ዜና

ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን እና የኢትዮጵያ አንድነት- ከታሪክ ትውስታ ጋር

Views: 57

መስፍን ታደሰ (ዶክተር)

(የፎቶግራፉ ባለቤት፣ አንድሬ ሻዤክ እኤአ በ፳፻፱ የተነሳ)

በዚህ ጽሑፍ ለማንሳት የፈለግኩት ሁለት ጉዳዮችን ነው። አንደኛው ቀደም ብዬ እንደጻፍኩት፣ አዲስ አበባ ውስጥ ያሉን አስደናቂ ሕንጻዎች ማን ሰራቸው ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ከታሪክ አኳያ፣ ይህ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ለኢትዮጵያ አንድነት ያበረከተውን አስተዋጽኦ በማንሳት፣ የአሁኑም ትውልድ ስለ አንድነት እና ስለ ሰላም ሲል እንዲተጋና እንዲሰራ ነው። የአብሮነትን፣ የኢትዮጵያዊነትን ዋጋን በአጽንኦት ለመግለጽም ጭምር ነው።

የአሁኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወይም አራዳ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አሁን በያዘው ቅርጽ ከመሰራቱ በፊት ሌላ መለስተኛ ከእንጨት፣ ከድንጋይ እና ከጭቃ የተሰራ ቤተክርስቲያን ከአስራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በቦታው እንደ ነበር ከታሪክ ጸሐፊዎች እና ከቅሪት አጥኚዎች (አርኪኦሎጂቶች) ድርሰቶች ለማወቅ ይቻላል።

የቅዱስ ጊዮርጊስን ቤተክርስቲያን እንደገና ያሰሩት አፄ ምኒልክ እኤአ በ፲፰፺፮ ነበር። ሰራዊታቸውን ይዘው ወደ አድዋ ሲዘምቱ ታቦቱን ይዘው ነበር የሄዱት።

ጣልያንን ድል በማድረጋቸው የታቦቱን ድል አድራጊነት አስነግረው ነበር። ቂም የያዘው ፋሽስት ጣልያን ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ መጥቶ አዲስ አበባን በተቆጣጠረበት በ፲፱፻፴፯ ቤተክርስቲያኑን አቃጠለው።

የኢትዮጵያ አርበኞች፣ የእንግሊዝ እና የአፍሪካውያን ወታደሮች እርዳታ ታክሎበት፣ ጣልያንን ድል ካደረጉ በኋላ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ቤተክርስቲያኑ እንደገና እኤአ በ፲፱፵፩ እንዲታነጽ አደረጉ።

በስእሉ ላይ የሚታዩት ሰዎች በአዲስ አበባው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ተገኝተውና ጎን ለጎን ሆነው ፀሎት የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያን ናቸው፣ እስላሞችና ክርስቲያኖች በአንድነት ነበሩ። ጊዜው በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት፣ ፀሎታቸው ስለ ሰላም ነበር። አሁንም ሰላም ለመላ ኢትዮጵያውያን ይሁን።

ስዕሉን ከአምስት አመታት በፊት የላከልኝ ወዳጄ ታደሰ ተገኝ ነው። አሁንም ምስጋናዬ ይድረሰው። ከስዕሉ ጋር አብሮ በላከው መልእክት እንዲህ ብሏል። “ወሎ ውስጥ፣ ለክርስቲያን ወለዬዎች ወልዲያ ገብርኤልን ያሰሩት ሙስሊሙ ራስ አሊ ነበሩ። የጓደኛዬ አባት (ሙስሊም ናቸው) በየአመቱ በዚህ ቤተክርስቲያን ነዋሪውን ይዘክራሉ። እኛም የፈለገብርሃን መለስተኛ አንደኛ ደረጃ ማስፋፊያ ማህበር አባላት ሙስሊም ኢትዮጵያውያንን ለመርዳት ባሌ፣ መስቀል ድርኪና ያለን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መርዳት ጀመርን፣ የሽንት ቤት ልንሰራ እና የውሃ ቧንቧ ልናስገባ ተዋዋልን።

የአካባቢው ነዋሪዎች ሙስሊም ወንድሞቻችን ናቸው። አዎን በዝርያ፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ ወዘተ፣ ሕዝብን ለመከፋፈል የሚፈልጉ አሉ፤ ይኖራሉም፡፡የተፈጥሮ ሕግ ነውና። ነገር ግን አብሮነትን፣ አንድነትን፣ ወንድማማችነትን፣ እህትማማችነትን ሊንዱና ሊያስወግዱ አይችሉም! አይሆንላቸውም። እንዲሳካላቸው አንፈቅድም! ነው የሚለው የሰው ልጅ የሆነና አሳቢ የሆነ አእምሮ ያለው ኃይል ሁሉ፡፡”

እናንተ ሰላማዊ ሰው የምታርዱና የምታሳድዱ ለመሆኑ ምንድን ናችሁ!? ኢትዮጵያዊ ይህን አያደርግም፤ ማን አስተማራችሁ!? ታረሙ፣ ማንበብ ከቻላችሁ ፈጣሪያችሁ ይቅር ይበላችሁ።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com