ ፈቃድ ደጋፊዎችን በጉልበትም በገንዘብም በማስተባበርና በማስተዋወቅ ሰደድ እሳቱ እንዲጠፋ አደረግን፤ ክረምቱ ሲገባም ከተለያዩ አካላት ድጋፍ በማሰባሰብ የወደመውን ደን ለመተካት ባለፈው ወር ብቻ ወደ 19 ሺህ ችግኝ እንዲተከል አድርገናል ብለዋል፡፡
አሁን ደግሞ ዋሊያ ቢራ ባደረገው ድጋፍና ትብብር ነው ችግኝ እየተከልን የምንገኘው ብለዋል፡፡ ወደ ፊት ይሄ ሥፍራ ብሔራዊ ፓርክ እንዲሆን በአማራ ክልል ጥረት እየተደረገ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ዋሊያ ቢራ አክሲዮን ማኅበር፣ የዋሊያ ቢራ ብራንድ መጠሪያ የሆነው ብርቅዬ የዱር እንስሳ (ዋሊያ) በሚገኝበት በሰሜን ተራራች ፓርክ ተገኝቶ ተመሳሳይ የችግኝ ተከላ ማከናወኑ ይታወሳል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ቂሊንጦ፣ በበደሌ፣ በሐረር ተፈጥሮን የማልማት፣ ዛፎችን የመትከል መርሃ ግብር፣ በየዓመቱ የሚያከናውነው የማኅበረሰብ ልማት ተግባራት ናቸው፡፡
Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com