ዜና

አሜሪካን ያልተመቻት ምንድ ነው?

Views: 89

አሜሪካን ያልተመቻት ምንድ ነው?

ክፍሉ ታደሰ

ሐምሌ 16 2013 ዓም (Jul 23, 2021)

ሰኔ 21 2013 ዓም (Jun 28, 2021) የኢትዮጵያ መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም በማድረግ፣ በድንገት ከመቀሌና ከዋና ዋና የትግራይ ከተሞች ለቆ ወጣ፡፡ ይህ የመንግስት ድንገተኛ እርምጃ አንዳንድ ወታደራዊ ጠቀሜታዎች የሚኖሩት ቢሆንም፣ ውሳኔው የኢትዮጵያ ሕዝብን አስደነገጠ፡፡ ህወሃትና ደጋፊዎቹ በወሰዷቸው እርምጃዎች አንዳንድ የመንግስት ደጋፊ ተብለው በሚቆጠሩ ወገኖች ላይ ጉዳት ደረሰ፡፡ በተለያዩ የትግራይ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪ የሆኑ ወጣቶች ለአደጋ ተጋለጡ፡፡

መንግስት የወሰደውን ይህን እርምጃ ህወሃት አልተቀበለውም፣ እንዲያውም መሳለቂያ አደረገው፡፡ የምዕራብ ሀገሮች መንግስታትም ጦርነቱ እንዲቆም ሲወተውቱ የቆዩ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደው እርምጃን ብዙዎቹ በዝምታ ለማለፍ ወሰኑ፡፡ ከሰኔ 21 በኋላ በነበረው ጊዜ የህወሃት ሃይሎች ያካሂዱ የነበሩትን መጠነ-ሰፊ ግድያ፣ ትንኮሳ፣ አፈና፣ የስደተኛ ጣቢያዎች ወረራ፣ ወዘተ፣ ባላየ፣ ባልሰማ አለፉት፡፡ ከነአካቴው፣ የህወሃት  ኃይል የአማራ ክልልን ሲወር፣ ቡድኑ “እንዲታቀብ” በመገሰጽ ፈንታ የሚያበረታታ መግለጫ ሰጡ፡፡ ይባስ ብለውም በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል በመሰናዳት ላይ ናቸው፡፡ በተጨማሪ፣ ዋና ዋና የምዕራቡ ዓለም ሚድያዎች፣ ሙያዊ ግዴታቸውንና ሃላፊነታቸውን በመዘንጋት የሃሰትና ወደ አንድ ወገን ያጋደሉ ዜናዎች ሲያስተላልፉ ከረሙ፡፡ አሁንም እያስተላለፉ ናቸው፡፡ ይህ የሚድያዎቹም ሆነ የምዕራቡ ሀገራት አካሄድ ህወሃት በጥቅምት ወር የሰሜን ዕዝ ላይ መጠነ ሰፊ እርምጃ ከወሰደ ጊዜ ጀምሮ ሲስተዋል የነበረ ሲሆን፣ ለሰብአዊ መብት ተሟጋች ነኝ የሚለው የምዕራቡ ዓለም ይህ ከባድ የሽብር እርምጃ ሲወሰድ አንድም ተቃውሞ አላሰማም፡፡ በማይካድራ ላይ በመቶዎቹ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በግፍ ሲጨፈጨፉም ምንም አልተነፈሰም፡፡

ሰኔ 21 ቀን መንግስት ተኩስ በማቆሙ፣ ትግራይ ውስጥ ገጥመውት የነበሩትን የተለያዩ ችግሮች ከጫንቃው ላይ አነሳ፡፡ ኳሱንም ወደ ህወሃት ሜዳ ወረወረ፡፡ የፖለቲካ አካሄዱ የገባው የምዕራቡ ዓለምም ሆነ ህወሃት ተደናገሩ፡፡ የምዕራቡ ዓለም ክሱን አላቋረጠም፣ ህወሃትም ጦርነቱን ቀጥላለሁ አለ፡፡ ይህ ሁኔታም፣ የችግሩ ስረ-መሰረት ከትግራይ መውጣት አለመውጣት፣ ጦርነት ማቆም ወይም አለማቆም ጋር የተያያዘ ሳይሆን ከዚያ የዘለለ መሆኑን አመላከተ፡፡ ብዙዎቻችን ልብ አላልነውም እንጅ፣ ለ6ተኛው ዙር ምርጫ ዝግጅት ይደረግ በነበረበት ወቅት፣ የምዕራቡ ዓለም ምርጫው ዲሞክራሲያዊ ሊሆን ስለማይችል በዚያ ፈንታ የብሄራዊ እርቅ መደረግ አለበት ሲል ገለጸ፡፡ ሰሚ አላገኘም፤ 40 ሚልዮን የሚገመት ሕዝብ፣ ብርዱንና ዝናቡን ተቋቁሞ ድምጹንና ፍላጎቱን ገለጸ፡፡ ከምርጫው ሰላምን መሻቱን አሳወቀ፡፡Will parties' merger change Ethiopia's political landscape? - WardheerNews

በእርግጥ ምርጫው በትግራይና በአንዳንድ አካባቢዎች አልተካሄደም፡፡ የተወሰኑ ብሄረተኛ ድርጅቶች በምርጫው እንደማይሳተፉም አሳውቀዋል፡፡ ከ40 ሚልዮን ሕዝብ በላይ ድምጽ ቢሰጥም፣ የምዕራቡ ዓለም ሃሳቡን አልቀየረም፡፡ የጎደለው ይሟላ፣ ያልመረጡ ድምጻቸው ይሰማ አላለም፡፡ ምርጫው ሀሉንም ስለማያካትት ለብሄራዊ ዕርቅ ድርድር መካሄድ አለበት በሚለው ሃሳቡ ገፋበት፡፡ ይህ የገደምዳሜ አነጋገር የሚጠቁመው፣ ድርድር ተካሂዶ ህወሃት ዳግመኛ የፖለቲካ ሥልጣን ተጋሪ መሆን አለበት የሚል ነው፡፡ ጉዳዩን ጠለቅ ብለን ስናየው፣ የሰሜን ዕዝ ላይ መጠነ-ሰፊ ጥቃት ሲካሄድም ሆነ ህወሃት የማጥቃት እርምጃ ሲጀምር የምዕራቡ ዓለም ከፍተኛ ባለሥልጣናት አያውቁም ወይም ህወሃት በግሉ ብቻ ወስኖ ያካሄደው ነው ብሎ ማሰብ/መገመት የዋህነት ነው፡፡ ጉምቱ የሆኑና በተባበሩት መንግስታትና በሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ የህወሃት የቀድሞ አባላት የጦርነቱ ዋነኛ ተሳታፊ እንዲሆኑ ሲደረግ፣ “እዚያ ማዶ ጭስ ይጨሳል…” ብሎ ማሰብ ተገቢና አስፈላጊ ነበር፡፡ በአጭሩ፣ የህወሃት ጦርነትም ሆነ የሚወስዳቸው እርምጃዎች በተናጠል ያደረገው ሳይሆን የምዕራቡ ዓለም ይሁንታን አግኝቶ ያካሄዳቸው ናቸው ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ እንዲያውም፣ የምዕራቡ ዓለም ፍላጎቶችን የሚያሟላ እርምጃ ነው ብሎ ማሰብ ይቻላል፡፡

የምዕራቡ ዓለም ኩርፊያና የጠ/ሚኒስቴር ዓብይ መንግስት

የምዕራቡ ዓለምና የህወሃት ግንኙነት የተጀመረው፣ በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ ለዛፍ ተከላ ተብሎ ከአሜሪካ በተበረከተ ገንዘብ አማካይነት ሲሆን፣ ቀሰ በቀስ ግንኙነቱ እየተጠናከረ ሂዶ፣ “…በተለይ ከ1977 ዓም ጀምሮ ስፍር ቁጥር የሌለው እርዳታ ለህወሃትና ለህዝቡ ለግሰዋል፡፡ የተለያዩ የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች የቁሳቁስና የገንዘብ እርዳታ የሚሰጡ ድርጅቶችና መንግስታት ቁጥራቸው እየጨመረ ሂዶ ነበር” ይላል “ሉዓላዊነትን ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ” የተባለው መጽሐፍ ደራሲ፣ የቀድሞ የህወሃት አመራር አባል የነበረው አቶ ገብሩ አስራት፡፡ (ኢትዮጵያ ሆይ፣ ክፍሉ ታደሰ፣ ገጽ 145) በጥቅሉ ህወሃት የምዕራቡ ዓለም ጉዳይ አስፈጻሚ ሆኖ እንዲወጣ ሰፊ ስራ የተሰራበት ሲሆን፣ ቁጥራቸው ስንት እንደሆነ በውል የማላውቀው የምዕራቡ ዓለም ወኪሎች በትግራይ በረሃዎች ከህወሃት ጋር ከርመዋል፡፡ ከእነዚህ መሀል አንዷ ጌይል ስሚት ትባላለች፡፡ ለአቶ መለስ ዜናዊ ቅርብ የነበረችው ጌይል ስሚት፣ ኋላ ላይ ሬስት የተባለው የህወሃት የእርዳታ ድርጅት አማካሪ ተደረገች፡፡ ህወሃት ሥልጣን ከያዘ በኋላ የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት አባል የሆነችው ጌይል፤ እአአ በ2009 ዓም፣ 20 ቢልዮን ዶላር ያንቀሳቅስ የነበረው ዩኤስ ኤድ የተባለው ድርጅትን እንድትመራ በፕሬዚዳንት ኦባማ ተመረጠች፡፡ በሌላ በኩል፣ የጌይል የቅርብ ረዳቷና ወደጇ ሱዛን ራይስ፣ በባይደን አስተዳደር ውስጥ የአገር አስተዳደር ምክር ቤት አባል ስትሆን፣ በፕሬዚዳንት ኦባማ አስተዳደር ዘመን የሷ ምክትል የነበረው ብሊንከን ደግሞ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው፡፡ ሱዛን ራይስ የአቶ መለስ አድናቂ የነበረችና ከመንግስታቸው ጋር በቅርበት ትሰራ የነበረች ስትሆን እነዚህ ሹመኞችን የማነሳው ከህወሃት ጋር የሚደረገው እሰጥ አገባ ምን ያህል ፈታኝና የአቀበት ጉዞ እንደሆነ ለማሳየት ነው፡፡

አሜሪካን ያልተመቻት ምንድ ነው?

 • አሜሪካ ኮትኩታ ያሳደገችው ድርጅት፣ እአአ በ2010 ዓም ከሥልጣኑ እንዲነሳ ሲደረግ፣ አጋጣሚው መብረቃዊና ዝግጅት ያልተደረገበት በመሆኑ ህወሃትን ያስደነገጠውን ያህል ለምዕራቡ ዓለም አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ሥልጣን ላይ የወጣው የዓብይ መንግስት ባህሪና አካሄድ ገና ግልጽ ስላልነበረና የደፈረሰው እስኪጠራ ድረስ መጠበቅ ግድ ነበር፡፡ በዚህ መሀል ለጠ/ሚኒስቴሩ የኖቤል ሽልማት ተበረከተ፡፡ “ዶሮን ሲደልሏት…” እንደማለት መሆኑ ነው፡፡
  • ጠ/ሚኒስቴሩ ብሄረተኛነትንና ኢትዮጵያዊነትን በግራና በቀኝ እጃቸው ይዘው ሁለቱንም በማስተናገዳቸው፣ አካሄዳቸው የምዕራቡ ዓለምን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያንንም ግራ አጋባ፡፡
  • በጊዜ ሂደት የጠ/ሚኒስቴሩ አካሄድ ይበልጥ ግልጽ እየሆነ፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የሚያስቀድሙ መሆናቸውን ይፋ እያደረጉ ሲሄዱ ጎራቸው እየለየ መጣ፡፡ ብሄረተኛውን ህወሃትን ሲደግፍ የቆየው የምዕራቡ ዓለም ሃሳብ የገባው መሰለ፡፡ ኢትዮጵያን ሊያስቀድም የሚችል ኃይል የበላይ ሆኖ መውጣቱ በምዕራቡ ዓለም ፖሊሲዎች ላይ ምን ጫና ሊያሳድር እንደሚችል አርቆ አሰበ፡፡
  • ከህወሃት ጋር የሰሩና ምናልባትም የጥቅም ተጋሪ የነበሩ የምዕራቡ ዓለም ባለሥልጣናት ይህ አዲስ ሁኔታ ሊመቻቸው እንደማይችል ሲገነዘቡ፣ “ይቺ ባቄላ…” ማለት ጀመሩ፡፡
 • ከምስራቁ ዓለም በተለይም ከሩስያና ከቻይና ጋር ኢትዮጵያ እያጠናከረች የሄደችውን ግንኙነት የምዕራቡ ዓለም በግዴለሽነት አልተመለከተውም፡፡ ቻይና ክፉኛ መመንደጓ ያሳሰበው የአሜሪካ መንግስት፣ ችግሩን ለመቋቋም የተለያዩ መላዎች መፈለግ ጀመረ፡፡ አንደኛው ዘዴም ጀርመንና ጃፓን በአፍሪቃ ውስጥ ጎላ ያለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ማሳሰብና መጎትጎት ሲሆን፣ ይህን በመሰለ ስራ ላይ የተሰማራ አንድ ሰው ጉዳዩን ዘርዘር አድርጎ አጫውቶኛል፡፡ ይህ ሰው፣ በጃፓን መንግስት ስር ባለ የልማት ድርጅት ውስጥ ሲሆን የሚሰራው፣ የመስሪያ ቤቱ ዋና ትኩረት የጃፓን ኢንቨስትመንትን በአፍሪቃ ማስፋፋት ነበር፡፡
 • ሌላውና ዋነኛ የትኩረት ጥያቄ ከኤደን ባህረ ሠላጤ፣ ወይም በአረብኛው ባብ ኤል መንደር ጋር የተያያዘው ሲሆን፣ በሜዲተራንያን ባህር አድርጎ፣ ቀይ ባህርን አቋርጦ ሕንድ ውቅያኖስ የሚገባው የባህር ላይ የንግድ መስመር ጠቃሚነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱ ነው፡፡ ይህ ቀጭን ባህረ ሠላጤ፣ በአንድ በኩል በአረብ ባህረ ገብ መሬት (Arabian Peninsula)፣ በሌላ ደግሞ በአፍሪቃ ቀንድ መሀል ይገኛል፡፡ ባህረ ሠላጤውም ሆነ አካባቢው የተለየ ትኩረት ያገኘው ሽፍቶች መርከብ በማስቆም በገንዘብ መደራደር ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ሲሆን፣ በርካታ ግዙፍና ሀብታም አገሮች ትኩረታቸውን ጥለውበታል፡፡
 • ዋና ዋናዎቹ፣ ቻይና፣ አሜሪካ፣ ሩስያ፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ቱርክ፣ ኢራን፣ ኤሚሬቶችና ሌሎች የአረብ አገሮች ናቸው፡፡ ይህ ቀጠና ከፍተኛ ርኩቻ፣ ፉክክርና ትንቅንቅ የሚካሄድበት ከባቢ ሲሆን፣ የቻይና እና የአሜሪካ ጉዳይ ጎልቶ ይታያል፡፡ የአረብ አገሮቹ ዋነኛ ትኩረት፣ የመሰረተ ግንባታ፣ ሪል ኤስቴት፣ እርሻና ሌሎች ግንባታ ነክ የሆኑ የኢኮኖሚና ጂኦፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ሲሆን፣ ቻይና እና አሜሪካ፣ ከኢኮኖሚ በዘለለ ወታደራዊና ሌሎች ጉዳዮች ላይ አተኩረዋል፡፡ ዱባይ ወደብ (ዱባይ ፖርትስ) የተባለው በጅቡቲ፣ ኤርትራ (አሰብ)፣ ሶማሌ (ኪስማዩ)፣ ሶማሌላንድ (በርበራ) ላይ የወደብ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ እአአ እስከ 2017 ዓ.ም ባለው ጊዜ፣ እነዚህ የገልፍ አገሮች (Gulf States) በሱዳንና ኢትዮጵያ ብቻ 13 ቢልዮን ዶላር ኢንቬስት አደረጉ፣ 7 ቢልዮን የሚሆን እርዳታ ሰጡ፡፡
 • ወደ አካባቢው በመጡ አገራት መሀል ፉክክሩና ፍትጊያው እየጠነከረ በመሄዱ፣ የወታደራዊ የጦር ሰፈሮችና የባህር ሃይል ግንባታው እየተጧጧፈ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያና የቻይና ግንኙነትChina cancels Ethiopia's interest-free loans, PM in Beijing for forum | Africanews

በቅርቡ ጅቡቲና ኢትዮጵያ ባደረጉት ስምምነት፣ ኢትዮጵያ የምታመርተው የተፈጥሮ ጋዝ፣ በቻይና ኩባንያ በሚገነባውና ቀይ ባህር ላይ በሚገኘው የጅቡቲ ወደብ በኩል እንዲከፋፈል ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ኢትዮጵያ ከቻይና በወሰደችው ብድር ብዛት ከጅቡቲ ቀጥላ ሁለተኛ ስትሆን፣ የገንዘቡ መጠንም 16 ቢልዮን ዶላር አካባቢ ነው፡፡ ከ200 ሚልዮን ዶላር በላይ የፈጀው የአፍሪቃ ህብረት ህንፃ አዲስ አበባ ነው የሚገኘው፡፡ የቻይና የንግድ ሚኒስቴር ወኪል፣ ቻይና ለአፍሪቃ የምትሰጠውን ፈንድ የሚመራው አካልና ሺንዋ የተባለው የቻይና የቀጠናው የዜና ወኪል ቢሮዎች አዲስ አበባ ናቸው፡፡

በመገንባት ላይ ያሉት የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ሀዲድና የውሃ ቧንቧ እንዲሁም 500 ሚልዮን ዶላር አካባቢ ያወጣው የአዲስ አበባ የባቡር መስመር፣ የቀለበት መንገዱ፣ የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በቻይና ነው የተገነቡት/የሚገነቡት፡፡

በቻይና የገንዘብ እርዳታ ጭምር የተገነባው የምርምር ሳተላይት፣ ሻንሲ በተባለ የቻይና ክፍለ ሀገር ነው የሚገኘው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የህዳሴ ግድቡ ስራ እንዲቀላጠፍ በማሰብ፣ የቻይና ኩባንያ በተቋራጭነት እንዲሰራ ተደርጓል፡፡

ከላይ የተጠቀሰው እንዳለ ሆኖ፣ እአአ በ2017 ዓም ጅቡቲ ላይ ቻይና የወታደራዊ አምባ ስትመሰርት ነበር አሜሪካ የባነነችው፡፡ የሁለቱ አገሮች ወታደራዊ የጦር ሰፈሮች አጠገብ ለአጠገብ መገንባታቸው “ትልቅ ተግዳሮት” ነው አሉ በጅቡቲ የአሜሪካ አምባሳደር፣፡፡ ጅቡቲ ከቻይና ጋር ያደረገችው ሽርክና “የአሜሪካን እንደልብ መንቀሳቀስና ተሰሚነት ያኮስሳል” ሲሉ በአፍሪቃ የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል መሪ ለአሜሪካ ኮንግረስ ተናገሩ፡፡ ከሁለት አመት በፊት ልዑክ መርተው ጅቡቲ የሄዱት ሴኔተር ኢንሆፌም ደስተኛ አለመሆናቸውን አሳወቁ፡፡

ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎች በቻይና እና በኢትዮጵያ መሀል የሚደረጉ መቀራረቦች ናቸው የአሜሪካን መንግስት ሊያስከፉ የሚችሉትና የጠ/ሚኒስቴር ዓብይ መንግስትን በጥርጣሬ ዓይን እንዲታዩ ያደረጓቸው/የሚያደርጓቸው፡፡ ሌላ ጉዳይም አለ፡፡

የአፍሪቃ ክንድን መመስረትFree Horn of Africa Editable Map - Free PowerPoint Template

ሱማሌ፣ ሱማሌላንድ፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራና ኢትዮጵያን ጨምሮ “የአፍሪቃ ቀንድን፣ የአፍሪቃ ክንድ” እናደርጋለን የሚለው የጠ/ሚኒስቴር ዓብይ ራዕይ ስራ ላይ ከዋለና አሰሪ የጋራ ፖሊሲ መንደፍ ከተቻለ፣

 • የሕዝብ ቁጥሩ ወደ 150 ሚልይን የሚጠጋው ይህ አካባቢ፣ ለብልጽግና መሰረት ይሆናል፡ አካባቢው ትልቅ ገበያ ሊሆን ከመቻሉ በላይ፣ ቀይ ባህርና የሕንድ ውቅያኖስ ላይ መገኘቱ ተጠቃሚነቱን ያጎላ፣ በየብስ ላይም ሆነ በባህር ውስጥ በርካታ የልማት ስራዎች ሊከናወኑ ይችላሉ፣
 • በአንድነት የተሰባሰቡት እነዚህ አገራት ጠንካራ የወታደራዊና የባህር ሃይል ለመመስረትና ለማስተዳደር ጉልበቱም አቅሙም ይኖራቸዋል፣

ከህዝብ ቁጥር ባለፈ፣ በኢኮኖሚ ሊጎለብቱ ከቻሉ ነፃነታቸውን፣ ልዑላዊነታቸውንና ክብራቸውን ያሰከብራሉ፤ ጥቅማቸውን ያስጠብቃሉ፣

 • አካባቢው የጦርነት ሳይሆን ወደ ሰላም ቀጠናነት ሊቀየር ይችላል፡፡
 • ለአህጉሩ ተምሳሌት በመሆን፣ ሌሎችም ተመሳሳይ እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በዩጋንዳ፣ ኬንያና ታንዛኒያ በመመስረት ላይ ካለው የምስራቅ አፍሪቃ ሕብረት ጋር መልካም የስራ ግንኙነት ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎች ትሩፋቶች የኃያላኑን ጥቅሞች የሚጋፉ በመሆናቸው በበጎ ዓይን የሚታዩ አይደሉም፣

ጦርነቱና የምዕራቡ ዓለም

ከላይ በተዘረዘሩትና ባልተጠቀሱ ሌሎች ኩነቶች ምክንያት፣ ህወሃት ጦርነቱን የለኮሰው በራሱ ተነሳሽነት ብቻ ነው ብሎ ማመን ያስቸግራል፡፡ ማስረጃዎች ባይኖሩም፣ አመላካች መረጃዎች ላይ በመንተራስና ከታሪክ በመማር፣ የኃያላን አገራትን ጥቅምና ፍላጎት ተጻሮ መቆም ውጤቱ አስከፊ፣ መዘዙም ሰፊ ነው፡፡ ከጥቂት ጊዜ በፊት የአሜሪካ መንግስት ይፋ ያደረጋቸው (ዲክላሲፋይድ ሰነዶች)፣ እአአ በ1973 ዓም በደቡብ አሜሪካ በምትገኘው በቺሊ የተካሄደው መፈንቅለ መንግስትና በሕዝብ የተመረጡት ሳላቫዶር አዬንዴ እንዴት እንደተገደሉ፣ የአሜሪካ የስራ አስፈጻሚው አካል መሪ የነበሩት ፕሬዚዳንት ኒክሰንና ሄንሪ ኪሲንጀር ምን ያህል ተሳታፊ እንደሆኑ ያሳያል፡፡ ሲገደሉ፣ ከተመረጡ ብዙም አልቆዩም ነበር ፕሬዚዳንት አዬንዴ፡፡ ወንጀላቸውም፣ ከኩዩባ ጋር ግንኙነት ሊፈጥሩ ይችላሉ መባሉና የምዕራብ አገሮች ባለሀብቶችን የሚጻረር ፖሊሲ አላቸው የሚል ነበር፡፡

ህወሃት ጦርነቱን ለመጀመር የተጋነነና እርካብ ያልረገጠ ሃሳብ ላይ ተመስርቶ ማድረጉ ግልጽ ሲሆን፣ ያን ትንታኔውን ለምዕራቡ ዓለም አቅርቦ ሊሆን ይችላል ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ ወዲያም አለ ወዲህ ግን፣ የምዕራቡ ዓለም እየተከተለ ያለው አፍቃሪ ህወሃት ፖሊሲ እንዲቀይር ጥረት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

መልሶ የማጥቃት ዘመቻው

ህወሃት ከመንግስት የተሰጠውን ዕድል ሊጠቀምበት አልቻለም፡፡ በእርግጥ የመንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም ፖሊሲ አፈጻጸሙ ላይ አንዳንድ ህጸጾች ቢኖሩበትም፣ ችግሮቹን ሁሉ ህወሃት ትከሻ ላይ አራገፈ፡፡ ያን ሃላፊነት ለመሸከምና ለመወጣት ያልፈለገውና ያልቻለው ህወሃት በጀመረው ወረራ ለመቀጠል ወሰነ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም ቀፎው እንደተነካበት ንብ በአንድነት ተነሳ፡፡ በነገራችን ላይ፣ ባለፉት 130 አመታት ታሪኩ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአመዛኙ በራሱ ተነሳሽነት ሆ ብሎ የተነሳው አራት ጊዜ ነው፡፡ ለአድዋ፣ ለማይጨው፣ ለሱማሌ መንግሰት ጦርነትና ለህወሃት፡፡ ሶስቱ ከውጭ ጠላቶች ጋር የተካሄዱ ሲሆኑ፣ የአሁኑ ግን ከሀገር በቀሉ ከህወሃት ጋር ነው፡፡ ይህ ሁኔታ የሚያመላክተው ግጭቱ ከመንግስት ወይም ከአማራው ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ከመላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር መሆኑ ነው፡፡

ህወሃት ተኩስ ለማቆም አለመፈለጉ የሚያመላክተው ጉዳይ ቢኖር፣ አንድም ትዕቢተኛነቱን፣ ቀጥሎም፣ ያቺ የዛሬ 3 አመት ያጣት ሥልጣን ላይ ተመልሶ ካልተፈናጠጠ አርፎ ሊቀመጥ አለመቻሉን ነው፡፡

የመልሶ ማጥቃት ዘመቻው ሶስት ዘርፎች እንዲኖሩት ቢደረግ በተሳካና አጠር ባለ ጊዜ ሊጠናቀቅ ይችል ይሆናል፡፡ በነገራችን ላይ፣ ከመጀመሪያው የሶስት ሳምንት ወግያ በኋላ ህወሃት እንደ አመድ ተበትኗል ብለው ጠ/ሚኒስቴር ዓብይ የተናገሩት የደፈጣ ውጊያን ባህሪ (guerilla warfare)  አይገልጽም፡፡ እንደ አመድ እንዳልተበተነ አይተናል፡፡ የማጥቃት ዘመቻውም ረዥም ጊዜ ሊፈጅ ይችላል፡፡ ጊዜውን ለማሳጠር ይረዳሉ የምላቸው ሃሳቦችን ላንሳ፡፡

ዘርፍ 1

የመልሶ ማጥቃቱ የመጀመሪያ እርምጃ ዲፕሎማሲን የሚመለከት ሲሆን፣ አካሄዶቹ በሁለት ሊከፈሉ ይችላሉ፡፡ ሁለተኛው ህወሃትን ከትግራይ ህዝብ መነጠል ይሆናል፡፡ ሶስተኛው፣ ህወሃት ትንኮሳ አቁሞና መሳሪያውን አውርዶ ለሰላም ተገዥ መሆኑ እስከሚረጋገጥና ሌሎች ለሰላም የሚደረጉ ስምምነቶችን እስከሚቀበልበት ጊዜ ድረሰ ሊቀጥል ይችላል፡፡ ይህን አልቀበልም ብሎ አሻፈረኝ ካለ ሂደቱ ይቀጥላል…

አካሄድ 1- ዲፕሎማሲ ተኮር ስራ ማከናወን

የአጭር ጊዜ ትልም

 • የምዕራቡ ዓለም ከሚያላዝንባቸው ጉዳዮች አንዱ የወልቃይትና የራያ ጉዳይ በመሆኑ፣ በሁለቱም አካባቢዎች ሕዝበ ውሳኔ አካሂዶ ለአንዴና ለሁልጊዜ ለጉዳዩ ህጋዊ እልባት ማበጀት ተገቢ ነው፣
 • የአፍሪቃ አገራትን ማዕከል ያደረገ ሰፊ የዲፕሎማሲ ስራ ማካሄድ፣
 • የኢትዮጵያ መንግስትን ሊወክሉና ሁኔታውን በሚገባ ሊያስረዱ የሚችሉ (ቢያንስ በእንግሊዘኛ ቋንቋ) ራሳቸውን መግለጽ የሚችሉ ኃላፊዎችን ያካተተ ልዩ የልዑክ ቡድን አቋቁሞ ወደተለያዩ የምዕራብ አገሮች መላክ፣ ከመንግስታቱ ውጭ የተለያዩ ተጽእኖ ፈጣሪዎች (ለምሳሌ የአፍሪቃ-አሜሪካውያን ስብስብ) ጋር እንዲመካከሩ ማድረግ፣
 • ተባባሪ ወደሆኑ አገሮችም ሌላ ልዑክ ልኮ ሁኔታውን እንዲያስረዱ ማድረግ፣
 • ወደ ጦርነት የወሰዱ ሁኔታዎችንም ሆነ በጦርነቱና ከዚያ ጋር ተዛማጅ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ጠንካራ ጽሁፍ/ቪድዮ ተዘጋጅቶ የልዑኩ አባላት ለሚመለከታቸው ሁሉ እንዲያደርሱ ማድረግ፣
 • በየሀገራቱ የሚሄዱት የልዑክ አባላት፣ በውጭ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያኖችን በመሰብሰብ መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ በማስረዳት፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሀገሩ አምባሳደር እንዲሆንና፣ ወዳጅ ከጠላት ሳይል በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለውን በደል እንዲያስረዳ ማድረግ፣
 • እንደ ዋሽንግተን ፖስት፣ ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ሎስ አንጀለስ  ታይምስና በመሳሰሉ ጋዜጦች ላይ ቢቻል ቃለ ምልልስ ማድረግ፣ ካልተቻለ ገጽ ገዝቶ የኢትዮጵያን ሁኔታ ማብራራት፣
 • ከላይ የተጠቀሱት ስራዎች ሊከናወኑ የሚችሉት የህወሃት ካድሬዎች በተሰገሰጉባቸው ኤምባሲዎች አማካይነት ሳይሆን በአዲስ መልክ በአፋጣኝ በተደራጀ የባለሙያዎች ስብስብ በመሆኑ ስራው ዛሬ መጀመር ይኖርበታል፣
 • ስራው በባለሙያዎች ሊሰራ ይገባል፡፡ ካድሬዎች ከዚህ ስራ እንዲገለሉ ማድረግ ተገቢና አስፈላጊ ነው፡፡

የረዥም ጊዜ የዲፕሎማሲ ትልም

 • በተመረጡ ሀገሮች ውስጥ፣ የአስተሳሰብና የቋንቋ ብቃት ያላቸው ባለሥልጣናት በመመደብ የተቀላጠፈ የዲፕሎማሲ ስራ መስራት ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡
 • በተወሰነ ጊዜ ወይም መረጃ በሚገኝበት ጊዜ በኤምባሲ ኃላፊዎች አማካይነት ለዜና አውታሮች ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት፣
 • በየጊዜው፣ በየአካባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን አመቺ በሆነ ዘዴ በመሰብሰብ ገለጻና ማብራሪያ መስጠት፡፡

አካሄድ 2- የዓለም የኃይል አሰላለፍን መፈተሸ

ዓለም ዳግመኛ በሁለት ጎራ፣ ማለትም የምዕራቡና የምስራቁ በሚል ስያሜ በመከፋፈል ላይ ይገኛል፡፡ ከፖለሲ ጋር በተያያዘ ምክንያትም ሆነ በሌላ፣ የአሜሪካ ተቀባይነት በተለይ በፕሬዚዳንት ትራምፕ ዘመን እየቀነሰ ሂዷል፡፡ ይህ ሁኔታም የምስራቁ ጎራን ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ የምዕራቡ ዓለም ለብዙ አመታት ሲጠቀምበት የነበረውን ፖሊሲ ለመፈተሸ አለመቻሉም ለደረሰበት ችግር ሌላ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡

በሀገር ልዑዋላዊነት ላይ የተመሰረተ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ ሁኔታዎች እስከፈቀዱ ድረስ ከሁለቱ ጎራዎች ጋር በጋራ መስራት ላይ ይሆናል፣ አንደኛው ፊቱን ሲያዞር ከሌላኛው ጋር ጠበቅ ያለ ግንኙነት መመስረት ተገቢ ነው፡፡ በአሁኑ ሁኔታም ይህን አሰራር መፈተሸ ተገቢ ሊሆን ይችላል፡፡

ሁልጊዜም ግን፣ አቅምና ጉልበት ለዲፕሎማሲ ስራ ዋልታ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ደሃን ማንም አይፈልገውም፡፡

ዘርፍ 2

ህወሃትን ከሕዝቡ መነጠል

ሁለተኛው አካሄድ፣ አሣን ከውሃ እንደሚባለው ህወሃትን ከሕዝቡ መነጠል ይሆናል፡፡ የሚነደፈው ስልትም ሆነ የሚድያ ስራ የትግራይ ሕዝብ ያለበት ስነ ልቦናዊ ሁኔታ ላይ መመስረት ይኖርበታል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ማስታወሻ ለማከል፣ የሂትለር የፕሮፓጋንዳ ሃላፊ የነበረው ጆሴፍ ጎብልስ ለሂትለር መነሳት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ናዚዎች በጦርነቱ ድል ከሆኑ በኋላ ራሱንና ቤተሰቡን ቢያጠፋም፣ የጀርመን መንግስት የእሱን አሰራር በመከተል የሶቭየት ሕብረትን ለመናደ ተጠቅሞበታል፡፡ አሰራሩም፣ በአመዛኙ የምዕራቡንና የምስራቁ ዓለምን የኑሮ ሁኔታ በማወዳደር ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ሁኔታም፣ የትግራይ አርሶ አደርንና የሌላውን፣ የትግራይ ተማሪዎችንና የወጣቱን ሁኔታና የሌላውን፣ ወዘተ ላይ የተመሰረተ የንጽጽር ስራ ቢሆን ሊጠቅም ይችላል፡፡

 

ዘርፍ 3

ዘርፍ 1 እና 2ን እያካሄዱ በህወሃት ላይ በደንብ የታቀደ፣ ብልህነት የተላበሰና ለሽምቅ ውጊያ የሚመጥን መላ ዘይዶ መንቀሳቀስ ተገቢና አስፈላጊ ነው፡፡ መጤን ያለበት ጉዳይ፣ ዛሬም ቢሆን በህወሃት የ17 አመት የሽምቅ ውጊያ ወቅት ወታደራዊ መሪ የነበሩ በርካታ ኃላፊዎች መኖራቸውን ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ዝርዝር ሃሳብ ማቅረብ ባይቻልም፣ አንዳንድ ጉዳዮችን ለማንሳት፣ ሸማቂ ኃይሉ ምግብ፣ መድኃኒትና መሳሪያ የሚያገኝባቸውን መስመሮች ከተቻለ መቁረጥ፣ ካልሆነም አስቸጋሪ ማድረግ ነው፡፡ ቀጣዩና ዋናው ስራ ግን፣ ሾህን በሾህ እንዲሉ፣ በሽምቅ ውጊያ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ማፍራት ኢትዮጵያን ግድ ይል ይሆናል፡፡

እንደ መደምደሚያ

በኢትዮጵያ በኩል የሚደረገው ተደርጎ ምዕራቡ ዓለም ለመተባበር ፍቃደኛ ላይሆን ይችላል፡፡ በሃሳቡ ገፍቶበት፣ የኢትዮጵያ መንግስትን በሌላ ዘዴ፣ ለምሳሌ መጠነ-ሰፊ ማዕቀብ በመጣል ሕዝቡ እንዲከፋ ማድረግ፣ በመፈንቅለ መንግስት ወይም በሌላ ዘዴዎች መሪዎችን በመግደል ለማስወገድ ወይም ሌሎች ሙከራዎች ሊያደርግ ይችላል፡፡ ይህን መሰሉ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ተገንዝቦ መንግስት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግም ሆነ ሕዝቡን ማሰናዳት ይኖርበታል፡፡ አምላክ ኢትዮጵያን ይጠብቃታል ብሎ ማመን ይቻላል፣ በመጀመሪያ ግን ኢትዮጵያ ራሷን መጠበቅ አለባት፡፡

ቸር ጊዜ ይግጠመን!

ኢትዮጵያ ታቸንፋለች!

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com