ዜና

የቬንትሌተር ዋጋ ስንት ይሆን?

Views: 448

መነሻ፡-

ራስን ከኮቪድ- 19 (ኮሮና) ቫይረስ ገዳይ ተውሳክ ጥቃት ለመጠበቅ፣ ከማጀት እስከ አደባባይ፣ ብዙ ተባለ፤ ብዙ ተደከመ፡፡ እጅን በ‹‹ሳኒታይዘር›› ማጽዳት፤ አፍንጫና አፍን በ‹‹ማስክ›› መከለል፤ የፈላ ውሃ፣ ቅመማ ቅመም፣ ቅጠላ ቅጠል፣ ሥራሥር በአመጋገብ ውስጥ መጠቀም፤ ራስን በምግብ እና በገንቢ ፈሳሽ ማጠናከር፡፡ በር ዘግቶ አደብ አድርጎ መቀመጥ፡፡ በየጊዜው ከንክኪ በኋላ እጅ በሳሙና መታጠብ፤ ተራርቆ መቀመጥ፣ ወዘተ … ተባለ፡፡  ጥቂት ለማስታወስ ከታች የተጫነው ‹‹ሊንክ›› ላይ ማንበቡ ለጥንቃቄ ያነቃቃ ይሆናል፡፡

https://ethio-online.com/archives/8594      ኮሮና ቫይረስ እና ቅመማ ቅመም፤

https://ethio-online.com/archives/8790  እርድ እና ቁንዶበርበሬ

የተባለው ሁሉ  በአግባብ ተተገበረ ወይም ተሸራርፎ ተተገበረ፣ የሆነው ሆነ፣ ….  እኛም የቻልነውን ተከላከልን፣ በሽታውም የቻለውን አጠቃን… የበረታ ታሞ ዳነ፣ የተረቱትንም ነብስ ይማር አላለሁ፡፡  ግብግቡ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ የሞት ሽረት ግብግብ፡፡ የአንዲት በአይን የማትታይ ተውሳክ ጥቃት እና የቸልተኛው የሰው ልጅ ጉዳት፡፡

አሁን አሁንማ ኮሮና ቫይረስ በሽታ ጭቃ ጅራፍ ሆነብን፡፡ ችግሩን የሚያባብሱት ብዙ ማህበራዊ፣ ባሕላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወዘተ ክስተቶች አሉ፡፡  ከዚህም አንዱ የመተንፈሻ መርጃ የሆነው ቬንትሌተር እጥረት መሆኑ እሙን ነው፡፡ ይህ የመተንፈሻ መርጃ ዋጋው ውድ ቢሆን ወይም ተመጣጣኝ፤ በገበያ እጅግ ተፈላጊ ስለሆነ፣ ለዓለም ሁሉ ባይዳረስ ምን ይደረግ!?

ሀ/ የቬንትሌተር እጥረት፣

በእኛ አገር ገና ከዛሬ አንድ አመት በፊት ይህ ማሽን እጥረት መኖሩን የሙያው ባለቤቶች ይገልፁ ነበር፡፡ ሜዲካል ኤክስፕረስ ዶት ኮም ይህን ገልፆ ነበር፡፡

Ethiopia races to bolster ventilator stockpile for coronavirus fight  April 3 2020

https://medicalxpress.com/news/2020-04-ethiopia-bolster-ventilator-stockpile-coronavirus.html

ዘንድሮ በሽታው እንዲህ ሲስፋፋ፤ የዚህ ማሽን እጥረት ችግር ጎልቶ ይወጣል፡፡ ለምሳሌ በአንድ ሆስፒታል ብዛታቸው 4ዐ ቬንትሌተር ቢኖር እና ቁጥራቸው ከዚያ በላይ የሚሆኑ ሕሙማን ቬንትሌተር ቢያስፈልጋቸው፤ ለማን ይሰጣል፤ ለማን ይቀራል? በምን መሥፈርት ይለያሉ?  

… ይህ እንኳን ለአስታማሚ፣ ለሐኪም ቀርቶ ከውጪ ከሩቅ ሆኖ ለሚሠማ፣ ለሚጽፍ፣ ለሚያነብ፤ … ቅስም ሰባሪ ጉዳይ ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ከጥቂቶች ጋር መላልሼ አውርቼ፤ አዝኜ፣ አልቅሼ… ቢቸግረኝ ብዬ ይቺን ፃፍኩኝ፡፡

የሰው ልጅ ለገንዘብ እጥረት ብድር ይወስዳል፤ ለምግብ እጥረት እርዳታ ይጠይቃል፤ የተገኘውን ይመገባል፣ ውሃ እየጠጣ ቀን ይገፋል፣ … መረሬ አፈር ያላምጣል፣ ጥቂት ቀናት ይሰነብታል.. ጊዜን ይገፋል፡፡  

አንድ ሰው በበሽታ ተይዞ መተንፈስ ተስኖት ሲሰቃይ፤ በሰውነቱ ውስጥ ለደረሰበት አየር እጥረት ምን መፍትሔ ይፈልጋል!?  

መፍትሔው ያለው በሐኪሞች እጅ ነው፤ የመተንፈሻ መሳሪያውን በአግባቡ መግጠም እና የማስታመም ጥበብ ያለው በሐኪም እጅ ነው፡፡   ሐኪሙም ቢሆን ያ በጠቢባን እጅ የተሠራው ማሽን ከሌለ ምን ማድረግ ይችላል!? 

ለ/ ሙያ ከጎረቤት ነው

ባለፈው አመት ሰኔ ወር ላይ ጎረቤታችን ኡጋንዳ፣ ማካራሬ ዩኒቨርሲቲ እና ኪራ ሞተርስ ኮርፖሬሽን በካምፓላ ውስጥ ዋጋው ተመጣጣኝ የሆነ ቬንትሌተር ሠሩ፡፡  በዚህ ላይ ከስር በሚገኘው ‹‹ሊንክ›› በሰፊው አንብቡ፡፡

https://rif.mak.ac.ug/update-about-production-of-the-low-cost-ventilator-in-uganda/

Makerere University is living up to the slogan ‘We Build for the Future’! June 9, 2020

በእኛ አገር ያሉን ሙያተኞች ይህን መሠል ማሽን ለመሥራት ማበረተቻ እና ድጋፍ ቢደረግ ይሠሩት ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡ በሌላም በኩል ከሥራ ውጪ የሆኑ፤ በትንሽ ብልሽት የተነሳ ከሥራ ውጪ የተደረጉትን ማሽን መጠገን ይችላሉ፡፡

ሐ/ ተሯሩጦ መግዛት፤

እስከ ዛሬ ከተወሰኑ አገራት ይህ ማሽን እርዳታ ተሰጥቶናል፡፡ እርዳታ የተሰጠው ደረጃው ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በዚህ ደረጃ የሆነውን ለመግዛት ወይ በቂ ገንዘብ አይኖርም ወይም እቃው አይገኝ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ከየትኛውም የዓለም አገራት ጥግ የተገኘውን ገዝቶ መጠቀም እውቀት ነው፤ ብልኃት ነው፡፡

መ/ ውድ የኢትዮጵያ ባለሐብቶች

ይህንን  የመተንፈሻ መርጃ ማሽን (ቬንትሌተር) የሕክምና ሕግ እና ደንብ በሚፈቅደው መሠረት ወደ አገራችን እንዲመጣ ትብብር አድርጉ፡፡

ሠ/ ሌሎቻችሁም ድምጽ አሠሙ

የሙያው ባለቤቶች፣ ጋዜጠኞች፣ ሁላችሁም በዚህ ጉዳይ ላይ ድምጻችሁን አሠሙ፡፡

ማጠቃለያ፡-

ለዚህ ገዳይ ተውሳክ፣ አሁንም ቢሆን ከመከላከል እስከ ማክሰም፣ ፈጽሞ መዘናጋት የለብንም፡፡ የተነገረውን ምክር እንተግብረው፡፡ የጎደለውን እንረዳዳ፣ በገንዘብ፣ በምክር፣ በሙያ፣ በጉርብትና፣ በጓደኝነት፣ በሁሉ ጉዳይ እንተባበር፡፡ የበሽታው ደረጃ ለመተንፈስ ካስቸገረ፣ ጉዳዩ ከባድ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ቬንትሌተር ወርቃማ ማሽን ሆነ፡፡ ይህን ማሽን እናፈላልገው፡፡  እግዚሐአብሔር በቸርነቱ ይርዳን፤ አግባብ ካለው ጥንቃቄ ጋር፡፡ ሠላም!!!

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com