ዜና

ግዳጃችንን በላቀ ወኔ ለመወጣት ተዘጋጅተናል

Views: 44
ኢንስፔክተር ቾል መኳች የህወሃት የሽብር ቡድንን የጥፋት ተልኮ ለመመከት ወደ ግዳጅ ቀጠና ለሚሰማራው ከጋምቤላ ክልል የሁለተኛው ዙር ዘማች የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት መካከል አንዱ ናቸው።
ቀደም ሲል ወደ ግዳጅ ቀጠናው ከተቀላቀሉት የክልሉ ልዩ ኃይል ጋር ባለመሄዳቸው ቅሬታ አድሮባቸው ነበር።
አሁን እድሉን በማግኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ በላቀ የሀገር ፍቅር ስሜትና ወኔ ነው ኢንስፔክተር ቾል የገለጹት።
አሸባሪው ቡድን ሀገር አፈርሳለሁ ብሎ የጀመረውን ትንኮሳ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ ሁሉም አባላት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ሰርጎ ገቡ አሸባሪ ቡድን በሀገራችን ላይ የከፈተውን ጦርነት ለመቀልበስ እየተካሄደ ባለው ተጋድሎ በመሳተፍ በላቀ ወኔ ግዳጃችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ያሉት ደግሞ ምክትል ሳጅን መሐመድ ሙሃሙድ ናቸው።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው አሸባሪው ቡድን ባለፉት 27 ዓመታት በጋምቤላ ክልል ብሎም በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ሲፈጽመው የቆየው ግፍና የፖሊተካ ሴራ ሳያንሰው አሁን ደግሞ ሀገርን ለማፍረስ የጥፋት ሴራውን ቀጥሎበታል ብለዋል።
መንግስት ለህዝቡ ሰላምና መረጋጋት በማሰብ ያደረገውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የጥፋት ኃይሉ አሻፈረኝ በማለት ሀገር ለማፍረስ በአማራና በአፋር ክልሎች ጠብ አጫሪ ድርጊቶችን መፈጸሙን አመላክተዋል።
አሸባሪ ቡድኑ ሀገር ለማፍረስ የጀመረውን ትንኮሳ ለመቀልበስ የክልሉ ሁለተኛው ዙር ልዩ ኃይል ቀደም ብለው እንደዘመቱት ሁሉ ከሀገር መከላከያ እና ሌሎች የጸጥታ አካላት ጎን በመሰለፍ ግዳጃቸውን በላቀ ቁርጠኝነት እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሁለተኛው ዙር የጋምቤላ ክልል የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት ትናንት ምሽት የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል።
Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com