ዜና

በአማራ ክልል በአንድ ጀምበር የ247 ሚሊየን ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር እየተካሄደ ነው

Views: 73
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 15 ፣ 2013 በአማራ ክልል የ2013 የአረንጓዴ አሻራ በአንድ ጀምበር የ247 ሚሊየን ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር እየተካሄደ ይገኛል።
በዛሬው ዕለትም 247ነጥብ 8 ሚሊየን ችግኞች በ24 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ይተከላሉ ተብሏል።
በክልሉ ርዕሰ መዲና ባህርዳር እየተካሄደ ባለው የችግኝ ተከላ መርሃግብር ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ፥ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ወንዞች ውሃን እንጅ አፈር ይዘው እንዳይሄዱ የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የሚተከሉ ችግኞች የታላቁ የህዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ ፋይዳቸው የላቀ መሆኑን ገልፀዋል።
የተተከሉ ችግኞች እስኪፀድቁ እንክብካቤ እንዲደረግም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የባህርዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ከድህነት ለመውጣት በሚደረገው ጥረት አይነተኛ መሳሪያ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መለስ መኮንን አብዛኛዎቹ የሚተከሉት ችግኞች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው አትክልትና ፍራፍሬ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በከተማ ውበትና ጽዳት ስራ የሚታወቀው ጋሽ አበራ ሞላና በማህበራዊ ሚድያ በርካታ ተከታዮች ያሉት የማህበራዊ አንቂ ጌጡ ተመስገን ህብረተሰቡ ችግኝ በመትከል የአረንጓዴ አሻራ ሀገራዊ መርሃ ግብርን እንዲያሳካ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢቢሲ እንደዘገበው በአማራ ክልል በ2013 የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር 2 ቢሊየን ችግኞች ይተከላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com