ዜና

አዲስ የጤፍ ምዕራፍ ጤፍ እና ማዳበሪያን በመሥመር የሚዘራ ማሽን

Views: 70

Tef and fertilizer Row planting machine

መነሻ፣

ጤፍ እርሻችን፣ ጤፍ ምግባችን፣ ጤፍ ተስፍችን፣.. …. ጤፍ ሁሉ ነገራችን ነው፡፡ ዛሬም ነገም ለጤፍ ልማት፣ ለጤፍ ምግብ፣ ለጤፍ የአገር ውስጥ እና የውጪ ገበያ፣ ለጤፍ ዕደጥበብ ገና ብዙ ሥራ ይጠብቀናል፡፡ ለጤፍ ጉዳይ አዳዲስ የአሥተራረስ ዘዴ፣ አዳዲስ ፈጠራ መጀመር፣ በሌላ አገር የዳበረ ቴክኖሎጂ መውሰድ ወዘተ ገና ብዙ ነገረ ጉዳዮች አሉብን፡፡ ይህም  ብቻ ሳይሆን እስከዛሬም በአገር ውስጥ ተሰርተው፤ ነገር ግን እውቅና ያላገኙ፣ ትኩረት ያላገኙ ብዙ የሥራ ውጤቶች አሉ፡፡

የጤፍን ምርት ለማሻሻል ብዙ ቁልፍ ጉዳዮች አሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ጤፍን በመስመር መዝራት ነው፡፡ ጤፍን በመሥመር ለመዝራት የተሠሩ አገራዊ የሆኑ፣ እውቅና የተቸራቸው መሣሪያዎች እስከ ዛሬ ብዙ የሉም፡፡ ብቻ አንድ በወርቃማ የአርሶአደር እጅ የተሠራ ጤፍና ማዳበሪያን በመሥመር የሚዘራ ማሽን የተሠራው በምሥራቅ ሸዋ ከአዳማ ከተማ በስተ-ምሥራቅ በቅርብ ርቀት በምትገኝ ወለንጪቲ ከተማ ውስጥ ነው፡፡

ማሽኑ የተሠራው በማን ነው?

አቶ ሲሳይ ተክለሥላሴ ሞዴል አርሶ አደር ናቸው፡፡ ከባለቤታቸው ወ/ሮ ቀለሟ፤  ከልጆቻቸው  እና  የልጅ  ልጆቻቸው ጋር በወለንጪት ከተማ ይኖራሉ፡፡   የትምህርት ደረጃ 8ኛ ክፍል ናቸው፡፡ በ2ዐ አመታት ልፋት እና ትጋት ጤፍ እና ማዳበሪያን በመስመር የሚዘራ በእንስሳት ጉልበት የሚጎተት ማሽን ሠሩ፡፡ ይህ ማሽን ጊዜን ይቆጥባል፣ ጤፍን እና ማዳበሪያን ይቆጥባል፡፡ ሥራን ያቀላጥፋል፡፡

አቶ ሲሳይ ተክለሥላሴ  

በ3ኛው የጤፍ ዓለም አቀፍ ወርክሾፕ ላይ

የማሽኑ ባለቤት  አቶ ሲሳይ ተክለሥላሴ (ሞዴል አርሶ አደር)  እንደገለፁት፡ “ታርሶ ለስልሶ ለዘር የተዘጋጀ አንድ ጥማድ ማሳ በአንድ ሰዓት ውስጥ ዘሩን እና ማዳበሪያውን  በመስመር  ዘርቶ አፈሩን በስስ አልብሶ መጨረስ ያስችላል፡፡ በዚህ ስሌት አንድ ሄክታር በ4 ሰዓት ማጠናቀቅ ይቻላል፡፡ በዚህ ማሽን ሲዘራ ለአንድ ሄክታር ከ 5 ኪሎ እስከ 8 ኪሎ የጤፍ ዘር እና እስከ 15 ኪሎ ማዳበሪያ ይበቃል፡፡”  ብለዋል፡፡  በእጅ ብተና ሲዘራ በሔክታር እስከ 25 ኪሎ ጤፍ እና እስከ 5ዐ ኪሎ ማዳበሪያ ሥራ ላይ ይውላል፡፡ ጤፍ እና ማዳበሪያን ይቆጥባል ሲባል እንዲህ ነው፡፡

የማሽኑን ውጤታማነት ለምሣሌ ለማስረዳት የሚከተለውን ንጽጽር ተመልከቱ ፡፡

ይህን ማሽን በኢትዮጵያ አዕምሮ ንብረት ጽ/ቤት አስመዝግበው፤ የአገልግሎት ሞዴል ሰርተፊኬት አግኝተዋል፡፡  በቢሾፍቱ ከተማ ጥቅምት 2ዐ12 ዓ.ም 3ኛው የጤፍ ዓለም አቀፍ ወርክሾፕ ላይ ለእይታ አቅርበውት ነበር፡፡

የማሽኑ ዕይታ ይህን ይመስላል፡፡ ይህ ፎቶ በመኖሪያ ቤታቸው ገለፃ ሲያደርጉ የተነሣ ነው፡፡

አቶ ሲሳይ የጤፍ ማሽኑን በቤታቸው ጊቢ ሲያሳዩ

ይህ አዲስ እና ልዩ  የጤፍ ዘር እና ማዳበሪያ መዝሪያ የእጅ ማሽን በዘር ወቅት የእርሻ ሥራን ለማቅለል የተዘጋጀ ነው፡፡ በጣም ተፈላጊነቱ የሥራ ጫናን መቀነሱ እና ማሽኑ በብዙ አማራጭ እንዲጎተት  ተደርጎ የተሠራ መሆኑ ነው፡፡

  • በሁለት በሬዎች አንገት ላይ ተጠምዶ ይሳባል፣
  • በአንድ ግመል  ላይ በግራ እና ቀኝ በሁለት ሞፈር መስል እንጨት ይሳባል፣
  • በአንድ  ፈረስ ላይ ታስሮ ይሳባል፣
  • በሁለት ፈረሶች  ላይ ተጠምዶ ይሳባል፣
  • በአንድ  አህያ በግራ እና ቀኝ ታስሮ ይሳባል፣
  • በሁለት አህዮች ላይ ተጠምዶ ይሳባል፣ ወይም
  • በአንድ አህያ እና በአንድ በሬ ጥማድእንዲሠራ

 ተገጥሞ የተሠራ ነው፡፡

በዚህ ማሽን አርሶ አደሩ እንደየአካባቢ የአፈር ሁኔታ የእንስሳትን ጉልበት ይገለገላል፡፡ይህ ማለት ለምሳሌ አሸዋማ ቀላል አፈር፣ መካከለኛ አፈር ወይም ዋልካ አፈር ከባድ ጭቃ ቢሆን ተገቢውን የእንስሳት ጉልበት ሥራ ላይ ያውላል ማለት ነው፡፡  በአሸዋ አፈር ላይ በአንድ አህያ ጉልበት መዝራት ይችላል፡፡ ዋልካ መረሬ ጭቃ ከሆነ ደግሞ ማሽኑ ጥማድ በሬ ወይም ፈረስ ላይ ጠመዳል፡፡

ጤፍ በብተና በሚዘራበት ወቅት ብዙ የዘር ብክነትን ያስከትላል፡፡ ማዳበሪያ በብተና ሲዘራ  ከሚፈልገው በላይ አፈር ላይ በመድረሱ አረም ያበዛል፤ አፈሩን ይጎዳዋል፡፡ ነገር ግን ይህ አዲሱ ማሽን በአንድ ጊዜ የተፈለገውን የእህል ዘር እና ማዳበሪያ በአንድ ሰው ለመዝራት ያስችላል፡፡

ብዛታቸው አምስት የሆኑ እየቆፈሩ መስመር ማውጫ ብረት ማረሻ  ጣቶች በፊት አሉት፡፡ በመስመሮች መካከል 2ዐ (ሃያ ሣንቲሜትር) ርቀት አለው፡፡  በአንድ ጊዜ አንድ ሜትር ያህል ዘር እና ማዳበሪያ ወይም ማዳበሪያ የማያስፈልግ ከሆነ ዘር ብቻ  ለመዝራት ያስችላል፡፡

ከታች ያለው የማሽኑ አካል የሚያሳየው 2ዐ ሳንቲሜትር ርቀት ያላቸው 5 መሥመሮችን ነው፡፡

መሥመር ማውጫው ምስል

ከላይ የዘር መያዣ እና የማዳበሪያ ቋት የተለያዩ ናቸው፡፡ ከሁለቱም ቋት ጋር የዘር እና ማዳበሪያ ማስተላለፊያና ማጓጓዣ ቱቦዎች ተገጥመዋል፡፡  በአንድ እጅ የሚታዘዝ   ዘር እና ማዳበሪያ ለመዝራት  የሚያስችል መነቅነቅያ አለው፡፡ በአንድ የዘር ስርጭት እንቅስቃሴ ጊዜ መነቅነቅቂያውን ከፍና ዝቅ በማድረግ  በተወሰነ መጠን በተቀየሰው ቦይ ውስጥ ዘርና ማዳበሪያ ይንጠባጠባል፡፡ ዘርና ማዳበሪያው በአንድ ጊዜ በአምስቱም መስመር ውስጥ ተዘራ ማለት ነው፡፡ ወድያው  የመስመር ማውጫ ጣቶችን ተከትሎ የተሰራጩ  ዘሮች እና ማዳበሪያ ላይ በጀርባ በኩል በስሱ አፈር የሚሸፍን ፌሮ ብረት ዘንግ ተገጥሞለታል፡፡

ጤፍና ማዳበሪያን

በአንድ መስመር የሚለቁ መንታ ቱቦዎች ከኋላ ሲታዩ

እስከዛሬ ብዙ ጊዜ አሻሽለው ደጋግመው ሠርተዋል፡፡ በቅርቡ እጅግ የተሻሻለው እና የአገልግሎት ምዝገባ ሠርተፊኬት ያገኙበት ማሽን ሙሉ ክብደቱ እስከ 4ዐ ኪሎ ግራም ነው፡፡  በየክርምቱ ወቅት  አርሶ አደሮችን ጠርተው የመስክ ምልከታ እና ግምገማ በራሳቸው አዘጋጅተዋል፡፡ በ2ዐ11 ዓ.ም የክረምት ወራት መግቢያ ላይ ባዘጋጁት የመስክ ምልከታ ላይ የምስራቅ ሸዋ ግብርና ጽ/ቤት፤ የመልካሳ እርሻ ምርምር፣ የቦሰት ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት እና የአካባቢውን አርሶ አደሮች ጠርተው ባዘጋጁት የመስክ ምልከታ ላይ ተገኝቼ ነበር፡፡ በወቅቱ አርሶ አደሮች ገንቢ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ይህን የተሻሻለውን ዓይነት ሰባት ያህል ማሽን ሠርተዋል፡፡ በራሳቸው የጤፍ እርሻ እና በቦሰት ወረዳ የጤፍ ዘር አባዥ ማህበር መሬት ላይ በማሽኑ ጤፍን በየክረምቱ ይዘሩበታል፡፡  አንዱን በምስራቅ ሸዋ ዞን፣ ለቦሰት ወረዳ ለወረዳው ግብርና ጽ/ቤት በውሰት ሰጥተዋል፣ ጽ/ቤቱም በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ ለብዙ የክረምት ወራት ግልጋሎት ላይ አውሏል፡፡  ወደ ሻሻመኔ አካባቢም አንድ በውሰት ልከው ለሶስት የክረምት ወቅት ተገልግለውበታል፡፡ ምንጃር አረርቲ ደብረ ፀሐይ ቀበሌ አርሶ አደሮች በግል ተከራይተው ባለፈው ክረምት ጤፍና ማዳበሪያን በመሥመር ዘርተውበታል፡፡

አንዱን ማሽን በ3ኛው የጤፍ ዓለም አቀፍ ወርክሾፕ ላይ ለተሳታፊዎች ለእይታ አቅርበው ነበር፡፡

በወቅቱም ስለ ማሽኑ ገለፃ አድረገዋል፡፡  ይኸው ጉዳይ በዚሁ የወርክሾፑ መጽሔት ላይ ቀርቧል፡፡ ማጣቀሻው ከታች ይገኛል፡፡

ከታች ያለው ምስል በ2ዐ11 ክረምት በቦሰት የጤፍ ዘር አባዥ ማህበር ማሳ ላይ በማሽኑ የተዘራውን የጤፉን አቋም ሲያሳዩ ነው፡፡

በመስመር የተዘራው ጤፍ በማሳ ላይ 2ዐ11 ክረምት

በቦሰት ገጠር ላይ

ማጠቃለያ

“የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል፤” እንደተባለው የጤፍ ነገር ብዙ ይቆጫል፡፡ መላ እና ማጣፊያ የሌላቸው የትየለሌ የጤፍ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለአዲስ የጤፍ ምዕራፍ ጤፍ እና ማዳበሪያን በመሥመር መዝራት ወሳኝ ነው፡፡

እኒህን አርሶ አደር እና መላውን ቤተሰባቸውን አለማድነቅ አይቻልም፡፡ ይህን ጤፍ እና ማዳበሪያን በመሥመር የሚሠራ ማሽን በፈጠራ ሲሰሩ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል፣ ጊዜ ሰውተዋል፣ ብረት ቀጥቅጠው፣ ብረት ቆርጠው፣ ብረት በይደው፣ አስተሳስረው፣ አስማምተው ለሥራ ብቁ አድርገዋል፡፡ ጥቂት ማሽኖችን በአርሶአደር አቅም በውሰት ሰጥተዋል፤ የቢሮ ሰዎችን ጠርተው የመስክ ምልከታ ፕሮግራም አዘጋጅተዋል፡፡ በጤፍ ዓለም አቀፍ ወርክሾፕ ላይ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ ብዙ ባለሙያተኞች እቤታቸው በመጡ ቁጥር በአድናቆት እንደመለከቱ አድርገዋል፡፡

ይህን ማሽን ከዚህ በላይ ለማስተዋወቅ ከአቅማቸው በላይ ነው፡፡ ሰሞኑን በስልክ ሳናግራቸው  አሁን ይህንን ባለበት ትተው ሌላ ሥራ የሚሠራ ሌላ የማሽን ፈጠራ እና የማሻሻል ሥራ ጀምረዋል፡፡  የፈጠራ ሰው መቸም እረፍት የለውምና አሁንም ሌላ ማሽን መጀመራቸው ገረመኝ፡፡  

ይህን ማሽን ለብዙዎች የጤፍ አርሶ አደሮች ተደራሽ ማድረግ ሌላ ከባድ ሥራ ነው፡፡  በዚህ ማሽን ተስፋ በማየቴ ሌሎችም ይሰሙት ዘንድ ይህንን ፃፍኩኝ፡፡ አንብቦ፤ ሰምቶ አስተያየት ያለው፣ ሥራውን ማገዝ ያሰበ፣  ማየት የፈለገ፣ ወዘተ ወለንጪቲ ከተማ የቦሰት ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት  ብቅ ማለት ይችላል፡፡ ቀጥሎም ከማሽኑ ሠሪ እና ቤተሰባቸው ብዙ ነገረጉዳይ መሥማት ይችላል፡፡

የጤፍ ነገር ……..

Reference:

Solomon Chanyalew, Worku Kebede, Dejene Girma, Zerihun Tadele and Kebebew Assefa (eds.). 2020. Tef Improvement: From Where to Where, Proceeding of the Third International Ttef Workshop, 22-24 October 2019, Ethio-Resorts, Bishoftu, Ethiopia

http://127.0.0.1/web-ebr/archives/5774        ብሥራተ ጤፍ፣

http://127.0.0.1/web-ebr/archives/3019  የእንጀራ ጉዳይ

https://www.youtube.com/watch?v=4EV0Yev5EGE  የጤፉ ጉዳይ፣ ይድረስ ለግብርና ሚ/ር

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com